የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ ላይ የተገኙ ተወካዮች

ዜና የትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ውክልና እንዲሰጠው ሕወሓት ጠየቀ

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: July 14, 2024

የትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ቀጥተኛ ውክልና እንዲኖረው ሕወሓት እንደጠየቀና ይህንንም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቀጣይ በሚደረግ የፖለቲካ ውይይት ለመፈጸም ስምምነት መደረሱ ተሰማ። 

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ፣ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ሲካሄድ፣ በሕወሓት በኩል ከቀረቡ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ የትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ቀጥተኛ ውክልና እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ይገኝበታል። 

ሕወሓት ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም፣ የትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ቀጥተኛ ውክልና እንዲኖረው መጠየቁን አስታውቋል። 

ከዚህ ጥያቄ በተጨማሪ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆችና የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲፈቱ፣ እንዲሁም የተሰረዘው የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል።

በሌላ በኩል በጦርነቱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን በተሟላ ሁኔታ መመለስ፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ማድረግ፣ የትግራይ ሠራዊትን ትጥቅ ማስፈታትና ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ስደተኞችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው የሚሉት በውይይቱ ወቅት ትኩረት የተደረጉባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የሕወሓት መግለጫ ያመለክታል

እነዚህን ጉዳዮችም በቀጣይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በሚካሄድ የፖለቲካ ውይይት ለመፈጸም ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል። 

የሚቀጥለው የአፈጻጸም ግምገማ በመጪው ኅዳር 2017 ዓ.ም. እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱንም ሕወሓት በመግለጫው አስታውቋል።

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተካሄደው ግምገማ በሕወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምነት ያሳካቸው ተግባራትን ለመገምገምና የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ እንዲሁም በዘላቂነት የትግበራውን ስኬታማነት ለማረጋገጥ ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ያለመ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

በዚህ ግምገማ ላይ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የተፈራረሙት የሕወሓትና የፌደራል መንግሥት ተወካዮች፣ እንዲሁም የስምምነቱ ታዛቢዎች የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ተሳትፈዋል።

የስምምነቱ ታዛቢዎች ከሆኑት አንዱ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር ሐሙስ ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ መቀሌ በመጓዝ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን፣ ሁለቱም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ባሠፈሩት መልዕክት ከአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር ጋር በመቀሌ ተገናኝተው ስለትግራይ፣ ኢትዮጵያና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የትግራይ ክልል በፌዴራል አደረጃጀት ውስጥ ቀጥተኛ ውክልና የሌለው በመሆኑ የሚፈጥረው ክፍተት ሊጤን እንደሚገባ፣ ለአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዌበር እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ቀጥተኛ ውክልና እንዲያገኝ ቢደረግ በትግራይም ሆነ በሌሎች በጦርነት የተጎዱ ክልሎች የታቀደውን የመልሶ ግንባታ፣ የመልሶ ማቋቋምና የማገገሚያ ፕሮጀክቶች ለማገዝ እንደሚያስችለው እንዳስረዷቸውም ተናግረዋል። 

የአፍሪካ ኅብረት የተካሄደውን ግምገማ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የፌደራል መንግሥትና ሕወሓት በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ፣ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ መበተንና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመወያየት በአተገባበሩ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል እንደታየ ዕውቅና ሰጥተው፣ ቀሪ ጉዳዮችን ደረጃ በደረጃ ለመፈጸም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቋል።