ዜና በወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉዳይ የአዲስ አበባና የሲዳማን ፖሊስ ኮሚሽኖች መግባባት እንዳልቻሉ ተገለጸ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: July 14, 2024

በቀድሞ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በ870 ሔክታር ቦታ ላይ የከሰል ማዕድን ከማልማት ጋር በተያያዘ፣ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የሲዳማ ፖሊስ ኮሚሽን ሊግባቡ እንዳልቻሉ ተገለጸ፡፡

ውዝግብ የፈጠረው የከሰል ማዕድን ልማት ቦታ በጋሞ ዞን በረዳ ወረዳ ሀምቢስ ቀበሌ የሚገኝ ሲሆን፣ 870 ሔክታር መሬት ባለይዞታ የሆኑ ሦስት ግለሰቦች፣ የይዞታውን 62 በመቶ ድርሻ ለአንድ ባለሀብት በ20 ሚሊዮን ብር ተስማምተው ከሸጡና ቅድሚያ ክፍያ አምስት ሚሊዮን ብር ከተረከቡ በኋላ፣ ቦታውን ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መሆኑን ሪፖርተር የተመለከታቸው ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

ውዝግቡ በከሰል ማዕድን ልማቱ ላይ 62 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው እየገለጹ ባሉት ባለሀብት አቶ ተመስገን ታፈሰና 38 በመቶ ድርሻ ባላቸው አቶ አርጋው አየለ፣ አቶ ዓለምገና ዘርጋው፣ አቶ አማረ ዘውዴና ወ/ሮ ድምቀት ያሬድ መካከል መሆኑን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

የከሰል ማዕድን ልማቱ 38 በመቶ ድርሻ ባላቸው አራት ግለሰቦች በተቋቋመው ኦታና የማዕድን ቁፋሮና ኳሪዩንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን፣ የአዋጭነት ጥናት ሠርተው 8.7 ኪሎ ሜትር ወይም 870 ሔክታር ቦታ ላይ ማልማት እንዲችሉ ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ ስለቦታው አጠቃላይ ይዘት፣ ምድራዊ መገኛ ሥፍራ (Geographic Coordinate) በመግለጽ ለአቶ ተመስገን 62 በመቶውን ድርሻ በ20 ሚሊዮን ብር እንደሸጡላቸው የተፈፈረሙባቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ከፍተኛ ባለድርሻው አቶ ተመስገን በስምምነታቸው መሠረት የመጀመርያውን አምስት ሚሊዮን ብር ከከፈሉ በኋላ፣ ቀጣዩን 15 ሚሊዮን ብር በድርጅታቸው ኮሽልድ ትሬዲንግ ሥም የተመዘገበ ቼክ፣ የከሰል ማዕድኑን በማልማትና በመሸጥ ከሚገኝ ገቢ እንደሚከፍሉ አድርገው የሰጡ ቢሆንም፣ ሻጮች (38 በመቶ ድርሻ ያላቸው) ቼኩ በቂ ስንቅ (ገንዘብ) እንደሌለው አረጋግጠው እንዳስመቱበት ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡ ድርጊቱ የወንጀል ኃላፊነት ስለሚያስከትል፣ አቤቱታቸውን በወቅቱ ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በማቅረባቸው፣ መምርያው አቶ ተመስገንን እናታቸውን በውጭ አገር ለማሳከም ከአገር ሊወጡ ሲሉ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸውም ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ተመስገን በበኩላቸው የከሰል ማዕድን ልማት በጋራ ለማልማት 62 በመቶ ድርሻ ባለቤት እንደሚሆኑ ተስማምተው ግዢ የፈጸሙበት ቦታ የሌለና ከባድ የማታለል ወንጀል እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ፣ ከላይ በተጠቀሱት ግለሰቦች ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ክስ ማቅረባቸውንም ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡

ሰነዶቹ እንደሚያስረዱት አቶ ተመስገን በውሉ መሠረት ለሻጮች የመጀመሪያ ክፍያ አምስት ሚሊዮን ብር ውሉ በተፈረመ በሦስት ቀናት ውስጥ ገቢ እንደሚያደርጉ፣ እንዲሁም ቀሪውን 15 ሚሊዮን ብር በተመለከተ ለገዥ ዋስትና ይሆን ዘንድ፣ በገዥ ድርጅት ኮሽልድ ትሬዲንግ የተመዘገበ የአዋሽ ባንክ ቼክ፣ ሻጮች የሰጡትን የማዕድን ፈቃድ 870 ሔክታር ቦታ ከተረከቡ በኋላ፣ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ምርት ተመርቶ ከሚገኘው የሽያጭ ገቢ ላይ የሚመነዘር ሆኖ ቼኩን በዋስትና መስጠታቸውን ሰነዱ ይገልጻል።

በውሉ ዝርዝር በቀረበው መሠረትም፣ ሻጮች በሁለተኛ ዙር የተፈቀደላቸውን 870 ሔክታር የድንጋይ ከሰል ማዕድን አክሲዮን መሸጣቸውን ገልጸው፣ ለሽያጩ መሠረት የሆነውን ማዕድን የማልማት መብትን የሚያረጋግጡ ማናቸውም ሕጋዊ ሰነዶችን ለገዥ በሰባት ቀናት ውስጥ ማስረከብ፣ ማዕድን ለማምረት አስፈላጊውን የምርት ፈቃድ የማቅረብ ተግባር መፈጸም፣ ሕጋዊነትን በተመለከተ ሰነዶችን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ለገዥ ማቅረብ፣ እንዲሁም ገዥ ምርት በሚያመርትበት ሰዓት በጋራ በመሆን የአካባቢውን ሰላም እንዲጠበቅ ከመንግሥት አካል ጋር ሆኖ ለምርቱ መጨመር ተገቢውን ዕርዳታ ለማድረግ የገዥ ግዴታ መሆኑን መስማማታቸውንም ሰነዶቹ ይገልጻሉ።

