የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት

ዜና ላለፉት 30 ዓመታት የጉዞ ዕግድ የተጣለባቸው አሥር ሺሕ ግለሰቦች ነፃ ተደረጉ

ፅዮን ታደሰ

ቀን: July 14, 2024

ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር በተደረገ ማጣራት ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ የጉዞ ዕግድ የተጣለባቸው አሥር ሺሕ ግለሰቦች ነፃ መደረጋቸውን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርቱን ሲያቀርብ እንደገለጸው፣ ከዚህ በፊት አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አደጋ ያስከትላሉ ተብለው የታገዱ ግለሰቦች በተደረገ ማጣራት ነፃ እንዲሆኑ መደረጋቸውን፣ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት አስታውቀዋል፡፡

በተቋሙ በተደረገ የለውጥ ሥራ ከዚህ ቀደም ዕግድ የተጣለባቸውን ግለሰቦች በሚመለከት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በተደረገ ማጣራት፣ ‹‹እነዚህ ግለሰቦች ይህን ያህል አደጋ ሊያስከትሉ አይችሉም በሚል ነው ከዕግዱ ነፃ የተደረጉት፤›› በማለት ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ፣ ከፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ እስኪገኝ ድረስ፣ በብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ሰዎች ከአገር እየወጡ ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ በሚኖርበት ወቅት፣ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ማንኛውም ሰው ከአገር እንዳይወጣ ሊያደርግ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

አዋጁን አስመልክቶ ማብራሪያቸውን የሰጡት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ከአዋጁ በፊትም አገልግሎቱ በአገር ላይ አደጋ ያመጣሉ የተባሉ ግለሰቦችን ያግድ እንደነበር ገልጸው፣ በዋና ዳይሬክተሩ ከአገር እንዳይወጣ ይደረጋል ተብሎ ስለተደነገገውም፣ ‹‹ጉዳዩ ሁሉም ኃላፊ ዘንድ እየቀረበ ያላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል ለመከላከል ነው፤›› ብለዋል፡፡

የተቋሙ ኃላፊዎች ወደ አመራርነት ሲመጡ ከነበረው ውዝፍ ሥራ አኳያ የተቋሙ ሠራተኞች ከመደበኛ የሥራ ሰዓት በተጨማሪ መሥራት ይገባቸው ነበር ያሉት ወ/ሮ ሰላማዊት፣ ይህን ለማድረግም ሠራተኞች ተጨማሪ ክፍያ ሊከፈላቸው ይገባ እንደነበርና ለዚህ የሚሆን በቂ ገንዘብ ባለመኖሩም ከቅጣት የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለክፍያ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በቅጣት ይሰበሰብ የነበረው ገንዘብ በግለሰቦች አካውንት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል ተብሎ የተሠራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን፣ ገንዘቡ ይሰበሰብ የነበረው ተቋሙ ከተቋቋመ ጀምሮ በነበረ የሠራተኞች ማኅበር አካውንት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር መመርያ ተዘጋጅቶለት ሲሠራበት ነበር ብለዋል፡፡ 

ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት 14.7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ውስጥ 148 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በቀን ሁለት ሺሕ ፓስፖርቶች ይታተሙ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ 14 ሺሕ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ በበኩላቸው፣ 820 ሺሕ ለሚሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ቪዛ መሰጠቱን ገልጸው፣ ከ51 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደግሞ መታወቂያ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡ 

አክለውም 10‚400 ያህል በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡና የመኖሪያ ፈቃድ ጊዜያቸው ያለፈ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ፣ አንዳንዶች በሕጋዊነት እንዲመዘገቡ መደረጉንና 18 ሺሕ በሚሆኑት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

የቱሪስትና የኮንፈረንስ ቪዛ ክፍያዎች ላይ ቅናሽ የሚያደርግ የአገልግሎቶች የዋጋ ማሻሻያ ከመጪው ነሐሴ ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም አቶ ጎሳ ተናግረዋል፡፡ 

በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ቢቂላ መዝገቡ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት 78 በመቶ በሚሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የምዝገባ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

በ2017 በጀት ዓመት ተቋሙ ሊያከናውናቸው በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከልም የቤት ለቤት የፓስፖርት አገልግሎት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ አገልግሎት የሚጀመረውም ከአንዳንድ ባለሀብቶችና ታዋቂ ሰዎች በቀረበ ጥያቄ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ቢቂላ፣ በተቋሙ ለአገልግሎቱ የሚቀመጠውን ክፍያ መክፈል የቻለ ማንኛውም ግለሰብ ቤቱ ድረስ ፓስፖርቱ እንደሚላክለት አክለዋል፡፡