
ከ 7 ሰአት በፊት
በናይጄሪያ የአንድ ትምህርት ቤት ሕንጻ ተደርምሶ 22 ተማሪ ሕጻናት ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ከ130 በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሴንትራል ፕሌቱ የተባለው ግዛት ባለሥልጣናት አስታወቁ።
በግዛቲቱ ዋና ከተማ ጆስ ውስጥ የሚገኘው እና ሴይንት አካዳሚ በተባለው ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች በፈተና ላይ ሳሉ ነው ሕንጻው አርብ ዕለት የተደረመሰባቸው።
በርካታ ልጆችም በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው እንደነበረም ተዘግቧል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ሕጻናቱን ከኮንክሪት ከፍርስራሾች ስር ለማውጣት የቁፋሮ መኪኖችን፣ መዶሻዎችን እና እጃቸውን በመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል።
ፖሊስ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቀው ቢያንስ 22 ሕጻናት በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በርካቶቹ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው በአካባቢው በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ነው።
አደጋው የደረሰበት ትምህርት ቤት ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች ይገኙበት እንደነበር ተገልጿል።
አቤል ፉዋንዳይ የተባለው የአካባቢው ነዋሪ የጓደኛው ልጅ በአደጋው መሞቱን በመግለጽ “የአደጋው ሁኔታ በጣም አስፈሪ ነው” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።
- ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባቸው ተማሪዎች ከታገቱ ከ10 ቀናት በላይ ሆናቸው12 ሀምሌ 2024
- የአየር ብክለት የኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አትሌቶችን እንዳይጎዳ የሳይንስ ጥረትከ 7 ሰአት በፊት
- 156 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት በመላው ዓለም መነጋገሪያ የሆነው የቱጃሮቹ ሕንዳውያን ሰርግከ 7 ሰአት በፊት
ለትምህርት ቤቱ ሕንጻ መደርመስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፤ አደጋው የተከሰተው በግዛቲቱ ውስጥ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከባድ ዝናብ ከጣለ በኋላ ነው።
ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል የሚገኘው ተማሪ ዉሊያ ኢብራሂም ለፈረንሳይ ዜና አልግሎት – ኤኤፍፒ “ወደ ክፍል ከገባሁ ከአምስት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የተለየ ድምጽ ከሰማሁ በኋላ እራሴን ያገኘሁት እዚህ ሆስፒታል ውስጥ ነው። በክፍሉ ውስጥ ብዙ ነበርን፤ ፈተና እየተፈተንን ነበር” ሲል ተናገሯል።
ቺካ ኦቢዮሃ የተባለው ነዋሪ ደግሞ አደጋውን ተከትሎ በርካታ አስከሬኖችን እንዳየ እና ብዙ ተማሪዎች ደግሞ በሕይወት መውጣታቸውን ገልጿል።
“ሁሉም ሰው ተማሪዎቹን ለማዳን ጥረት ሲያደርግ ነበረ” በማለት የአካባቢው ነዋሪ በነፍስ አድን ጥረቱ ውስጥ መሳተፉን አመልክቷል።
በናይጄሪያ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት – ዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት ክርስቲያን ሙንዳውቴ በኤክስ ገጻቸው ላይ “በሴይንት አካዳሚ በደረሰው ጉዳት የታዳጊዎች ሕይወት መቀጠፉ በእጅጉ አሳዝኖኛል” ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
አክለውም “የትምህርት ቤቱ ሕንጻ ሲደረመስ የወደፊት ህልም ያላቸው ሕጻናት በፈተና ላይ ነበሩ። በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት ልጆች ቤተሰቦች ጥልቅ ሐዘኔን እገልጻለሁ” ብለዋል።
በቅርብ ዓመታት በናይጄሪያ ውስጥ ውስጥ በርካታ አደገኛ የሕንጻ መደርመሶች ያጋጠሙ ሲሆን፣ ለዚህም የባለሙያዎች ችግር፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የግንባታ ቁሶች እና ሙስና በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
በአውሮፓውያኑ 2021 በሌጎስ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የሀብታሞች ሰፈር ውስጥ በግንባታ ላይ የነበረ አንድ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ተደርምሶ ቢያንስ 45 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ተዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።