
ከ 7 ሰአት በፊት
የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የኬንያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የፖሊስ አዛዥ ጃፌት ኩሜ ከሥልጣን ለቀቁ።
ለሳምንታት በዘለቀው እና የተለያዩ ግብር ጭማሪዎችን ያካተተው የፋይናንስ ሕግ ውድቅ እንዲደረግ በተጠየቀበት የአደባባይ ተቃውሞ ከ40 በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ፖሊሶች ለተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በቀጥታ በጥይት ተኩሰው መግደላቸውን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውን እንዲሁም ሕጋዊ ባልሆነ ሁኔታ ማሰራቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።
የፖሊስ ኃላፊው ሥልጣን መልቀቅ የተሰማው ተቃውሞውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አብዛኞቹን ሚኒስትሮቻቸውን ካባረሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት የኬንያ ሕግ አውጪዎች አወዛጋቢውን የፋይናንስ ረቂቅ ካጸደቁ በኋላ የተቆጡ ወጣቶች ፓርላማውን ጥሰው መግባታቸው ይታወሳል። በምላሹም ፖሊስ ጎዳና ላይ በነበሩ ተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል።
- የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአገሪቱ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ካቢኔያቸውን በተኑ11 ሀምሌ 2024
- ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ያቀጣጠለው የኬንያ አዲሱ ትውልድ22 ሰኔ 2024
- “ኃይል የሕዝብ ነው” ያሉት ኬንያውያን ወጣቶች27 ሰኔ 2024
ሕዝባዊ ተቃውሞ የጠነከረባቸው ሩቶ በረቂቁ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ እና ውድቅ መደረጉን አስታውቀው ነበር።
ነገር ግን ሕዝባዊ ተቃውሞው መልኩን ቀይሮ እሳቸው ከሥልጣን እንዲወርዱ እና ተጨማሪ ማሻሻያዎችን የሚጠይቁ የአደባባይ ተቃውሞዎች ታቅደዋል።
የፖሊስ አዛዡ ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ምክትላቸው ዳግላስ ካንጃ ኃላፊነቱን እንደተረከቡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ቢሮ አስታውቋል።
የፖሊስ ኃላፊው ከሥልጣን መልቀቅ በርካታ ኬንያውንን ያስደሰተ ቢሆን፣ በተቃዋሚዎች ላይ ሲተኩሱ በቪዲዮ የተቀረጹ ፖሊሶች ለፍርድ አለመቅረባቸው አሁንም ጥያቄ እየተነሳበት ያለ ጉዳይ ነው።
ባለፈው ሳምንት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ቀርበው ከወጣቶች ጋር ውይይት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ የቪዲዮ ማስረጃ ካገኙ በእነዚህ የፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተው ነበር።
ሆኖም ይህ ተግባራዊ ስለመደረጉ የተባለ ነገር የለም።
ትናንት አርብ፣ ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም. ቢያንስ 11 አስከሬኖች የተወሰኑት አካላቸው ተቆራርጦ በናይሮቢ ቆሻሻ መጣያ ስፍራ መገኘቱ ተገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ካቀረቡ በኋላ የተገኙት እነዚህ አስከሬኖች ከሰሞኑ ተቃውሞ ጋር ስለመያያዛቸው እስካሁን አልተገለጸም።
በሁለት ዓመት የፕሬዚዳንትነታቸው ዘመናቸው በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባው ሩቶ በዚህ ሳምንት ከተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ጋር ተገናኝተው 150 አባላት ያሉት የውይይት ኮሚቴ በማቋቋም ለአገሪቱ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጨምሮ ቁልፍ ሚኒስትሮቻቸውን ከሥልጣን ያሰናበቱት ፕሬዚዳንቱ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት እንደሚመክሩ ተናግረዋል።