ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል ሰብዓዊ ድጋፍ በሚደረግበት ስፍራ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 90 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 300 ያህል ሰዎች መቁሰላቸውም ተገልጿል። እስራኤል በበኩሏ በጥቃቱ ዒላማ ያደረገችው ከፍተኛ የሐማስ መሪ የሆነውን ሞሐመድ ደይፍ እና ምክትሉ ራፋ ሳላማን ነው ብላለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቅዳሜ ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሁለቱ መሪዎች መገደላቸውን እርግጠኛ አይደለንም ብለዋል።

የእስራኤል ጦር የሰብአዊ ቀጠና ብሎ በሰየመው በዃን ዩኒስ አቅራቢያ በሚገኘው አል-ማዋሲ አካባቢ ነው ጥቃቱ የተሰነዘረው።

በአል-ማዋሲ የሚገኝ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው ጥቃቱ የተሰነዘረበት ቦታ “የመሬት መንቀጥቀጥ” ያጋጠመው ይመስላል።

ከአካባቢው የወጡ ቪዲዮዎች ደም የፈሰሳቸው ተጎጂዎች በቃሬዛ ላይ ሲጫኑ እና የህንጻ ፍርስራሽ ያሳያሉ።

ሰዎች ላያቸው ላይ ከተቆለለው ፍርስራሽ ስር ለመውጣት በእጃቸው ፍርስራሹን ለማንሳት ሲሞክሩም ይታያል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ከጥቃቱ በኋላ የተነሱትን ምስሎች በመተንተን በእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ድረ-ገጽ ላይ ሰብአዊ ቀጠና በሚል የተለየ አካባቢ ጥቃቱ መሰንዘሩን አረጋግጧል።

ኔታንያሁ ጥቃቱ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጡት በፀጥታ ኃይላቸው ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።

ኔታኒያሁ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ሁሉንም የሐማስ ከፍተኛ አባላትን ለማጥፋት ቃል ገብተዋል።

“በየትኛውም መንገድ ሁሉንም የሐማስን አመራሮች እንደርስባቸዋለን” ሲሉ ኔታንያሁ አክለው ገልጸዋል።

የሐማስ መሪ ኢስማኢል ሃኒዬህ በሰጡት መግለጫ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን “በአሰቃቂ ጭፍጨፋ” ለማደናቀፍ ሞከረዋል ሲሉ ኔታንያሁን ከሰዋል።

ሐማስ መሪዎቹ ዒላማ ነበሩ የሚለውን መግለጫ አስተባብሏል።

“እስራኤል የፍልስጤም መሪዎችን ኢላማ አድርጊያለሁ ካለች በኋላ ውሸት መሆኑ ሲረጋገጥ የመጀመሪያው አይደለም” ብሏል ሐማስ በመግለጫው።

የእስራኤል ጦር ኃላፊ በበኩላቸው ጥቃቱ የተፈፀመው ምንም አይነት ሠላማዊ ህዝብ በሌለበት “ክፍት ቦታ” ነው ብሏል።

አክለውም ቦታው “ዒላማ” ከመሆኑ በፊት “ትክክለኛ መረጃ” ተሰብስቦ ነበር ብለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ በሆስፒታል ውስጥ ህክምና ከሚሰጡ ዶክተሮች አንዱ ከህይወቴ “አስከፊ ቀናት አንዱ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር መሐመድ አቡ ራያ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ እንደተናገሩት ከሆነ አብዛኛዎቹ ሆስፒታል የደረሱ ሰዎች የሞቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በርካታ ስፍራ ቆስለዋል ብለዋል።

“በገሃነም ውስጥ የመሆን ያህል ነው” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸው፤ ከሟቾቹ መካከል ብዙዎቹ ሲቪሎች በተለይም ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአቅራቢያው ከሚገኘው የኩዌት ሆስፒታል የተወሰደው ምስል እንደሚያሳየው ከሆነ ተጎጂዎች ወለል ላይ ጭምር እየታከሙ እና አካባቢው በትርምስ መሞላቱን አሳይተዋል።

በዃን ዩኒስ የሚገኘው የናስር የህክምና ማዕከል ከመጨናነቁ የተነሳ መሥራት አለመቻሉ ተነግሯል።

ዳይፍ በድብቅ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል
የምስሉ መግለጫ,የሐማስ ከፍተኛ አመራር የሆነው ዳይፍ በድብቅ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል

ሞሐመድ ደይፍ ማን ነው?

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው የአልቃሳም ብርጌድ መሪው ሞሐመድ ደይፍ በእስራኤል በጣም ከሚፈለጉት ግለሰቦች አንዱ ነው።

እእአ በ2002 አይኑን ያጣበትን ጨምሮ ከበርካታ የግድያ እና በቁጥጥር ስር ለማዋል ከተደረጉ ሙከራዎች ማምለጡ ይነገራል።

እአአ በ1989 በእስራኤል ባለስልጣናት ታስሮ የነበር ሲሆን ከዚያ በኋላ የእስራኤል ወታደሮችን ለመያዝ በማለም የጦር ኃይል አቋቋመ።

እአአ በ1996 ከ10 በላይ እስራኤላውያንን የገደለውን የአውቶቡስ ፍንዳታ በማቀድ እና በመምራት እንዲሁም በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ሦስት የእስራኤል ወታደሮችን በመያዝ እና በመግደል ላይ ተሳትፎ አድርጓል በማለት እስራኤል ትከሰዋለች።

መስከረም 26 ሐማስ ጥቃት ሰንዝሮ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ እስራኤላውያን እና የውጭ አገር ዜጎች ተገድለው 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ከተወሰዱበት ጥቃት ጀርባ ከሚገኙ ከዋነኞቹ መሪዎች አንዱ ነው ተብሎ ይታሰባል።

ይህም እስራኤል ትልቅ ወታደራዊ ዘመቻ እንድትጀምር ያደረጋት ሲሆን በዚህም በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ38 ሺህ 400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

የሐማስ ባለስልጣን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ የቅዳሜው ጥቃት እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንደሌላት የሚያሳይ “ከባድ አባባሽ” ጥቃት ሲሉ ገልጸውታል።

በኳታር እና በግብጽ አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው የተኩስ አቁም ድርድር አርብ ዕለት ያለውጤት መጠናቀቁን ቢቢሲ ተረድቷል።