የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኃላፊዎች መግለጫቸውን በሰጡበት ወቅት

ዜና በአዋጅ ከተደነገገ ከ18 ዓመታት በኋላ ከ175 ሺሕ በላይ የመንግሥት ኃላፊዎች ሀብታቸውን ማስመዝገባቸው…

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: July 14, 2024

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ የሕዝብና መንግሥት ሀብት ላይ ውሳኔ የሚያሳልፉ፣ እንዲሁም በሕዝብና በመንግሥት ገንዘብ ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያላቸው 175,627 የመንግሥት አመራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች ሀብት የማስመዝገብ አዋጅ ለመጀመርያ ጊዜ በሕግ ከተደነገገ ከ18 ዓመታት በኋላ ሀብታቸውን ማስመዝገባቸውን አስታወቀ፡፡

አዋጁ በ2005 ዓ.ም. እና በመጨረሻም በአዋጅ ቁጥር 881/2007 በ2007 ዓ.ም. መሻሻሉ ይታወሳል፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን የገለጸው በአስቸኳይ ሙስና መከላከል፣ በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ፣ እንዲሁም በሙስና መከላከል ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ዓርብ ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲሰጥ ነው፡፡

የኮሚሽኑ የሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን በላይነህ እንደገለጹት፣ በ2016 በጀት ዓመት ሀብታቸውን ማስመዝገብ አለባቸው ተብለው በትኩረት ከተለዩት ውስጥ ሁሉም አመራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎቸ ሀብታቸውን አስመዝግበዋል፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 6,565 የሙስና ወንጀል ጥቆማ ለኮሚሽኑ የደረሰ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥም 2,123 ለተጨማሪ ምርመራ ለፍትሕ አካላት የተላከ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ 1,209 ጥቆማዎች በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራዎች የተሠራባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 215 ጥቆማዎች ተጨማሪ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ለኮሚሽኑ ጥቆማ ከደረሱ የሙስና ወንጀሎች ውስጥ 3,208 የሚሆኑት ጥቆማዎች ላይ የምክር አገልግሎት የተሰጠባቸው መሆኑን፣ በአጠቃላይ 6,565 ጥቆማ ለኮሚሽኑ የደረሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሀብት ያስመዘገቡ አመራሮች ላይ ማጣራት ተደርጎ እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ዘንድሮ በፌዴራል ደረጃ 113 አመራሮች ላይ የሀብት ማጣራት ሥራ እንደተካሄደ ገልጸው፣ በእነዚህ አመራሮች ላይ የተደረገው ማጣራት ግኝት ምን ይመስላል? ምን ያህሎቹ ወደ ፍትሕ አካላት ተልከዋል? የሚለውን በቀጣይ ኮሚሽኑ ያሳውቃል ብለዋል፡፡

በሕዝብ ሀብት ላይ ውሳኔ የሚያሳልፉ አካላት የመንግሥትን ሥራ ከመሥራት ውጪ ጥቅምን የሚያስገኝ ነገር ላይ መሰማራት እንደሌለባቸው ገልጸው፣ ይህንን በተመለከተ አገር አቀፍ የጥቅም ግጭት መከላከልና የሥነ ምግባር ደንብ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን አብራርተዋል፡፡

የሀብት ምዝገባ በቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማከናወን ከዚህ ቀደም ከህንድ ኩባንያ የተዘጋጀው የቴክኖሎጂ ሲስተም ተዘርግቶ እንደነበር፣ ይህም በተወሰነ ደረጃ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የደኅንነት ጉዳይ እንደተነሳበት፣ በአሁኑ ወቅት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)ቴክኖሎጂውን እያበለፀገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለሀብት ምዝገባ አገልግሎት እንዲውል የተዘጋጀው የቴክኖሎጂ ሲስተም ቢቆምም የሀብት ምዝገባው እንደማይቆም የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን እንዲያስፈጽም በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣን በመሆኑ ምዝገባውን በሰነድ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በአገር ደረጃ ማንኛውም ተመራጭ፣ ተሿሚ፣ እንዲሁም ሠራተኛ ሀብታቸውን ማስመዝገብ እንደሚኖርባቸውና በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገብ እንዳለባቸው የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

በ2016 በጀት ዓመት በፌዴራል ዘርፎች በተሠራ 102 የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ ላይ በዋናነት ከ687,584,666 በላይ ብርና 8,490 ዶላር የሕዝብና የመንግሥት ሀብትና ንብረት ማዳን መቻሉን፣ የኮሚሽኑ የአስቸኳይ ሙስናን የመከላከል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገዛኸኝ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሥነ ምግባር የፀረ ሙስና ኮሚሽኖቹ በተሠራው 985 የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ከ2,127,651 በላይ ብር፣ እንዲሁም 46,457 በላይ ካሬ ሜትር የከተማና የገጠር መሬት በሙስና ሊጭበረበር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘርፎች፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች በተሠራ 1,087 የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ በዋናነት 2,810,235 በላይ ብርና 8,490 ዶላር፣ እንዲሁም መጠኑ 46,467,393 ካሬ ሜትር የሆነ የከተማና የገጠር ቦታ በሙስና ሊጭበረበር እንደነበር አክለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የንዑስ ፕሮግራሙን አፈጻጸም የተሻለ ለማድረግ በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ጥናትና ክትትል ዙሪያ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ፣ የ14 ክልሎችና ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባር የፀረ ሙስና ኮሚሽኖችን ያቀፈ የቴክኒክ ኮሚቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