
ከ 8 ሰአት በፊት
ከኬንያ ሕዝብ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ጄንዚ (ጄኔሬሽን ዙመርስ) የተሰኘው እና በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው አፍላ ትውልድ ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን ስጋት ሆኗል።
የኬንያን ብድር ለመክፈል በሚደረግ ጥረት እና በቁጣ በተሞላ ወጣት መካከል ተይዘው የነበሩት ዊሊያም ሩቶ አሁን የግብር ጭማሪ ዕቅዳቸውን እርግፍ አድርገው ትተውታል።
“የምንቃወመው ግብር መክፈል ስለማንፈልግ አይደለም። ስለእውነት ከሆነ መክፈል እንፈልጋለን! ገንዘቡ ምን ላይ እንደዋለ ግን ማየት እንፈልጋለን” ስትል ስሟን መግለጽ ያልፈለገች አንዲት ወጣት ተቃዋሚ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“በሥልጣን ላይ ለመቆየት ከፈለግክ ከሕዝብ ጎን ቁም! ሕዝቡን አዳምጥ” ብላለች።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው የተቃውሞ ሰልፎችን አደራጁ። ፕሬዝዳንታቸውን “ዛካዮ” አሏቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግብር በመሰብሰብ ከሚታወቀው ዘኪዎስ የተዋሱት ስም ነው።
ተቃዋሚዎች ሐሙስ ዕለትም መሐል ናይሮቢ ተሰባስበዋል። የተገደሉትን ለማሰብ እና የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ወደ ሆነው ስቴት ሐውስ ለማምራት ነው ዕቅዱ።
ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ለወራት የዘለቀውን የኑሮ ውድነት ትኩሳት ተከትሎ ነው።
ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ በርካታ የዓለም አገራት በኑሮ መወደድ እየተሰቃዩ ነው። ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟ እና የጋዛ ጦርነት ችግሩን አባብሶታል።
በዚህ ላይ ደግሞ ኬንያውያን የነዳጅ እና የስንዴ ድጎማ ተነስቶባቸዋል። በየዕለቱ የታክስ ጭማሪ መደረጉ ደግሞ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ጣራ አስነክቶታል።

‘ወጣት የነበር ጣት’
በወጣቶች የሚመራው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ብዙዎችን ወደ ድህነት ይከታል ያሉትን የፋይናንስ ሕግ እንዳያጸድቁት ለፕሬዝዳንት ሩቶ አስቀድሞ አስጠንቅቆ ነበር።
የመጀመሪያው ዕቅድ ከባድ ነበር። ከዳይፐር ጀምሮ እስከ ዳቦ (16 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ) አለፍ ሲል ደግሞ ከሞባይል የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እስከ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ድረስ ታክስ ተቆልሎባቸው ነበር።
ማክሰኞ ዕለት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ ተጀመረ። ሆኖም ብዙም ሳይዘልቅ ወደ ከፍተኛ ብጥብጥ ተሸጋገረ። ናይሮቢ ውስጥ ፖሊስ አትለፉ ያላቸውን ቦታ ጥሰው የገቡ ወጣት ተቃዋሚዎችን ተኩሶ ገድሏል።
የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኬኤንሲኤችአር) የ22 ሰዎችን መሞታቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።
ለአስር ዓመታት ኬንያን አጋጥሟት አያውቅም በተባለው ከባድ ተቃውሞ የፓርላማው የተወሰነ ክፍል በእሳት ተያይዟል።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ አክሎም በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን በመግለጽ ምርመራ ጀምሯል።
- የኬንያ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቀልበስ ጦሩ እንዲሰማራ ወሰነ28 ሰኔ 2024
- “ኃይል የሕዝብ ነው” ያሉት ኬንያውያን ወጣቶች27 ሰኔ 2024
- የኬንያን ፓርላማ እና አባላቱን ዒላማ ባደረገው ተቃውሞ ምን ተከሰተ?26 ሰኔ 2024

ፕሬዚዳንቱ ለምን ሃሳባቸውን ቀለበሱ?
