ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን

ከ 4 ሰአት በፊት

ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ክርክር ባይድን ቃላቶች እየጠፏቸው ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው ታዩ።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው ምርጫ የመጀመሪያውን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የተላለፈ ክርክር አድርገዋል።

ከዚህ ክርክር በፊት በርካታ አሜሪካውያን ጆ ባይደን የተጫናቸው እርጅና ለተጨማሪ አራት ዓመታት አገሪቱን መምራት ያስችላቸው እንደሆነ ሲጠይቁ ነበር።

የአሜሪካውያኑ ስጋት ትክክል መሆኑ በዚህ የምርጫ ክርክር ላይ ጎልቶ ታይቷል።

ፕሬዝዳንት ባይደን አንዳንድ ንግግራቸው ግልጽ አልነበረም። ቃላት ጠፍቶባቸው ንግግራቸው ሲወለካከፍ እና ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው ታይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ባይደን በክርክሩ ወቅት ድምጻቸው እንደመታፈንም ብሎ ነበር። በክርክሩ መካከል የጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የፕሬዝዳንቱ ድምጽ እንደመታፈን ያለው ጉንፋን ይዟቸው ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ክርክሩን ሲከታተል የነበረው የቢቢሲው አንቶኒ ዛከር ፕሬዝዳንቱ ምናልባት ጉንፋን ነገር ይዟቸው ሊሆን ይችላል ግን ሕመሙ የማምለጫ ምክንያት ነው የሚመስለው ይላል።

ለ90 ደቂቃዎች ዘልቆ በቆየው ክርክር ባይደን በትራምፕ ተበልጠው ታይተዋል። በተለይ የክርክሩ ማብቂያ አካባቢ አንዳንድ መልሶቻቸው ምክንያታዊ አይመስሉም ነበር።

የቀድሞ የጆ ባይደን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የነበሩት ኬት ቤዲንግፊልድ ከክርክሩ በኋላ በሰጡት አስተያየት “ይህ ለጆ ባይደን ጥሩ የሚባል ክርክር አይደለም” ብለዋል።

ኬት ፕሬዝዳንቱ አገሪቱን ለመምራት አቅሙ እና ኃይሉ እንዳላቸው ለማሳያት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

ባይደን ብዙም ትርጉም የማይሰጥ ነገረ ሲናገሩ ትራምፕ ተቀብለው፤ “ምን ማለት እንደፈለገ አልገባኝም። እርሱም እራሱ ምን እያለ እንደሆነ የገባው አይመስለኝም” ሲሉ ተሳልቀውባቸዋል።

አንቶኒ እንደሚለው በክርክሩ ወቅት ባይደን የፈለጉትን ማሳካት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ለንግግራቸው ትራምፕ በቁጣ ምላሽ እንዲሰጡ ማድረጋቸው ነው ይላል።

ባይደን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ለራሳቸው ክብር ስለሌላቸው ከልቅ የወሲብ ፊልም ትናዋይት ጋር ተኝተዋል ሲሉ ትራምፕ በብስጭት “ልቅ ወሲብ ከምትሰራው ጋር ወሲብ አልፈጸምኩም” ሲሉ መልሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባይደን የቀድሞ ፕሬዝዳንት በወንጀል ክስ የተከሰሱ ፖለቲከኛ መሆናቸውን በማስታወስ ትራምፕን አንጓጠዋል።

በክርክሩ ወቅት ትራምፕ የባይደን የምጣኔ ሃብት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን አጥብቀው ሲተቹ ባይደን በበኩላቸው ትራምፕ በወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ መሪ መሆናቸውን ለማስታወስ የ2020 የምርጫ ውጤትን በኃይል ለመቀልበስ ጥረት ያደረገ ግለሰብ ነው ብለዋቸዋል።

የቢቢሲው አንቶኒ ዛከር ከዚህ ክርክር በኋላ አሜሪካውያን ዘንድ መነጋጋሪያ የሆነው በክርክሩ ወቅት የተነሱ ጉዳዮች ላይ የትኛው እጩ ምን አቋም አለው ሳይሆን የባይደን ዕድሜ ጉዳይ ሆኗል ብሏል።

ሕዳር ወር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራቶች በጆ ባይደን፤ ሪፓብሊካኖች ደግሞ በትራምፕን ተወክለው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ፖለቲከኞች መስከረም 2017 ለሁለተኛ ዙር ክርክር የፊት ለፊት እንዲገናኙ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።