ሙሽሮቹ አናንት አምባኒ እና ራዲካ መርቻንት
የምስሉ መግለጫ,ሙሽሮቹ አናንት አምባኒ እና ራዲካ መርቻንት

ከ 7 ሰአት በፊት

ብዙ የሚባለው ስንት ነው? ወራትን የፈጀው የእስያ ባለጸጋ ልጅ የሠርግ ድግስ ወደ መቋጫው በደረሰበት በዚህ ዕለት ብዙዎች የሚጠይቁት ጥያቄ ነው።

በዚህ ሳምንት የሚጠናቀቀው ሰርግ የሁለት የናጠጡ ቤተሰቦች ልጆች ነው። የቢሊየነሩ የሪሊያንስ ኢንዱስትሪዎች ሊቀ መንበር ሙኬሽ አምባኒ የመጨረሻ ልጅ አናንት አምባኒ ቢጤውን መርጦ በህክምና ዘርፍ የናጠጡ ሃብታም ለመሆን የበቁትን የቪረን እና ሻይላ መርቻንትን ሴት ልጅ ራዲካ መርቻንትን አግብቶ ጎጆ የሚቀልሱበት ነው።

አሁን ከሚካሄደው ዋነኛው ሰርግ ሥነ ሥርዓት በፊት የነበሩት አራት ወራት በሙሉ በድግስ የተሞሉ ነበሩ። የሚያምሩ አልባሳት፣ አስደናቂ ጌጣጌጦች እና የድግስ ማስጌጫዎች (ዲኮር) ብቻ ሳይሆኑ ሕንድ አሉኝ የምትላቸው እና ዓለም አቀፍ ከዋክብት የተሳተፉበት የሙዚቃ ድግሶች ተከናውነዋል።

“ከንጉሣውያን ሰርግ ይስተካከላል። የእኛ ቢሊየነሮች አዲሶቹ የሕንድ ማሃራጃዎች [ንጉሣዊያን ቤተሰቦች] ናቸው። ባለአክሲዮኖቻቸው በጣም ትልቅ ድል ያለ ድግስ ብቻ ነው የሚጠብቁት” ሲሉ ፀሐፊው እና አምደኛው ሾብሃ ዲ ተናግረዋል።

ሕንዳውያን “ሁልጊዜም ድል ያለ እና የተጋነነ ድግስ ይወዳሉ። [የሰርጉ ግዝፈት] ከአምባኒ ሀብት ጋር የሚስማማ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ሰርጉ ግን የጎረፈለትን አድናቆት ያህል ቁጣቸውን የሰነዘሩም ጥቂት አይደሉም። በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከድህነት ወለል በታች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት በሚንከራተቱባት እና የገቢ ኢ-ፍትሃዊነት በጣም በተስፋፋባት አገር ውስጥ እዩኝ እዩኝ ለማለት የፈሰሰውን ከፍተኛ ገንዘብ ተችተዋል።

“[ሰርጉ] የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ እንዳለማየት ወይም እንደመሳለቅ ሊታይ ይችላል። ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የሕንድ ሰርግ እጅግ በጣም አስደንጋጭ እየሆነ መምጣቱን ሊያሳይ ይቻላል” ሲሉ ፀሐፊው ሳንቶሽ ዴሳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እየተካሄደ ያለው ትልቅ ለውጥ አካል ነው። ከአንድ ወይም ከሁለት ትውልድ በፊት ስለ ሀብት በሹክሹክታ ይነገር ነበር። ዛሬ ግን ሃብት በተቻለ መጠን ጮክ ብሎ መናገር አለበት። ያኔም ቢሆን የዚህ ሰርግ ሚዛን ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል” ብለዋል።

ዋናው ድንግስ ሙምባይ ላይ ይከናወናል
የሙሽራው ወላጆች ኒታ እና ሙኬሽ አምባኒ
የምስሉ መግለጫ,የሙሽራው ወላጆች ኒታ እና ሙኬሽ አምባኒ

