
ከ 8 ሰአት በፊት
ሽታዬ ሆማ (ዶ/ር) ልጅነቷን መለስ ብላ ስታስታውስ መሆን ትፈልግ የነበረው የሕክምና ባለሙያ (ነርስ) ነበር።
ለዚህ የልጅነቷ ህልሟ ደግሞ ለሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ ) ትምህርት ያላት ፍቅር ትልቁን እገዛ አድርጓል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ ግን የትምህርት ሚኒስቴር ድልድል ከህልሟ ሳይሆን ‘ከዛሬው እንጀራዋ’ ጋር አገናኛት።
ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘችው ሽታዬ በአገር፣ በአህጉር እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ስሟን ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ ሥራ የሠራችው ከዚህ በኋላ ነው።
የግብርና ተመራማሪዋ ሽታዬ የከፍተኛ ትምህርቷን የተከታተለችው፣ የዶክተሬት ዲግሪዋን ያገኘችው፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሽልማቶችን የተቀበለችው በዚሁ የግብርና ምርምር ሥራዋ ነው።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ የዱረም ስንዴ ምርምር አስተባባሪ የሆነችው ሽታዬ፣ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በዚህ የስንዴ ምርት ብትታወቅም፣ ነገር ግን የምታመርተው የአገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት እንደማይችል ትናገራለች።
ዱረም ስንዴ ፓስታ እና ማካሮኒ ለማምረት የሚውል የስንዴ ዓይነት ሲሆን፣ በአገር ውስጥም በስፋት ተፈላጊ ነው።
ሽታዬ (ዶ/ር) የምታስተባብረው የምርምር ቡድንም የዚህን የስንዴ ዝርያ ለማሻሻል የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ትናገራለች።
የዱረም ስንዴ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ አገራት በሞሮኮ፣ በቱኒዝያ፣ በአልጄሪያ፤ ከአውሮፓ አገራት ደግሞ ጣልያን የተለያዩ የባህል ምግቦቻቸውን ለማምረት እንዲሁም ለፓስታ እና ማካሮኒ ሥራ በብዛት ይፈለጋል ትላለች።
ሽታዬ (ዶ/ር) እና ባልደረቦቿ የሚያከናውኗቸው የምርምር ሥራዎች የዚህን የስንዴ ዘር ምርታማነት መጨመር እንዲሁም በብዛት ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ነው።
- ለዕርዳታ እጆችዋን የምትዘረጋው ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ትችል ይሆን?26 ጥቅምት 2022
- ከዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሳይንቲስቶች መካከል አንዷ የሆኑት ኢትዮጵያዊት12 የካቲት 2020
- ከጆ ባይደን የአሜሪካን ትልቅ ሽልማት የተቀበሉት ተመራማሪው ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ ማን ናቸው?25 ጥቅምት 2023
‘ከ189 ተማሪዎች መካከል ብቸኛዋ ሴት ነበርኩ’
የስንዴ ተመራማሪዋ ሽታዬ (ዶ/ር ) በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ ነው የምትሠራው።
ተመራማሪዋ በዱረም ስንዴ ላይ የምታደርገውን ምርምር አጠናክራ የቀጠለችው ከሦስት ዓመት በፊት በ2021 (እኤአ) የሦስተኛ ዲግሪዋን አሜሪካ ከሚገኘው የኮርኔል ዩኒቨርስቲ አግኝታ ከተመለሰች በኋላ ነው።