ማክሰኞ ዕለት የአገሪቱ የፓርላማ አባላት የፋይናንስ ረቂቅ አዋጁን አጸደቁ። 24 ሰዓታት ሳይሞላ ግን ፕሬዝዳንት ሩቶ ውድቅ ለማድረግ ተገደዱ።
ፕሬዝዳንቱ በቀጥታ በተላለፈ መልዕክታቸው “ተሸንፌያለሁ” አሉ።
በዚህ ሳያበቁ ፕሬዝዳንት ሩቶ ለፓርላማው አፈ-ጉባዔ በጻፉት ደብዳቤ በረቂቅ ሕጉ ውስጥ ያሉት አንቀጾች በሙሉ እንዲሰረዙ አዘዙ።
ረቂቅ ሕጉንም ሙሉ ለሙሉ አነሱ። ፓርቲያቸው የፓርላማውን አብዛኛውን መቀመጫ ስለሚቆጣጠር የሕዝብ እንደራሴዎቹ ሃሳቡን ይደግፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሩቶ የግብር ጭማሪ ለመድረግ ያቀዱት ሐምሌ 1 በሚጀመረው የበጀት ዓመት 2.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ነበር።
በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ውስት 5.7 በመቶ የነበረውን የበጀት ጉድለት ወደ 3 ነጥብ 3 በመቶ ለማውረድ ነበር የመንግሥት ዓላማ።

አዲሱ የኬንያ ትውልድ ዓላማውን እንዴት አሳካ?
በኑሮ ውድነቱ የተነሳ የሚብሰለሰሉት የኬንያ ወጣቶች ብቻ አይደሉም። ባለፈው ዓመት ከላይቤሪያ እስከ ሞዛምቢክ ድረስ በበርካታ አገራት ተቃውሞ እና ግጭት ተፈጥሯል።
“ይህ እንቅስቃሴ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በፍጥነት የተጠነሰሰ እንቅስቃሴ ነው። እስካሁንም መሪው ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም” ሲሉ በኬንያ ስላለው የተቃውሞ ሰልፍ የቻተም ሐውስ የአፍሪካ ተንታኝ የሆኑት አሌክስ ቫይን ገልጸዋል።
“በኬንያ ያለው ሚዲያ ጠንካራ በመሆኑ ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ይታያል። ኬንያውያንም የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀማቸው ድንቅ ነው። ከዚህ ቀደም የተቃውሞ ቀስቃሾቹ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ እንሞክር ነበር። የአሁኑ በብዙ አካባቢዎች የተሰራጨበት መንገድ ግን ኬንያ በአህጉሪቱ ምን ያህል የላቀ እና የተሳሰረች እንደሆነ ያሳያል” ብለዋል።
የሜንቶሪያ ኢኮኖሚክስ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ኬን ጊቺንጋ በበኩላቸው የተቃውሞው በጣም ግዙፍ ነበር ብለዋል። ይህ የሆነውም የፕሬዝዳንት ሩቶ የፋይናንስ ፖሊሲዎች “በወጣቶች ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ ነው” ብለዋል።
ጊቺንጋ እንደሚሉት ከሆነ እንደምግብ ባሉ የፍጆታ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣሉ “ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ክፉኛ ይጎዳል” ብለዋል።
ጭማሪው የንግድ ድርጅቶችን ከሥራ የሚያስወጣ በመሆኑ ኩባንያዎች ሠራተኞችን እንዳይቀጥሩ እና ለወጣቶች የሚፈጥሩትን የሥራ ዕድል ያመናምነዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ ወደ ስልጣን ሲመጡ ለስኬት የሚለፉትን እንደሚያግዙ ቃል መግባታቸው ወጣቶቹ ብዙ እንዲጠብቁ አድርጓቸው ነበር። አዲስ አካሄድ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ሁኔታውን ለወጣት ኬንያውያን ተስፋ አስቆራጭ አድርጎታል።

የኬንያ ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ ነው?
የኬንያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የብድር ዕዳ አለበት። ብዙ አገራትም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ግብፅ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የምትከፍለው 11 ቢሊዮን ዶላር አለባት። አርጀንቲና ደግሞ 31 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈል ይጠበቅባታል።
ኬንያ ለአይኤምኤፍ መክፈል የሚጠበቅባት 3.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት። ይህ አሃዝ ከጋና የሚበልጥ ሲሆን፣ ከአንጎላ ደግሞ ያነሰ ነው።
ከ2021 ጀምሮ ከአይኤምኤፍ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ በኬንያውያን ዘንድ ቅሬታ እያደገ መጥቷል።
በፍጥነትም ብዙዎች በበይነ መረብ ዘመቻ ከፍተው አዲሱን የብድር ስምምነትን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። ቀደም ሲል የተወሰዱ ብድሮች በጥሩ ሁኔታ አልተያዙም በማለትም አይኤምኤፍ ብድሩን እንዲያነሳ አሳስበዋል።
የአይኤምኤፍ የብድር ውሳኔ ከዚህ በተቃራኒ ነበር። ተቋሙ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለአገሪቱ የሚሰጠውን ብድር ከ2.3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.4 ቢሊዮን ዶላር አሳድጓል።
የአይኤምኤፍ መስፈርቶችም የፖለቲካውን ስስ ጎን የሚነካኩ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ትኩረት አድርጓል ሲሉ የኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ አፍሪካ የምጣኔ ባለሙያ የሆኑት ሻኒ ስሚት-ሌንግተን ተናግረዋል።
እአአ ከ2022 እስከ 2023 ባለው ጊዜ የነዳጅ እና የስንዴ ድጎማዎችን ማስወገድን የሚያካትት ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ ተቋሙ አዟል።
አይኤምኤፍ በኬንያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። ዋና አላማው አገሪቱ አስቸጋሪ ፈተናዎችን እንድታልፍ መርዳት መሆኑንም አክሏል።
“ባለፉት ቀናት በኬንያ የተከሰቱት አሳዛኝ ክስተቶች በጣም አሳስቦናል። በሰዎች ሕይወት መጥፋት እና በርካቶች መጎዳት አዝነናል” ሲሉ የአይኤምኤፍ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጁሊ ኮዛክ ተናግረዋል።
በ2023 የኬንያ ዕዳ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ (ጂዲፒ) 73.5 በመቶ ደርሷል። ለንጽጽር ያህል በተመሳሳይ ወቅት የጎረቤት አገር ታንዛኒያ የዕዳ ጫና ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ 45.2 በመቶ ብቻ ነበር።
በዚህ ሳያበቃ ኬንያ ከፍተኛ ሥራ አጥነት አለባት። ይህ ቁጥር ደግሞ ከ25 ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ነው።
ኢኮኖሚው ደግሞ የተለያየ መልክ አለው።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የኬንያ ሽልንግ በዓለም ላይ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በጣም ጠንካራው ለመሆን ችሎ ነበር። እንደ ማዕከላዊ ባንክ ዘገባ ከሆነ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት ከ5 በመቶ በላይ እንደሚያድግ ትንበያ ተሰጥቷል። ይህንን አሃዝ ከደቡብ አፍሪካ 1.3 በመቶ እና ከናይጄሪያ 3.2 በመቶ ጋር መነጻጸር የሚችል ነው።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ኬን ጊቺንጋ ወጣቶች “ራሳቸውን ለማስተዳደር እየታገሉ ነው” ብለዋል።
“የኢኮኖሚ እድገቱ ወደ ሥራ ፈጠራ አይተረጎምም። አዎን የአገር ውስጥ ምርት እያደገ ነው፤ ነገር ግን ከሥራ ፈጠራ ጋር በእኩል እየሄደ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ ለዚህ ተጠያቂው ከእሳቸው በፊት የአገሪቱ መሪ የነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው ይላሉ። ኬንያታ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በመንገድ እና በባቡር መስመር ዝርጋታ ላይ ከፍተኛ ወጪ አውጥተዋል በሚል ከፍተኛ ትችት ይሰነዘርባቸዋል።
እነዚህ ኢንቨስትመንቶች መጨረሻ ፍሬያማ ሊሆኑ ቢችሉም ለጊዜው ግን ተራ ኬንያውያንን ከማሳደግ ይልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እየጠቀሙ ይመስላል።
ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ፕሬዝዳንት ሩቶ የፋይናንስ አዋጁን ካነሱ በኋላ ሁሉም ዐይኖች ትኩረት ያደረጉት አገሪቱ ከአይኤምኤፍ ጋር ባላት ቀጣይ ድርድር ላይ ይሆናል ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሻኒ ስሚት ሌንግተን ተናግረዋል።
“ኬንያ አሁን ያላትን ስምምነት ለማደስ ወይም እንዲራዘም እንደምትጠይቅ እናምናለን” በማለት “ሰዎችን ያበሳጨው የታክስ መለወጥ ነው” ይላሉ።
ሃኪ እንደሚሉት ከሆነ ኬንያውያን በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት ተቆጥተዋል።
“መንግሥት ገንዘቡን ስለሚያወጣበት መንገድ እምነት የላቸውም። ሰዎች የሚሰበሰበው ግብር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደሚውል ቢሰማቸው ወደ ጎዳና አይወጡም ነበር” ብለዋል።
ሚት-ሌንግተን በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ አሁን የመንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ እና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመነጋገር አንድ ዓይነት ስትራቴጂ ለመፍጠር ለመወያየት ማቀዳቸውን ተናግረዋል ።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ አጥጋቢ ነው፣ አይደለም የሚለውን በተመለከተ ተቃዋሚዎቹ በሚቀጥሉት ቀናት ሃሳባቸውን ግልጽ ያደርጋሉ።