አምባኒዎች ሰፊ የቢዝነስ ኢምፓየር ገንብተዋል። ከነዳጅ፣ ከቴሌኮም፣ ከኬሚካል፣ ከቴክኖሎጂ እና ከፋሽን እስከ ምግብ ኢንዱስትሪ ድረስ ያልገበቡት ዘርፍ የለም። ቤተሰቡ ሕንድ ውስጥ መነጋገሪያ በመሆንም ይታወቃል።

በፎርብስ መጽሄት ባለሃብቶች ደረጃ መሠረት የሙሽራው አባት የ66 ዓመቱ ሙኬሽ ምባኒ በ115 ቢሊዮን ዶላር ሃብት በዓለም ላይ ካሉ ባለጸጎች መካከል በ10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የ29 ዓመቱ ሙሽራ አናንት አምባኒ የአባቱ ንብረት በሆነው በሬዚሊያንስ ኢንደስትሪዎች ውስጥ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ነው።

ሙኬሽ አምባኒ እና ሌላኛው ሕንዳዊ ባለሀብት ጋኡታም አዳኒ ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መንግሥት ጋር ቅርበት እንዳላቸው ይነገራል። መንግሥት ሁለቱን ባለሃብቶች ያለአግባብ ይደግፋል ሲሉ ተቃዋሚዎች ይከሳሉ። የሕንድ መንግሥትም ሆነ ባለሃብቶቹ ውንጀላውን ያስተባብላሉ።

የአምባኒ ቤተሰብ የሃብት መጠን እና ክብር በሕንድ ውስጥ ይታወቃል። ቀሪው ዓለም ግን እስካሁን ላያውቀው ይችላል።

መጋቢት ወር ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ። አምባኒ ለልጃቸው የሦስት ቀን የቅድመ ሰርግ ድግስ ሲያሰናዱ ሁሉም ነገር ተለወጠ።

የቦሊውድ አክተሯ ጆንቪ ካፑር
የምስሉ መግለጫ,የቦሊውድ አክተሯ ጆንቪ ካፑር
የሙዚቃ ድግስ

ድግሱ በምዕራብ ጉጅራት በምተገኘው በቤተሰቡ የትውልድ ከተማ ጃምናጋር ነበር የተሰናዳው። ከተማው በዓለም ትልቅ የሆነው የአምባኒ የዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ የተተከለበት ነው።

በድግሱ ላይ አንድ ሺህ 200 የክብር እንግዶች ተሳትፈዋል። የሜታው (ፌስቡክ) ማርክ ዛከርበርግ እና የማይክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ በድግሱ ላይ ከተገኙት ስመ ጥር ሰዎች መካከል ናቸው።

ግብዣው የተጀመረው ለድግሱ ተብሎ በተሠራ የመስታወት ቤት ውስጥ በተሰናዳ የእራት ግብዣ ነበር። አስደናቂው ቤት ራዲካ በኒውዮርክ ከተማ የኮሌጅ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ በምትወደው ፓልም ሐውስ ቅርጽ የተሠራ ነው።

ድግሱ ቀጠለና ሪሃና መድረኩን ተቆጣተረች። የአምባኒ ቤተሰብ አባላት ከኮከቧ ድምጻዊት ጋር በመድረክ ላይ ሲወዛወዙ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።

ሙሽሮቹ ከሜታ (ፌስቡክ) መሥራች ዛከርበርግ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሙሽሮቹ ከሜታ (ፌስቡክ) መሥራች ዛከርበርግ ጋር
አምባኒዎች ከሪሃና ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሙሽሮቹ ከሪሃና ጋር

ስመ ጥር ምግብ አብሳዮች ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ ሁለት ሺህ የሚደርሱ ምግቦችን አዘጋጅተው በቅንጡ ድንኳኖች ውስጥ ለነበሩ እንግዶች አቅርበዋል።