በምርምር ተቋሙ ውስጥ በዱረም ስንዴ ላይ የሚደረገውን የምርምር ሥራ ከማስተባበር ኃላፊነቷ ቀደም ብሎ በ2013 ነው ወደ ተቋሙ ተቀላቀለችው።
በሰበታ የመጀመርያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው ሽታዬ፣ በትምህርቷ “ተወዳዳሪ” እንደነበረች ትናገራለች።
በተለይ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ በርትታ ትሠራ እንደነበር የምታስታውሰው ሽታዬ፣ የሕክምና ባለሙያ የመሆን ፍላጎት ስለነበራት የባይሎጂ ትምህርት ከሁሉ በተለየ ይስባት ነበር።
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስትገባ ግን ምንም እንኳ የመጀመሪያ ምርጫዋ ነርሲንግ የነበረ ቢሆንም፣ የደረሳት ግን 13ኛ ምርጫዋ የነበረው ግብርና ሳይንስ ነው።
“የምፈልገውን ባለማግኘቴ በጣም አዝኜ ነበር” ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።
በወቅቱ ትምህርቷን አቋርጣ ዳግም አጥንታ በመፈተን ውጤቷን በማሻሻል የምትፈልገውን የትምህርት ዓይነት ለማግኘት ፈልጋ ነበር።
ይህንን ዕቅዷን ያማከረቻቸው መምህሮቿ ግን በተመደበችበት ትምህርት እንድትቀጥል እና በሂደት ምርጫዋ የሆነውን ዘርፍ መማር እንደምትችል ስለመከሯት በትምህርቷ ገፋችበት።
በወቅቱ በተመደበችበት የጅማ እርሻ ኮሌጅ ከነበሩ የ189 የግብርና ትምህርት ክፍል የዲፕሎማ ተማሪዎች መካከል ብቸኛዋ ሴት እንደነበረችም ታስታውሳለች።
የመምህሮቿን ምክር ሰምታ በግብርና ትምህርት የቀጠለችው ሽታዬ በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ በቃች።
ከተመረቀች በኋላ ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎችን እየመለመለ ይቀጥር የነበረው የኢትዮጵያ ግብርና ምርመር ኢንስቲትዩት ቢሾፍቱ በሚገኘው የምርምር ማዕከሉ በረዳት ተመራማሪነት ቀጠራት።
የማደግ ህልሟን ይዛ ሥራዋን የጀመረችው ሽታዬ፣ በስድስት ወር ውስጥ እናቷ በመሞታቸው የመማር እና የመለወጥ ዕቅዷ ጥያቄ ውስጥ ወደቀ።
ብዙም ሳይቆይ የአባቷ መሞት ደግሞ በርካታ ኃላፊነቶች በትከሻዋ ላይ እንዲወድቁ አደረገ።

ከጠንካራዋ ሽታዬ ጎን ያለው ባለቤቷ
ምንም እንኳ ነርስ የመሆን ህልሟ ባይሳካም፣ ሽታዬ (ዶ/ር) የመምህሮቿን ምክር ሰምታ ግብርና በማጥናቷ አትጸጸትም።
ስለዚህ በትምህርቷ ለመቀጠል ያሉትን አማራጮች ሁሉ ትመለከት ጀመር።
ይሁን እንጂ በተከታታይ ያጣቻቸው እናት እና አባቷ ለትምህርት የነበራትን ሞራል ጎዳው።
በዚህ ወቅት ነው ጓደኛዋ የነበረው እና በኋላም ባለቤቷ የሆነው ኃይለማርያም ተክለወልድ (ዶ/ር) ለትምሀርት ያላትን ዝንባሌ እና አቅም ዐይቶ እንድትማር አበረታት።
ሽታዬ ምክሩን ተቀብላ ወደ ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ በማምራት በዕጽዋት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አገኘች።
በወቅቱ በከፍተኛ ማዕረግ ትምሀርቷን ያጠናቀቀችው ሽታዬ (ዶ/ር) ወደ የኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት በመመለስ በተመራማሪነት ቀጠለች።
ሽታዬ እንደምትለው ያላትን ትጋት እና አቅም የተረዳው ባለቤቷ እያበረታታት ሁለት ዓመት ከሠራች በኋላ በኔዘርላንድስ ለሁለተኛ ዲግሪዋ የትምህርት ዕድል በማግኘቷ በዕጽዋት ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪዋን አገኘች።
