ቤት አልባዎች የሰሯቸው መጠለያዎች

ከ 7 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተሞች ቤት አልባዎች የሚዘረጓቸውን መጠለያዎች እንዲከለክሉ 6 ለ3 በሆነ ድምጽ ውሳኔ አስተላለፈ።

ውሳኔው ቤት አልባዎች አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዳይኖሩ ካለው እሳቤ ጋር በሚጣጣም መልኩ እንደተወሰነ ተገልጿል።

ይህም የአሜሪካ የመኖሪያ ቤት እጦት ቀውስ ከጀመረበት ከ1980ዎቹ በኋላ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ጉልህ ውሳኔ ነው ተብሏል።

በዚህም መሰረት የተለያዩ ከተሞች አስተዳደሮች ሕገ መንግሥቱ የደነገገውን የጭካኔ እና ያልተለመደ ቅጣትን ባስወገደ መልኩ በሕዝብ ሥፍራዎች ላይ መጠለያዎች እየዘረጉ ባሉ ሕጉን ማስከበር እንደሚችሉም ተጠቅሷል።

ይህንን ውሳኔ ለማሳለፍ መነሻ የሆነው ኦሪጎን በተሰኘችው ግዛት በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ሦስት ቤት አልባዎች በውጭ መጠለያዎችን በመዘርጋት እያደሩ ነው በሚል ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ ነው።

ከተማዋ “በንጽህና እና በደኅንነት ምክንያቶች” ቤት አልባዎች በሕዝብ ሥፍራዎች መጠለያዎችን እንዳይዘረጉ የሚከለክሉ የወንጀል ቅጣቶች አስፈላጊ መሆኑንም ሚያዝያ ወር ላይ በዋለ ችሎት ተከራክሮ ነበር።

ቤት አልባ ነዋሪዎቹ ከተማዋ ምንም ዓይነት ሕዝባዊ መጠለያ እንደሌላት ጠቅሰው ቅጣቶቹ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት የጣሰ ነው ሲሉም መከራከሪያ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ወግ አጥባቂው ዳኛ ኒል ጎርሶች የከተማዋ የመጠለያ ሕጎች “ውርደትን” የማያስከትሉ ናቸው ብሏል።

አክለውም ሕጉ ቤት አልባ መሆንን እንደ ወንጀል እንደማያይና እገዳው በግለሰቦች ድርጊት ላይ ያተኮረ እንደሆነም ተከራክረዋል።

“በከተማዋ ሕግ መሰረት በውጭ መጠለያ የሰሩት ቤት አልባ ሆኑም፣ ለመዝናኛ የዘረጉ ወይም ተማሪዎች ለተቃውሞ ቢያደርጉም ምንም ለውጥ አያመጣም” ሲሉ ዳኛው አትተዋል።

ውሳኔውን የተቃወሙ ሦስቱን የሊበራል ዳኞች የወከሉት ዳኛ ሶንያ ሶቶማየር በበኩላቸው “እንቅልፍ መሰረታዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳይ እንጂ ወንጀል አይደለም።ቤት አልባነት የበርካታ አሜሪካውያን እውነታ ነው” ብለዋል።

በርካታ ከተሞች ውሳኔውን በደስታ ተቀብለው መግለጫ ሰጥተዋል።

የሳንፍራንሲስኮ ከተማ፣ ከተሞች የሕዝብ ሥፍራዎችን በብቃት ለማስተዳደር እንደሚረዳቸው ገልጻለች። የዚህ ውዝግብ ማዕከል የሆነችው የኦሪጎኗ ግራንትስ ፓስ ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ለሚደረጉ እርምጃዎች ከጠበቆቻቸው ጋር እንደሚገናኙ አስታውቃለች።

በአሜሪካ ውስጥ ቤት አልባነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ይገኛል። ለዚህም የቤቶች እጥረት እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋው መናሩ እንደሆነ ይጠቀሳል።

ባለፈው ዓመት 653 ሺህ ሰዎች ቤት እንደሌላቸው የአሜሪካ መንግሥት አኃዝ የሚያሳይ ሲሆን ይህም ቆጠራ ከተጀመረበት ከ2007 ጀምሮ ከፍተኛው ነው ተብሏል።