የዝግጅቱን የአለባበስ በተመለከተ ባለ 10 ገጽ መመሪያም ተዘጋጅቷል። “የደን” ጭብጥን ያካተተው የቤተሰቡ ንብረት የሆነው የእንስሳት ማቆያ ስፍራን ለመጎብኘት የቀረበ ነው። ለእራት እና ለሙዚቃ ድግስ የሚሆን አለባበስን የሚመለከት መመሪያም ነበር።

ሙሽራዋ በልዩ ትዕዛዝ የተሠሩ የተለያዩ ልብሶችን ለብሳ ነበር። ከእነዚህም መካከል ሁለት የሐር የሙሽራ ቀሚሶች ሲሆኑ፣ አንደኛው በ20 ሺህ ስዋሮቭስኪ ክሪስታሎች ያጌጠ ሲሆን፣ ሁለተኛውን ለመሥራት ደግሞ 5 ሺህ 700 ሰዓታት እንደፈጀበት ተነግሯል።

ሙሽራው በአብዛኛው የዶልቼ ኤንድ ጋባና አልባሳትን መርጧል። 1.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ ያለውን ሪቻርድ ሚሌ የተሰኘ የእጅ ሰዓት አጥልቆ ነበር። ዛከርበርግ እና ሚስቱ ፕሪሲላ ቻን ሰዓቱን በአድናቆት ሲመለከቱ የሚያሳየው ቪዲዮ ሕንድ ውስጥ ብዙ ተመልካች አግኝቶ ነበር።

ጋዜጦች እና ድረ ገፆች ከዓለም ዙሪያ የመጡ እንግዶች የታደሙበትን የእነዚህን ግዙፍ ድግሶች ተከታትለው ዘግበዋል። “ይህ ልክ ማሃራጃዎች ከ100 ዓመታት በፊት የሚያደርጉት ዓይነት ነበር” ሲል ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ሙሽሮቹ (ከመሃል) ከቤተሰቦቻቸው ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሙሽሮቹ (ከመሃል) ከቤተሰቦቻቸው ጋር

የሕንድ መንግሥት በአንድ ጀምበር የከተማዋን ትንሽ አውሮፕላን ማረፊያ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲል ሰየማት። ሠራተኞችን ጨመረ እና ቤተሰቡን የሚያገለግሉ ወታደራዊ እና የአየር ኃይል አባላትን አሰማራ። ይህ ደግሞ ተቃውሞ አስከትሎበታል።

የሦስት ቀኑ ድግስ በመብራት ትዕይንት እና ርችት ሲጠናቀቅ በቀጣይ የተዘጋጀውን ድግስ ለመገመት ያስቻለ ነበር።

በሰኔ ወር ጥንዶቹ እና እንግዶቻቸው ቅድመ ሰርግ ድግሳቸውን ከአገር ውጪ አደረጉ። በርካታ የቦሊውድ ኮከቦችን ያቀፈው ይህ ፓርቲ በጣሊያን በሚገኘው የቲርሄኒያን ባሕር ዳርቻ ተጀምሮ ወደ ፈረንሳይ በሚደረግ የቅንጦት መርከብ ጉዞ የተከናወነ ነበር።

ሰርገኞቹ በሮም፣ በፖርቶፊኖ፣ በጄኖዋ እና በኬን ለምሽት ድግስ መቆማቸው ከአካባቢውን ሰዎች ቅሬታ አስነስቶባቸዋል።

በሙሽሮቹ የሚወደዱት ባክስትሪት ቦይስ፣ ኬቲ ፔሪ ጣሊያናዊው አንድሪያ ቦሴሊ ሙዚቃዎቻቸውን አቅርበዋል።

በዚህ ሳምንት በተጀመረ ሌላ የሰርግ ድግስ ደግሞ ሙምባይ በሚገኘው የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ጀስቲን ቢበር ተገኝቶ ሙዚቃዎቹን አቅርቧል።