ሽታዬ (ዶ/ር) የምርምር ሥራዋን እና ትምህርቷን ቀጥላ ሦስተኛ ዲግሪዋን በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርስቲ አጠናቀቀች።
ከዚህ ሁሉ የሽታዬ ስኬት ጋር አብሮ ስሙ የሚጠቀሰው የትዳር አጋሯ መሆኑን የምትናገረው ተመራማሪዋ፣ “ባለቤቴ ልዩ ሰው ነው። እኔ ስማር ልጆቻችንን እየተንከባከበ በማሳደግ ያበረታታኝ ነበር” ትላለች።
አክላም “በእርግጥ ሴቶች ከጎናቸው የሚያግዛቸው እና የሚያበረታታቸው ካለ ውጤታማ መሆን ይችላሉ። እኔም ውጤታማ የሆንኩት ዛሬ በሕይወት የሌለው ባለቤቴ ስለደገፈኝ ነው” በማለት ተመሰክራለች።
“ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች እንደሚባለው ሁሉ ከጠንካራ ሴት ጀርባም ጠንካራ ወንድ አለ። ለዚህም እኔ ምስክር ነኝ” በማለት ባለቤቷ የነበረውን ጠንካራ ድጋፍ ትገልጻለች።
ሴት የግብርና ተመራማሪዎች
ሽታዬ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ ልክ እንደ ቡና ሁሉ ለፓስታ እና ለማካረኒ ስንዴ መገኛ (center of diversity and center of origin) ናት” ትላለች።
እነዚህ የአገር በቀል የሆኑ የዱረም ስንዴ ዝርያዎች ላይ የተለያዩ ምርምሮችን የምትሠራው ሽታዬ (ዶ/ር) በተሻሻለ የስንዴ ዘር ላይ ላደረገችው የምርምር ሥራ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሽልማቶችን እና እውቅናዎችን አግኝታለች።
ሽታዬ (ዶ/ር) ከBorlaug Global Rust Initiative (BGRI) የግንድ ዋግን የሚቋቋም ስንዴ ላይ ላበረከተችው የምርምር ሥራ ሽልማት አግኝታለች።
“ምርምር የቡድን ሥራ ነው” የምትለው ተመራማሪዋ፣ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጪ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት በኬንያ፣ በሜክሲኮ፣ በአሜሪካ ከሚገኙ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን እንደምትሠራ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ገልጻለች።
አሁን ያገኘቻቸው ሽልማቶች እና እውቅናዎች እንደሚያበረታቷት የምትናገረው ሽታዬ (ዶ/ር) ለወደፊት በርካታ የምርምር ሥራዋችን ለማበርከት ሞራል እንደሚሆኗት ታምናለች።
በኢትዮጵያ የሚገኙ እና በምርምር ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ አካላት ከተባበሩ “በስንዴ ምርት ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለሌሎች እንተርፋለን” የምትለው ሽታዬ ይህ ግን በጠንካራ ምርምር እና ድጋፍ መታገዝ እንዳለበት ትመክራለች።
“የኢትዮጵያ ሴቶች ሊያውቁ የሚገባው ቤት ውስጥ ካለባቸው ኃላፊነት በላይ ማበርከት እንደሚችሉ ነው። እና ሴቶችን የምመክረው ሥራቸውን እንዲወድዱ እና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ነው።”
በእኛ ባህል ሴቶች በቤት ውስጥ ሥራ ራሳቸውን ገድበው ልጅ በመውለድ እና በማሳደግ ላይ ተገድበው ይታያሉ የምትለው ሽታዬ (ዶ/ር)፣ ድጋፍ ከተደረገላቸው ከቤት አልፈው በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ የራሷን ታሪክ በአስረጅነት በማቅረብ ታስረዳለች።
አክላም ሴቶች ጥንካሬያቸውን የሚያውቁ ከሆነ፣ ወንዶች በተሰማሩበት መስክ ጭምር ውጤታማ ይሆናሉ ትላለች።