
ከ 8 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ኪንግደሙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ድንኳኖችን ተክለው በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እየተቃወሙ ያሉ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው የማይወጡ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው አስጠነቀቀ።
ዩኒቨርስቲው ኦክስፎርድ አክሽን ፎር ፓለስታይን ለተሰኘው ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ለቆመው ቡድን በላከው ደብዳቤ በግቢው በራድክሊፍ ካሜራ ያሉ ድንኳኖች እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንዲፈርሱ ብሏል።
በዩኒቨርስቲው ከተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ውጭ ያሉ ድንኳኖች እንዲፈርሱ ተደርጓል።
የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናውን ዩኒቨርስቲው እንዲያቆም እና የኢንቨስትመንት ፖሊሲውን እንዲያስተካክል እየጠየቁ ይገኛሉ።
እስራኤል በጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።
ዩኒቨርስቲው በደብዳቤው “የሰላማዊ ተቃውሞን አስፈላጊነት ዕውቅና እንደሚሰጠው” ገልጾ፣ በጋዛ እና በእስራኤል ያለውን ሁኔታ አሳሳቢነት ይረዳል ብሏል።
ሆኖም ተማሪዎቹ በግድ ወደ ዌሊንግተን አደባባይ መግባታቸውን እንዲሁም የፈተና ትምህርት ቤቶችን መቆጣጠራቸው “በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።
- የጋዛን ጦርነት በሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ታዋቂው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ፕሮግራም ተሰረዘ26 ሚያዚያ 2024
- ፍልስጤማውያን በእስራኤል ላይ ሲያካሂዱት የቆየው ‘ኢንቲፋዳ’ ምንድን ነው?29 ሚያዚያ 2024
- ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያቀረበችው የዘር ማጥፋት ክስ16 ጥር 2024
“ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት በራድክሊፍ ያለውን የተዘረጉ ድንኳኖች ለማንሳት ማስታወቂያ ሰጥቷል። በተሰጣችሁ ማስታወቂያ መሰረት ድንኳኖቹን አፍርሳችሁ መሬቱን እንድትለቁ ታዝዟል” ይላል።
“ድንኳኖቹ እስከ ሰኔ 30 ድረስ እስካልተነሱ ድረስ ዩኒቨርስቲው የመሬት ይዞታው እንዲመለስለት ለፍርድ ቤት ያመለክታል” ብሏል።
ተማሪዎቹ በሥፍራው ላይ እስከዚያች ዕለት ድረስ በድንኳኖች ውስጥ መገኘታቸውን በተመለከተ ምንም ዓይነት የዲሲፒሊን እርምጃ እንደማይወስድም አክሏል።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እየፈጸመችው ያለችውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ከ37 ሺህ 765 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውም በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡብ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና 253 ታጋቾች መወሰዳቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።