ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራ ከተፈጸመባቸው በኋላ

ከ 5 ሰአት በፊት

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ በጥይት ተመትተው የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው።

ትራምፕ በአሜሪካዋ ፔንስልቬኒያ ግዛት ከደጋፊዎቻቸው ፊት ቆመው ንግግር እያደረጉ ሳለ በርካታ ጥይቶች ወደ እርሳቸው የተተኮሱ ሲሆን፤ በቀኝ በኩል ያለው ጆሯቸው በጥይት ተመትቷል።

ተደጋጋሚ የተኩስ ድምጾቹ እንደተሰሙ የአሜሪካ መንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ለመከላከል በፍጥነት ወደ መድረክ በመውጣት ዝቅ አድርገዋቸው ከሚተኮሰው ጥይት መጠበቅ ችለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዝቅ ካሉበት ሲነሱ ፊታቸው እና ቀኝ ጆሯቸው በደም ተሸፍኖ የታየ ሲሆን፤ የግድያ ሙከራው ከተፈጸመባቸው ስፍራ ወደተዘጋጀላቸው መኪና ሲወሰዱ ቀኝ እጃቸውን በማንሳት መልዕክት አስተላልፈዋል። ደጋፊዎቻቸውም “ዩ ኤስ ኤ! ዩ ኤስ ኤ! ዩ ኤስ ኤ!” ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የጆሯቸው የላይኛው ክፍል በጥይት መመታቱን ተናግረዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት በአካባቢው ባለ ሆስፒታል የሕክምና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸው፤ “ጥይት ቆዳዬን በስቶ ሲገባ ተሰማኝ። በጣም ብዙ ደም ፈሶኛል። ምን እየተፈጸመ እንደሆነ ግራ ገብቶኝ ነበር” ብለዋል።

የግድያ ሙከራውን የፈጸመው ግለሰብ በአሜሪካ ሴክሬት ሰርቪስ [ደኅንነት] አባላት መገደሉን የተቋሙ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ከተጠርጣሪው በተጨማሪ ሁለት ሰዎች በተኩስ ልውውጡ መገደላቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ መቁሰላቸው ተገልጿል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ጥቃት ፈጸሚው ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ስፍራ ከሚያደርጉበት በመቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ሆኖ መተኮሱን ተናግረዋል።

ማንነቱን የሚለይ ሠነድ ያልያዘውን ግለሰብ ለመለየት ፖሊስ የዘረ መል ናሙና (ዲኔንኤ) መውሰዱ ተገልጿል።

ኤፍቢአይ ምርመራ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ ኤጀንሲው ትራምፕ ላይ የተፈጸውን ድርጊት የግድያ ሙከራ አድርጎ እንደሚመለከተው ገልጿል።

ሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራው የተፈጸመባቸው በትለር በተባለችው የፔንሰልቪኒያ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳቸውን እንደጀመሩ ነበር።

ትራምፕ ስለ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን አስተዳደር መናገር እንደጀመሩ ነበር በርካታ ጥይቶች የተተኮሱባቸው።

አንድ የዐይን እማኝ ትራምፕ ንግግር ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ከጀርባቸው ባለ ሕንጻ አንደኛ ፎቅ ላይ አጎንብሶ ሲድህ የነበረ አጠራጣሪ ሰው መመልከቱን ለቢቢሲ ተናግሯል። ይህ ግሬግ የተባለ የዐይን እማኝ አጠራጣሪውን ሰው ለፖሊስ የጠቆመው እርሱ ስለመሆኑም ተናግሯል።

የዓይን እማኙ ግሬግ
የምስሉ መግለጫ,የዓይን እማኙ ግሬግ

“ጦር መሳሪያ ይዟል። መሳሪያ እንደያዘ በግልጽ ማየት ይቻላል። ወደ እርሱ እየጠቆምን ለፖሊስ አባላት ‘ያ ሰው መሳሪያ ይዟል’ እያልን እየነገርናቸው ነበር። ፖሊስ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ግራ ተጋብቶ ነበር” ብሏል።

ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባስተላለፉት መልዕክት “ይህ በአሜሪካ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው” ሲሉ የግድያ ሙከራውን አጥብቀው አውግዘዋል።

“ሁሉም ሰው ሊያወግዘው ይገባል” ብለዋል ባይደን።

ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ፕሬዝዳንት ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር መነጋገራቸው አስታውቋል።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም እንዲሁ “በዴሞክራሲያችን ውስጥ ፖለቲካዊ ፍላጎትን በኃይል ማሳካት ጨርሶ ቦታ የለውም” ብለዋል።

ትራምፕ በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ማወቃቸው ትልቅ እረፍት እንደሰጣቸው ኦባማ ተናግረዋል።

በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ማይክ ፔንስም እንዲሁ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ለትራምፕ ጸሎት እያደረጉ እንደሚገኙ እንዲሁም ሁሉም አሜሪካዊ ትራምፕን በጸሎት እንዲያስባቸው ጠይቀዋል።

ከወጭ አገራት ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚኦ ኪሺዳ እንዲሁ ጥቃቱን ካወገዙ መሪዎች መካከል ይገኙበታል።