ባይደን

ከ 5 ሰአት በፊት

ፕሬዚዳንት ባይደን የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ጀግና፣ ቁርጥ ብለው ባወደሱበት ንግግራቸው ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪን “ፑቲን” ሲሉ መጥራታቸው በዓለም ዙሪያ አነጋጋሪ ሆኗል።

የአፍ ወለምታ ነው ተብሎ እንዳይታለፍ ከሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት ክርክር ላይ ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው ከመታየቱ ጋር ተደማምሮ በርካቶች ለወጣት ዕጩ ቦታውን ይልቀቁ እያሉ ነው።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ዲሞክራቶች እና ደጋፊዎቻቸው “እስከ መጨረሻው ድረስ ከጎንዎ ነን” በማለት ጸንተዋል።

ባይደን አርብ አመሻሽ ላይ በዲትሮይት ሚቺጋን በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተው ነበር።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከታዩ የምርጫ ዘመቻዎች ደማቅ ነው በተባለለትም በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ በርካቶች ባይደን “ከፉክክሩ አይወጡም” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በጩኽት እና በመፈክሮች ከጎናቸው መሆናቸውን የገለጹላቸው ባይደንም “እወዳደራለሁ፤ እንዲሁም አሸንፋለሁ!” ሲሉም ነው ቃል የገቡት።

መድረኩን ለቀው ሲወርዱ በቶም ፔቲ “አይ ዎንት ባክ ዳውን” በሚለው ዘፈን ታጅበው ነበር።

የድጋፍ ዘመቻው በተካሄደበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጂምናዚየም ሙዚቃው አስተጋባ። የፓርቲያቸው አባላትም በዕድሜ ምክንያት የደከሙትን ባይደንን ከጎን ደገፍ አድርገው ነበር የወሰዷቸው።

ባይደን የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ዜና እና መነጋገሪያ ሆነው ቢቀጥሉም የበርካታ ዲሞክራቶች ድጋፍ አልተለያቸውም።

ቢያንስ 80 የሚሆኑ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች ለ81 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት በአደባባይ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። እሳቸውም ከፉክክሩ አልወጣም በማለት መጽናታቸውን ተከትሎ ሌሎችም እንዲሁ የድጋፍ ጎራውን ተቀላቅለዋል።

ለበርካታ የፓርቲው አባላት፣ ባይደን በሕይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸው ተግባራት፣ መርሆቻቸው፣ እንዲሁም ከአራት ዓመታት በፊት ዶናልድ ትራምፕን መርታት መቻላቸው በሰሞኑ ከታየው ገጽታቸው ወይም መጪውን አራት ዓመታት በብቃት መምራት ይችላሉ ከሚሉ ስጋቶች በላይ ነው።

በዚህ ሳምንት ሐሙስ ባይደን ብቻቸውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ቢመረጡ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት እንዲሁም ኔቶን በተመለከተ ያላቸውን ራዕይ ዘርዘር ባለ መልኩ ነው ያስረዱት።

ነገር ግን በርካታ መገናኛ ብዙኃን ያተኮሩት ምክትላቸው ካማላ ሃሪስን “ምክትል ፕሬዚዳንት ትራምፕ” ብለው መጥቀሳቸው ላይ ነው።

ሆኖም አጋሮቻቸው የአገሪቱ የጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ የሆኑትን የባይደንን ንግግር በአድናቆት ነው የተመለከቱት። አጋሮቻቸው ብቻ ሳይሆን ከኦስካር ሽልማት በበለጠ 23 ሚሊዮን ሕዝብ ነው የባይደንን መግለጫ በቀጥታ የተከታተለው።

“የውጭ ፖሊሲያቸውን በተመለከተ ግልጽ ያሉ ሃሳቦችን አቅርበዋል፣ በጣም የሚደንቅ። ዶናልድ ትራምፕ ቢሆን ለአንድ ደቂቃ ያህል እንኳን ሃሳባቸውን አሳክተው ስለ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማውራት አይችሉም” ሲሉ የሰሜን ካሮላይና አስተዳዳሪ ሮይ ኩፐር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ባይደንን እንደሚተኩ ሲነገርላቸው የነበሩት የካሊፎርኒያው አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም በበኩላቸው “ሙሉ ድጋፌ ለባይደን ነው” ሲሉ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

