ሻምሳ ሻራዌ
የምስሉ መግለጫ,ሻምሳ ሻራዌ

ከ 5 ሰአት በፊት

“በድጋሚ በስለት የመቆረጥ ሃሳብ በጣም አስፈርቶኝ ነበር። ግን አሁን ላይ በራሴ ፍላጎት በመሆኑ ለአእምሮ ጤናዬ ስል ማድረግ እንዳለብኝ ወሰንኩ” የምትለው ሻምሳ ሻራዌ ነች።

ሻምሳ ከ25 ዓመታት በፊት ገና ልጅ ሳለች ከፍላጎቷ ውጪ ግርዛት ተፈጽሞባት ነበር።

የ6 ዓመት ልጅ ሳለች የተፈጸመባት ግርዛት አብዛኛውን የመራቢያ የሰውነቷን አክፍል ቆርጦ ያስወገደ ነው።

ሻምሳ አባል የሆነችበት የሶማሊ ማኅብረሰብ የሴት ልጅ ግርዛትን [በስፋት የሴት ልጅ ብልት መተልተል በማባል ይታወቃል] በስፋት ይፈጽማል።

በቅርቡ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከሆነ በመላው ዓለም ከ230 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የተለያየ ደረጃ ያለው ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል።

በአፍሪካ ደግሞ ቁጥሩ ያይላል። እንደ ዩኒሴፍ ከሆነ 140 ሚሊዮን የሚሆኑት በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ሴቶች መገኛ አፍሪካ ናት።

የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ ያለው ወደ 30 በሚጠጉ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሲሆን፤ በእስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ አገራት ውስጥም የሴት ልጅ ግርዛት ይፈጸማል።

ሶማሊያ፣ ጊኒ እና ጂቡቲ ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ በሦስቱ አገራት የሚገኙ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንዲህ ያለው ከባድ የግርዛት ዓይነት ይፈጸምባቸዋል።

ግርዛት በሚፈጸምባቸው በተለይ እንደ ሶማሊያ ባሉ አገራት ውስጥ ድርጊቱ የሴት ልጅን ድንግልና ያረጋግጣል የሚል እምነት አለ። በሶማሊ ማኅብረሰብ ውስጥ ሴት ልጅን ማስገረዝ የቤተሰብ ክብርን ከማስጠበቅ ጋር ይቆራኛል።

በዚህ ማኅብረሰብ ውስጥ ያልተገረዙ ሴቶች “ያነሰ ሞራል ወይም ለጾታዊ ግንኙነት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው” ተደርገው ይወሰዳሉ። እነዚህ በሃሪያት ደግሞ የቤተሰብን ክብር የሚያቀሉ ተደርገው ይወሰዳሉ።

ሻምሳ በግርዛቱ ምክንያት የወረ አበባዋ በመጣ ቁጥር ከፍተኛ ህመም እንደሚሰማት ትገልጻለች።

“ስቃይ ይበቃኛል” ትላለች የ30 ዓመት ወጣቷ ሻምሳ።

የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሃገራት

በአውሮፓውያኑ 2023 ማብቂያ ላይ ሻምሳ ህመሟን በቀዶ ሕክምና ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያላትን አማራጭ ማጤን ጀመረች።

ነዋሪነቷን በዩናይትድ ኪንደግም (ዩኬ) ያደረገችው ሻምሳ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም አጥብቃ ትጠይቃለች።

“እኔ ስላደረኩት ቀዶ ሕክምና እንኳን ብዙ መረጃ የለም። ይህን ለማድረግ የወሰንኩትም ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ነው” ትላለች።

በግርዛት ምክንያት የተበላሸ የመራቢያ አካልን መልሶ የመጠገን ቀዶ ሕክምና ለውበት ወይም ለቀንጦት ተብሎ የሚሠራ ሳይሆን የሴት ልጅ ብልት መሠረታዊ ሥራውን እንዲያከናውን ለማድረግ ነው።

