
ከ 6 ሰአት በፊት
የፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራዶስላው ሲኮርስኪ በዩክሬን አየር ክልል ውስጥ ሆነው በፖላንድ ግዛት በኩል የሚወነጨፉ የሩሲያ ሚሳኤሎችን ለመምታት ከዩክሬን የቀረበላትን ሃሳብ አገራቸው እያጤነችው እንደሆነ አስታወቁ።
ይህ ዕቅድ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ወደ ዋርሶው አቅንተው በሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው የጋራ መከላከያ ስምምነት ውስጥ ተካቷል።
“አሁን በሃሳብ ደረጃ ነው ያለው። ስምምነታችን ምን እንደሚያካትት ይህንን ዕቅድ የምናጤነው ይሆናል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሲኮርስኪ በዋሽንግተን ለሚገኝ የአሜሪካ ኢንተርፕራይዝ ተቋም ተናግረዋል።
ከሴንት ፒተርስበርግ የሚወነጨፉ የሩሲያ ሚሳኤሎች ከፖላንድ ድንበር በቅርብ ርቀት በምትገኘው የሊቪቭ ከተማ አቅራቢያ በኩል ቤላሩስን አቋርጠው ለ40 ሰኮንዶች ያህል ወደ ፖላንድ አየር ክልል ገብተው ነው የዩክሬን ኢላማቸውን የሚመቱት ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሩሲያ ሚሳኤሎች በፖላንድ አየር ክልል ላይ የሚቆዩበት ጊዜ ያጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገራቸው ምላሽ እንዳትሰጥ እንዳደረጋትም አምነዋል።
ሆኖም አሁን የቀረበው ዕቅድ በፖላንድ አቅጣጫ ወደ ምዕራብ ዩክሬን የሚያቋርጡ ሚሳኤሎችን ይሸፍናል።
“ከጦርነቱ የፊት መስመር ላይ ያለን አገር ነን። የሩሲያ ሚሳኤሎች የአየር ክልላችንን ይጥሳሉ። በስህተት እንደሆነ እንገምታለን” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
- ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባቸው ተማሪዎች ከታገቱ ከ10 ቀናት በላይ ሆናቸው12 ሀምሌ 2024
- የአየር ብክለት የኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አትሌቶችን እንዳይጎዳ የሳይንስ ጥረትከ 7 ሰአት በፊት
- በርካቶች የተቀጠፉበትን የኬንያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የፖሊስ አዛዡ ከሥልጣን ለቀቁከ 6 ሰአት በፊት
“ሚሳኤሎቹ ወደ አየር ክልላችን ሲገቡ ተኩሰን ብንመታቸው ስብርባሪዎቹ ለዜጎቻችን እና ለንብረታችን ጠንቅ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ችግር ይፈጥራል” ሲሉም አክለዋል።
“አሁን ዩክሬናውያን ሚሳኤሎቹ የፖላንድን ግዛት አቋርጠው ሲወነጨፉ በእኛ አየር ክልል ላይ መትታችሁ ጣሏቸው። እባካችሁ እያሉን ነው” ብለዋል።
“ይህ ለእኔ ራስን መከላከል ነው፤ ነገር ግን አሁንም ዕቅዱን በማጤን ላይ ነው” ብለዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት አንድ ያልታጠቀ የሩሲያ ሚሳኤል ከቤላሩስ ድንበር 500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትኘው ባይድጎስዝክዝ መንደራቸው እንዳረፈ የገለጹት ሚኒስትሩ ሆኖም ጉዳት አላደረሰም ብለዋል።
ከዚያ ቀደም ብሎ ግን ዩክሬን በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ የተወነጨፈ የሩሲያ ሚሳኤልን መትታ ስትጥል ሁለት የፖላንድ ዜጎች በሚሳኤሉ ስብርባሪዎች ተገድለዋል።
የፖላንድ የመከላከያ ሚኒስትር ውላዲስላው ኮስኒያክ በበኩላቸው አገራቸው ማንኛውንም የሩሲያ ሚሳኤልን ለመምታት ከመሞከሯ በፊት ከኔቶ አጋሮቿ ጋር እንደምትመክር እና ስምምነታቸውንም እንደምትሻ ተናግረዋል።
“እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በትብብር የተደረሰ ውሳኔ ብቻ ሊሆን ነው የሚችለው። የአንድ አገር ብቻ ውሳኔ ሊሆን አይችልም” ሲሉም በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ከፖላንድ የቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
“በዚህ ጉዳይ ላይ ቁልፉ አስተያየት የአሜሪካ ነው። አሜሪካ ሁኔታውን በጥርጣሬ ከማየቷ አንጻር ፖላንድ በእርግጠኝነት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በራሷ ልታከናውን አትችልም” ብለዋል።