የፔንስልቬንያው ተወካይ ብሬንዳን ቦይል በበኩላቸው ባይደን “ከወንጀለኛው እና አጭበርባሪው ትራምፕ ከአንድ ሚሊዮን እጥፍ በበለጠ ፖሊሲዎችን እንደሚያውቅ አሳይቷል” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

ባይደን በሥልጣን ዘመናቸው ያስመዘጓቧቸው ስኬቶች፣ በትራምፕ ላይ የተጎናጸፉትን ድል ጨምሮ መጪው ምርጫ ከወራት በኋላ በሚደረግበት እና ጥቂት ጊዜ በቀረበት ሁኔታ አዲስ ዕጩ የማምጣትን ሁኔታ ፖለቲከኞቹ እንደ ስጋት ማየታቸው ለድጋፋቸው ምክነያት እንደሆኑ ተንታኞች ያስረዳሉ።

“ፕሬዚዳንቱ በፉክክሩ እንደሚቀጥሉ በግልጽ ተናግረዋል፤ እናም በርካቶች ይህንን እያከበሩ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉም የዲሞክራት ፓርቲ ስትራቴጂ ባለሙያ የሆኑት ሲሞን ሮዘንበርግ ይናገራሉ።

“በፖለቲካ ሥርዓታችን ውስጥ ዘግይቶ ዕጩ ፕሬዚዳንትን መተካት ፈታኝ እና ከዚህ በፊት ተደርጎ የማይታወቅ ስለሆነ ይህንን ለውጥ ለማድረግ ትልቅ ክፍተት አለ” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን

የስትራቴጂ ባለሙያው ቀጣዩ ዕጩ ማን ሊሆን ይገባል? በሚለው “ጤናማ ውይይት” እንደተካሄደም አክለዋል።

ሆኖም የስፓኒሽ ዝርያ ያላቸው የ40 ምክር ቤት አባላትን የያዘው እንዲሁም 60 ጥቁር የምክር ቤት አባላት ያሉት ካውከስን ጨምሮ በርካቶች ባይደን እንዲሆኑ መወሰናቸውን ይናገራሉ።

የቀድሞ የኦባማ የምርጫ ዘመቻ አማካሪ አሜሺያ ክሮስ እንደሚሉት ጥቁር የምክር ቤቱ አባላት እንዲሁም በርካታ ጥቁር መራጮች ባይደንን ከተቀናቃኛቸው ትራምፕ በተሻለ ለሲቪል መብቶች የሚታገሉ ፕሬዚዳንት አድርገው እንደሚያዩዋቸው ተናግረዋል።

ባይደን ከኒው ዮርክ ተወካይዋ አሌክሳንዲሪያ አካሲዮ ኮርቴዝ እና የቬርሞንት ሴናተር በርኒ ሳንደርስን ጨምሮ በርካታ የግራ ዘመም ፖለቲከኞችን ድጋፋቸውን እየሰጧቸው ይገኛሉ። እነዚህ ፖለቲከኞች ቀደም ሲል ባይደን በአንዳንድ ፖሊሲያቸው “ጽኑ አቋም የላቸውም” በማለት ሲተቿቸው ነበር።

ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በሲቪል እና በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መብቶች እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚደቅኑትን ስጋት በርካቶች እንደሚገነዘቡም ነው አሜሺያ የሚያስረዱት።

እስካሁን ድረስ ለባይደን ድጋፋቸውን እየሰጡ ያሉት የዲሞክራቶች ጠንካራ የድጋፍ መሠረት ናቸው በሚባሉ አካባቢዎች የሚወዳደሩ ፖለቲከኞች ናቸው።

ሆኖም ባይደን በዕጩነታቸው ቢቀጥሉ መመረጣቸውን አደጋ ውስጥ ይከተዋል በሚባሉ አካባቢዎች የሚወዳደሩ ፖለቲከኞች ያደረባቸውን ስጋት ዋይት ሐውስ ችላ ሊለው እንዳይማይገባ እና መፍትሄም ማበጅት እንደሚየስፈልገው አሜሺያ ያስረዳሉ።