ቀዶ ሕክምናው በግርዛት የመጣን ህመም ያስወግዳል፤ እንዲሁም የሴት ልጅ የወሲብ ሕይወትን እንደሚያሻሽል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአንዳንድ ቀዶ ሕክምናዎችም በግርዛት ምክንያት የጠበበ ብልት ወደ ተፈጥሯዊ መጠኑ እንዲመለስ ይደረጋል።

ሻምሳ ብዙ ጥናት ካደረገች በኋላ በተሻለ ደረጃ ቀዶ ሕክምናውን ማድረግ የምትችለው በጀርመን አገር እንደሆነ ወሰነች። ለሕክምና የሚያስፈልገውን ገንዘብ በመዋጮ 31 ሺህ ዶላር ማሰባሰብ ቻለች።

ሻምሳ በአጠቃላይ 37 ሺህ ዶላር ወጪ አድርጋ እና ከ4 ሺህ ዶላር በላይ ዕዳ ውስጥ ገብታ ቀዶ ሕክምናውን አደርጋ ከጀርመን ተመልሳለች።

“ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ዶክተር ለማግኘት ተመልሼ መሄድ ነበረብኝ። ነገር ግን ገንዘብ ስለሌለኝ ዳግም ወደ ጀርመን አልተጓዝኩም” ትላለች።

“እኔ በራሴ ላይ ላልፈጠርኩት ጉዳት ገንዘብ መክፈል አግባብ አይደለም” ትላለች።

የግርዛት ዓይነቶች እንደየ ባሕሉ የተለያዩ ናቸው። የመጀመሪያው ዓይነት ክሊቶሪዲክቶሚይ (Clitoridectomy) ይባላል። ይህ ቂንጥር የሚባለውን የብልት ክፍል እና በአከባቢው የሚገኝን ስስ አካል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።

ፕላስቲክ ሰርጀሪ ሲከናወን
የምስሉ መግለጫ,ፕላስቲክ ሰርጀሪ ሲከናወን

ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ ኤክሲሺን (Excision) የሚባል ሲሆን፤ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልትን የውስጠኛውን ከንፈርን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የሚያስወግድ ግርዛት ነው።

ሦስተኛ ዓይነት የሚባለው ሳይንሳዊ መጠሪያው ኢንፊቢዩሊሽን (Infibulation) ይባላል።

ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልት ከንፈሮችን ቆርጦ አውጥቶ ብልትን በመስፋት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምቹ እንዳይሆን ማጥበብ ማለት ነው። ይህ ተግባር የሚያስከትለው ህመም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል።

አራተኛው ዓይነት ደግሞ እጅግ የከፋው ነው። ይህ ዓይነቱ ሁሉንም የብልት አካላት በመቁረጥ የቀረውን ስስ አካል መስፋትን ይጨምራል።

ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት በምዕራቡ ዓለም ያሉ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በግርዛት የተጎዱ የሴቶችን የመራቢያ አካላትን መልሶ ለመጠገን ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እንደ ቤልጂየም፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ፊንላንድ እና ስዊትዘርላንድ ባሉ አገራት በመንግሥት ወጪ በግርዛት የተጎዳን የሴትን የመራቢያ አካል ማስተካከል ይቻላል።

በግርዛት ብዙ ጉዳት የገጠሟቸው የበርካታ ሴቶች መገኛ በሆነችው አፍሪካ ግን ይህን ዕድል ማግኘት ቀላል አይደለም።

በአፍሪካ በኬንያ እና ግብፅ ብቻ ነው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚቻለው። ለዚህም ከፍተኛ ገንዘብ ከኪሳቸው አውጥተው መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ካርታ

በግርዛት ከደረሰባት ጉዳት በርካታ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናዎችን ካደረጉት መካከል ሃጃ ቢልኪሱ ትገኝበታለች።