ቢበር በመድረኩ ጫፍ ላይ ሲዘፍን ሙሽሪት እና ጓደኞቿ አብረውት ሲያዜሙ የሚያሳየው ቪዲዮ 38 ሚሊዮን ዕይታን አግኝቷል። ግጥሙን ልቅም አድርገው አብረው ሲዘፍኑ ታይተዋል።

ጀስቲን ቢበር መድረክ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ጀስቲን ቢበር መድረክ ላይ
ሙሽሮቹ
የምስሉ መግለጫ,ሙሽሮቹ

ቤተሰቡ ለሰርጉ ድምቀት ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ ድግሱ አሳይቷል። አዴል በሰርጉ ማሳረጊያ ላይ ትዘፍናለች ቢባልም ቤተሰቡ ግን ምንም አልተነፈሰም።

በእርግጥ ሕንድ ለትልቅ ሰርጎች እንግዳ አይደለችም። ከአሜሪካ ቀጥሎ ለሰርግ ከፍተኛ ወጪ የምታወጣ አገርም ናት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰርግ ሃብት የሚታይበት፤ የፉክክር ማሳያ እና ደረጃ የሚታይበት አዝማሚያ እየሆነ መምጣቱን የሻዲ መሥራች ቲና ታርዋኒ ተናግረዋል።

ውድ የሆኑ ሰርጎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አርዕስተ ዜናዎችን ሲቆጣጠሩ አይተናል። ለምሳሌ በ74 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሰርግ በአውሮፓውያኑ 2016 ተደግሷል።

ሌሎቹ የአምባኒ ልጆችም ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው የቅድመ ሰርግ ድግሶችን አሰናድተዋል። ሂላሪ ክሊንተን እና ጆን ኬሪ እአአ በ2018 በተደረገው የኢሻ አምባኒ ቅድመ ሰርግ ድግስ ላይ ተገኝተዋል። ቢዮንሴ ደግሞ ድግሱን አድምቃዋለች።

ከአንድ ዓመት በኋላ ተደረገው የአካሽ አምባኒ የቅድመ ጋብቻ ድግስ ላይም ኮልድፕሌይ ተባለው ታዋቂ ባንድ ሙዚቃዎችን አቀርቧል።

ኢቫንካ ትራምፕ እና ኒታ አምባኒ
የምስሉ መግለጫ,ኢቫንካ ትራምፕ እና ኒታ አምባኒ
ታዋቂው ሻሩክ ኻን
የምስሉ መግለጫ,ታዋቂው ሻሩክ ኻን

አምባኒዎቹ ይህ ሰርግ ምን ያህል እንደሚያስወጣቸው አልገለጹም። አርያ ግን “ከ132 እስከ 156 ሚሊዮን ዶላር አውጥተዋል” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ሪሃና በሰርጉ ላይ ሙዚቃዋን ለማቅረብ 7 ሚሊዮን ዶላር እንደተከፈላት ተነግሯል። ለጀስቲን ቢበር ደግሞ 10 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎታል።

የሕንድ ባህላዊ ቅርሶችን ለማሳየት እና የሰርጉን ገጽታ ለማጉላት በጃምናጋር 14 ቤተመቅደሶችን ለመገንባት ገንዘብ ወጥቷል። የሰርጉ አካል በማድረግ አምባኒዎች ለ50 ደካማ ጥንዶችም የጅምላ ሰርግ ደግሰዋል።

ቤተሰቡ ሁሉንም ነገር ያደረገው ሁሉም የአምባኒ ልጆች በማግባታቸው ይህ የቤተሰቡ የመጨረሻው ሰርግ ይሆናል በሚል ነው።

እያንዳንዱ ክስተት ግን ትችትንም አስከትሎ ነበረ። ቀድሞም በትራፊክ መጨናነቅ ምትታወቀው ሙምባይ በድግሱ ምክንያት ሁኔታዎቹ ይበልጥ በመወሳሰባቸው ነዋሪዎች ሲያማርሩ ነበር።

አምባኒዎች አቅም ለሌላቸው ጥንዶች የጅምላ ሰርግ ደግሰዋል
የምስሉ መግለጫ,አምባኒዎች አቅም ለሌላቸው ጥንዶች የጅምላ ሰርግ ደግሰዋል