ባይደን ከምርጫ ፉክክሩ ራሳቸውን እንዲያገሉ ጫናዎች በበረቱበት ወቅት የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየት መለኪያዎች የበርካታ መራጮቻቸውን ድጋፍ እንዳላጡ የሚጠቁሙ ይመስላሉ ተብሏል።

ዋሽንግተን ፖስት፣ ኤቢሲ ኒውስ እና ኢፕሶስ ባይደን እና ትራምፕ ካደረጉት የምርጫ ክርክር በኋላም ቢሆን ትንቅንቅ ላይ እንዳሉ በዚህ ሳምንት ያተሙትን የዳሰሳ ጥናት በመጥቀስ የባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን ተከራክሯል።

የዳሰሳ ጥናቱ ከምርጫው ክርክር በፊት ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያሳየ ነው።

ነገር ግን ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት አሜሪካውያን ባይደን ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ እንደሚፈልጉ በቅርቡ የተደረገ የሕዝብ አስተያየት መለኪያው ጠቁሟል።

ፕሬዚዳንቱ በሆሊውድ ልሂቃን መካከልም ያላቸውን ድጋፍ እያጡ ነው።

ታዋቂዋ ተዋናይት አሽሊ ጁድ ፓርቲው “ጠንካራ” ዕጩ ያስፈልገዋል በማለት ባይደን ከምርጫ ፉክክሩ እንዲወጡ ጠይቃለች።

ከእሷ በፊትም ታዋቂው ጆርጅ ክሉኒ እንዲሁ ጠንከር ባለ መልዕክቱ ባይደን ከምርጫ ፉክክሩ ይውጡ ብሏል።

ለረዥም ጊዜ ዲሞክራቶችን በገንዘብ በመለገስ የሚታወቁት ዊትኒ ትልሰንም ባይደን ከምርጫ ፉክክሩ እንደሚወጡ ከፍተኛ መተማመን እንደነበራቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሌሎች የዲሞክራቲክ ፓርቲ ለጋሾችም እንዲሁ “ፊውቸር ፎርዋርድ” ለተሰኘው የባይደን ገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ቡድን ሊሰጡት ቃል ገብተው የነበረውን 90 ሚሊዮን ዶላርን ባይደን እስኪወጡ ድረስ እንደማይለቁ ኒው ዮርክ ታይምስ በዘገባው አስነብቧል።

ሆኖም ሌሎች ከፍተኛ ለጋሾች ባይደንን ከጎንዎት ነን እያሏቸው ነው።

ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ለዲሞክራቶች የገቢ ማሰባሰቢያዎችን በማዘጋጀት የሚታወቁት ሽካር ናራሲምሃን በዕቅዳቸው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ የለም ሲሉ ተናግረዋል።

“ዐይናችን እየሆነ ያለውን ነገር መመልከት ይችላል። ጆሯችንም የሚወራውን ማድመጥ ይችላል። ነገር ግን አንገታችንን ደፍተን ሥራችንን እየሠራን ነው” ሲሉ ሽካር አስረድተዋል።

“በምርጫው ፉክክር መቀጠል ወይም ራሱን ማግለል፤ ውሳኔው የፕሬዚዳንቱ ነው። የሚወስነውን ሁሉ እንቀበላለን። ሆኖም ይህ ውይይት በቅርቡ መቋጫ ሊያገኝ ይገባዋል” ሲሉ የተናገሩት ሽካር ለባይደን ያላቸው ድጋፍ እንደሚያሸንፉ ከማመን የመነጨ ነው ብለዋል።

“የዚህ ምርጫ ወሳኞቹ ሦስት ግዛቶች ሚቺጋን፣ ፔንሲልቪኒያ እና ዊስኮንሲን በአጠቃላይ ከ50 ሺህ የማይበልጥ ድምጽ ነው። በእነዚህ ግዛቶች ለማሸነፍ መሠረታዊ ሥራዎችን አከናውነናል” ሲሉም ሽካር ተደምጠዋል።

የብሔራዊ ፋይናንስ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፍራንክ አስላም በበኩላቸው በቅርቡ በሜሪላንድ በሚገኘው ቤታቸው ለባይደን የገቢ ማሰባሲያ እንዳቀዱ ተናግረዋል። “ባይደን እንደሚያሸንፉ ስለማውቅ ነው ይህንን የገቢ ማሰባሰቢያ የማደርገው” ብለዋል።