ሃጃ ጀርመናዊ ብትሆንም ትውልዷ ሴራሊዮን ነው። ሃጃ እአአ 2002 ወደ ምዕራባዊቷ አፍሪካዊት አገር ከተወሰደች በኋላ ነበር የተገረዘችው።

ሃጃ ሴቶች ጥናቶችን አድርገው ቀዶ ሕክምናውን እንዲያደርጉ ታበረታታለች። “የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና የምናደርገው በግርዛት የተበላሸ አካላችንን ለማስተካከል ብቻ አይደለም” ትላለች።

“የተገረዙ አብዛኞቹ ሴቶች ጠባሳ አላቸው። እነዚህን ጠባሳዎች እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል እና አካላችን መሳሳብ እንዲችል ማድረግ ይቻል እንደሆነ ከዶክተር ጋር መነጋገር ያስፈልጋል” ትላለች።

ሃጃ ግርዛት ወሲብ መፈጽም ብቻ ሳይሆን ልጅ መውለድን ጭምር እንደሚያከብደው ትገልጻለች።

ዶ/ር ሬሃም አዋድ በግብፅ በግርዛት የተጎዳን የሴትን የመራቢያ አካል ለመጠገን በተቋቋመ ክሊኒክ ውስጥ ሐኪም ናቸው።

ሐኪሟ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በሴቷ ሕይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸው፤ አንዳንዴ ግን በግርዛት በሚደርስ ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ምንም ለውጥ ማምጣት አይቻልም ይላሉ።

“ለሁሉም የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ምላሽ ይሰጣል ብዬ አላስብም” ይላሉ። እርሳቸው አንደሚሉት ከቀዶ ሕክምና ውጪ ወደ ሴት ብልት ደም የሚሄድበትን ሁኔታ በመፍጠር ሕክምና እንደሚሰጥ ይናገራሉ።

ሃጃ ቢለኪሱ
የምስሉ መግለጫ,ሃጃ ከጀርመን ወደ ሲዬራ ሊዮን እአአ 2002 ላይ ከተወሰደች በኋላ ነበር የተገረዘችው

አዲስ አካል

በከባድ ግርዛት ምክንያት የተጎዳ አካላቸውበቀዶ ሕክምና ከተስተካለ በኋላ ሴቶች እስኪላመዱት ድረስ ጊዜ ይወስድባቸዋል።

“ለመጀመሪያ ጊዜ ብልቴን ስመለከት በጣም ነበር የተደናገጥኩት። የእኔ አካል አልመስልሽ ብሎኝም በጣም ተቸግሬ ነበር” ትላለሽ ሻምሳ።

“የተገረዝኩት ገና የ8 ዓመት ታዳጊ ሳለሁ ስለነበረ ይህን አካል ጨርሶ አላስታውሰውም።”

አሁን ላይ ከቀዶ ሕክምናዋ እያገገመች ያለችው ሻምሳ “ካገገምኩ በኋላ ከአዲሱ አካሌ ጋር እንዴት መኖር እንዳለብኝ መላመድ ይኖርብኛል”

አሁን ላይ ግን ሙሉ የሴትነት እና ሙሉ ክብር ስሜት እንደሚሰማት ትናገራለች።

ይህንን በሴቶች ጤና እና አጠቃላይ ሕይወት ላይ ከባድ ተጽእኖ ያለውን አሰቃቂ የሴቶች ግርዛትን ለማስቆም አንዳንድ አገራት በሕግ ጭምር ክልከላ ቢያደርጉም፤ የባሕላቸው እና የእምነታቸው አንድ አካል አድርገው የሚመለከቱ ማኅበረሰቦች ድርጊቱን መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

በዚህም ሳቢያ በርካታ ሴቶች ከባድ የጤና ችግር ከመጋፈጣቸው በተጨማሪ በወሊድ ጊዜ እስከሞት የሚያደርስ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።