ተቃዋሚ በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ ሲወሰድ

ከ 7 ሰአት በፊት

ባሳለፍነው ሳምንት በኬንያ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ በተወሰደው የኃይል እርምጃ ታፍነው የተወሰዱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ።

የፋይናንስ ሕጉን የተቃውሞ ሰልፍ ሲመሩ እንደነበር የተጠረጠሩ 35 የሚጠጉ ሰዎች ታፍነው የተወሰዱት በፖሊስ በተቀነባበረ አሰሳ መሆኑ ተገልጿል።

ታፍነው የተወሰዱት አብዛኞቹ የተለቀቁ ሲሆን፣10 አክቲቪስቶች [የማኅበረሰብ አንቂዎች] አሁንም ያሉበት አለመታወቁን የኬንያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ለቢቢሲ ገልጿል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ አይዛክ ምዋውራ በበኩላቸው “ መፈንቅለ መንግሥት ማድረግ የሚፈልጉ ወንጀለኞች ሰላማዊ ሰልፉን ለመጠቀም ሞክረዋል” ሲሉ ፖሊስ ላይ የቀረበውን ክስ ተከላክለዋል።

ተይዘው ከተለቀቁ ተቃዋሚዎች መካከል የተወሰኑት ስልካቸውንና ላፕቶፓቸውን መነጠቃቸውን እና በጨለማ ክፍል ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸውን ተናግረዋል።

የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚደንት ፌዝ ኦዲያምቦ “ አብዛኞቹ ሰውነታቸው ሲንቀጠቀጥ እንደነበር እና ስላሳለፉት ማውራት እንደማይፈልጉ” ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወጣቶች የተመራው ተቃውሞ የጀመረው ባለፈው ሳምንት ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በመዲናዋ ናይሮቢ እና በሌሎች ከተሞች አደባባይ በመውጣት የኑሮ ውድነቱን ያባብሳል የተባለውን የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

ሆኖም ማክሰኞ ዕለት ከሰዓት ፖሊስ ከአገሪቷ ፓርላማ ደጅ ላይ በተሰባሰቡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከከፈተ በኋላ ውጥረቱ ተባብሶ የነበረ ሲሆን ተቃዋሚዎችም የጸጥታ ኃይሎችን ጥሰው ፓርላማ ውስጥ ገብተዋል።

የሐኪሞች ማኅበር እንዳስታወቀው ማክሰኞ ዕለት በነበረው ተቃውሞ ቢያንስ 23 ተቃዋሚዎች ተገድለዋል።

በሚቀጥለው ቀን በተቃዋሚዎች ጫና የደረሰባቸው ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በምክር ቤት አባላት የፀደቀው ረቂቅ ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችለውን ፊርማቸውን እንደማያኖሩ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንቱ ጨምረውም በመንግሥት የሚፈፀም አስገድዶ መሰወር እንደ ፖለቲካ መሣሪያ መጠቀምን ለማስቆም ቃል ገብተዋል።

ምክትላቸው ሪጋቲ ጋቻጉም ለተቃዋሚዎች መሰወር ብሔራዊ የፖሊስ የደኅንነት አገልግሎትን ተጠያቂ አድርገዋል።

ረቡዕ ዕለት ፕሬዚደንት ሩቶ ሁሉም የተሰወሩ ግለሰቦች መለቀቃቸውን ቢገልጹም፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ግን ይህ እውነት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ኦዲያምቦም ፕሬዚደንቱ እየተናገሩ በነበረበት ሰዓት እንኳን 12 ተቃዋሚዎች የገቡበት አልታወቀም ብለዋል።

“ ሆኖም ከዚያ በኋላ ሁለቱ ያሉበት የታወቀ ሲሆን አንደኛው በሻይ ቅጠል እርሻ ውስጥ እርቃኑን ተጥሎ ተገኝቷል።” ብለዋል።

የተለቀቁት አብዛኞቹ አካላዊ ጉዳት ባይደርስባቸውም በከፋ ጭንቀት ተዳርገው ስለነበር ያሳለፉትን እንኳን መናገር አልፈለጉም ብለዋል የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚደንቷ።

ፕሬዚደንቷ እንዳሉት “ የተወሰኑት ከናይሮቢ ውጭ እርሻ ውስጥ ሌሎች ደግሞ መንገድ ዳር ላይ ተጥለው ነበር የተገኙት።”

በደረሰባቸው ስቃይ ምክንያትም አንዳንዶቹ በከተማዋ ደኅንነት ስለማይሰማቸው ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ፣ ሌሎች ደግሞ አገሪቷን ለቀው መውጣት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ኦዲያምቦ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ30 በታች ሲሆን ከቤታቸው አሊያም ከመንገድ ላይ ፖሊሶች እንደሆኑ በሚታመኑ የታጠቁ ኃይሎች ነው የተወሰዱት።

አብዛኞቹ በኤክስ የማኅበራዊ መድረክ ላይ የታክስ ሕጉን በግልጽ ሲቃወሙ የነበሩ ናቸው።

ተቃዋሚዎቹ እንዳሉትም አግተው የወሰዷቸው የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞው ላይ ስለነበራቸው ተሳትፎ እና ማን በገንዘብ ሲደግፋቸው እንደነበር ጠይቀዋቸዋል።

ተሰውረው ከነበሩ ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ የሆነው ጆርጅ ዲያምቦ በኤክስ ገጹ ስለደረሰበት ስቃይ ገልጾ ሕዝቡ እስካሁን የገቡበት ላልታወቀ ተቃዋሚዎች እንዲፀልይ ጠይቋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ጃ ፕራዶ በሚል ስሙ የሚታወቀውና ለተጎዱት ተቃዋሚዎች የደም ልገሳን ሲያስተባብር የነበረው ዶክተር ኦስቲን ኦሞንዲ ከተሰወሩት መካከል ይገኝበታል።

ለስድስት ሰዓታት ተይዞ ከቆየ በኋላ ሐኪሞች ተቃውሞ ለመምታት መግለጻቸውን ተከትሎ መለቀቁን የኬንያ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፀሐፊ ዴቪጂ አቴላህ ለቢቢሲ ኒውስ ደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

በመንግሥት የሚደገፈው የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በሕገ ወጥ መንገድ ታስረው የነበሩ ከ300 በላይ ሰዎች እንዲለቀቁ ማድረጉን ገልጿል።

የአገሪቷ ዋና ዳኛ ማርታ ኮሜ በበኩላቸው ‘በሕግ የበላይነት ላይ የተቃጣ ጥቃት’ ሲሉ የተቃዋሚዎችን መሰወር አውግዘዋል።