ይህ የዘመኑ የዓለማችን ድል ያለ የሰርግ ድግስ ለሕንድ የሰርግ ኢንዱስትሪ አስደሳች የገበያ ዕድልን የፈጠረ እንደሆነ ይነገራል።

የፋሽን ዲዛይነር ሆኑት አናንድ ቡሻን እንደተናገሩት ይህ ለዲዛይነሮች ሥራቸውን ለማሳየት ጥሩ ዕድል የሚፈጥር ነው።

ታዋቂ ሰዎች በአንድ ድግስ አምስት ስድስት አልባሳትን መቀያየራቸው አንዳንድ ጊዜ “ትንሽ አድካሚ” ስሜት ሊኖረው እንደሚችል አምኗል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቦሊውድ ታዋቂ ፓፓራዚዎች [አሳዳጅ ፎቶግራፍ አንሺዎች] አንዱ የሆነው ቫሪንዳር ቻውላ የድግሱን ፎቶግራፎች እየመረጠ ነው።

በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ የሚገኙ ጥቂት ታዋቂ ሰዎች በመግቢያው ላይ ለፎቶ ቆም ይላሉ።

እነዚህ ፎቶዎች በሚሊዮን ሚቆጠር ተመልካች ያገኛሉ።

“ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ትልልቅ ድግሶች ውስጥ መግባት ከባድ ነው። ይህ ቤተሰብ ግን እያንዳንዱን ነገር ፎቶ ማንሳት እንደንችል ለማድረግ መንገዱን አመቻችቷል” ብሏል።

“ንጉሣዊ ሰርግ ሲሆን፣ እኛም የንጉሣውያን እንክብካቤን እያገኘን ነው” ብሏል።

ድግሱ አንዳንድ የሙምባይ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል
የምስሉ መግለጫ,ድግሱ አንዳንድ የሙምባይ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል
ታዋቂዎቹ ቦሊውድ ተወንያን በድግሱ ላይ ተገኝተዋል
የምስሉ መግለጫ,ታዋቂዎቹ ቦሊውድ ተወንያን በድግሱ ላይ ተገኝተዋል

ለወራት ሲካሄድ የቆየውን የሰርግ ሥነ ሥርዓት ለማጠናቀቅ ከአርብ ጀምሮ እስከ ሰኞ የሚቆይ የማይቋረጥ ድግስ ይካሄዳል።

ለቀናት በሚካሄደው ሰርግ ላይ በርካታ ዓለም አቀፍ እና የሕንድ እጅግ ታዋቂ ሰዎች ስለሚሳተፉበት የሙምባይ ፖሊስም ሥነ ሥርዓቱን “ሕዝባዊ ዝግጅት” ሲል እንደሰየመው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ለዚህም የከተማዋ ፖሊስ ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ቦታ ዙሪያ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሏል።

ለዚህም በታላቋ ሙምባይ ከተማ በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ወቅት ዝግጅቶች በሚካሄድባት ስፍራ አካባቢ የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች ድግሱ እስከሚያበቃበት እስከ ሰኞ ድረስ ለበርካታ ሰዓታት ዝግ ይሆናሉ።

ከአርብ እስከ ሰኞ የሰርጉ ድግስ በሚካሄድበት አካባቢ ያሉ መንገዶች በሙሉ ለሰርጉ ታዳሚዎች ብቻ ክፍት ሆኖ ሌሎች እንዲንቀሳቀሱ አይፈቀድላቸውም።

የኪራይ አውሮፕላን አቅራቢ የሆነው ‘ክለብ ዋን ኤር’ ለሮይተርስ እንደገለጸው የሰርጉ አዘጋጅ ቤተሰብ ታዳሚዎችን ወደ ድግሱ ስፍራ ለማጓጓዝ ሦስት ትላልቅ ጄት አውሮፕላኖችን ተከራይቷል።