ባለሀብቱ አቶ ተመስገን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ሻጮች ማስፋፊያ በሚል በውሉ ላይ የሠፈረውን በሥፍራው ተገኝቼ የተመለከትኩትን፣ አጠቃላይ 870 ሔክታር ቦታ ሊያስረክቡኝ አልቻሉም፤›› ብለዋል።

ከሻጮች አንዱ የሆኑት አቶ አርጋው በበኩላቸው፣ ‹‹ቦታውን መረከብ ብቻ ነው የቀረው፣ ፈቃድ የተቀበልንበት ሰነድ አለን፤›› ብለዋል፡፡

ሻጭና ገዥ፣ ፈቃድን በተመለከተ ያቀረቡትን ሰነዶች ሪፖርተር የተመለከተ ሲሆን፣ ሰነዶቹ ሁለት የተለያዩ ይዘቶች ያላቸው መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡

አቶ አርጋው ‹‹የማዕድን ማምረት ፈቃድ መሰጠቱን ስለማሳወቅ›› በሚል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ፣ የማዕድን ሀብት ጥናት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ገብረ ሥላሴ ተፈርሞ የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ተየወጣ ደብዳቤ፣ የመልክዓ ምድር መገኛ ሥፍራቸው ተለይቶ የተጠቀሰ በብሎክ አንድ አራት ቦታዎች በአጠቃላይ 11.44 ሔክታር፣ እንዲሁም ብሎክ ሁለት በተመሳሳይ አራት ቦታዎች በጥቅሉ 11.3 ሔክታር መሬት፣ ጠቅላላ ስፋቱ 22.74 ሔክታር በሆነ ቦታ ላይ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማምረት ፈቃድ እንደተሰጠው ይገልጻል።

በሌላ በኩል ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በዚሁ የክልሉ ኤጀንሲ ለኦታና የማዕድን ቁፋሮና ኳየሪንግ ድርጅት የተጻፈና ሪፖርተር የተመለከተው ሰነድ፣ የማዕድን ሥራ ፈቃድ ቦታ ማስተካከያ ጥያቄን በሚመለከት በተሰጠ የመልስ ደብዳቤ ላይ፣ ድርጅቱ የቦታ ማስተካከያ የጠየቀበት አብዛኛው ክፍል ከዚህ በፊት የምርመራ ሥራ ፈቃድ ወስዶ ጥናት ካካሄደበት ቦታ ውጪ የሆነና ለሌሎች አልሚዎች ፈቃድ የተሰጠበት በመሆኑ፣ ድርጅቱ ከጠየቀው ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የቀረው ቦታም ቢሆን የማምረት ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ፣ የማዕድን ማውጫ ቦታ ነፃ በመደረጉ ለሌሎች አልሚዎች ፈቃድ የተሰጠበት መሆኑን ኤጀንሲው ያረጋገጠ ስለሆነ፣ የቦታ ማስተካከያ ጥያቄውን ተቀብሎ ማስተናገድ እንዳልቻለ ያብራራል።

በሻጭና በገዥ መካከል ያለው አለመግባባትና የክፍያ ጥያቄ ጉዳይ ቀጥሎ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምርያ ‹‹የተፈጸመብን የወንጀል ድርጊት ተጣርቶ በአፋጣኝ ክስ እንዲመሠረትልን›› በሚል፣ በየግለሰቦቹ ስም ለየብቻ የተጻፈ የክስ ማመልከቻ አስገብተዋል።

ማመልከቻው ገዥ አቶ ተመስገን ታፈሰ ለድርጅታቸው 62 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ በውል ከተስማሙበት 20 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ አሥር ሚሊዮን ብር በተለያዩ ጊዜያት መክፈላቸውን ያስረዳል።

ሁለቱ አመልካቾች ለፖሊስ መምርያው ያስገቡት ማመልከቻ፣ አቶ ተመስገን በአክሲዮን ሽያጩ ወቅት ያለባቸውን ቀሪ ገንዘብ ለመክፈል በማሰብ ለሻጮች የሰጡት ቼክ ምንም ዓይነት ስንቅ የሌለው ወይም ደረቅ ቼክ መሆኑን ተከትሎ፣ ለፖሊስ መምርያው ክስ አቅርበው የነበረና ግለሰቡም በቦሌ ኤርፖርት በኩል ከአገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ ሲጣራ መቆየቱን ያስረዳል።

አቶ ተመስገን በበኩላቸው፣ ‹‹ከአገር ለመውጣት እየሞከርኩ አልነበረም፣ ሕመምተኛ እናቴን በሕክምና ቦርድ ወደ ውጭ አገር ሄዳ መታከም እንዳለባት በተረጋገጠ የሕክምና ጉዳይ ወደ አሜሪካ አገር ጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ወስጄ ለማሳከም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተገኘሁበት ታሰርኩ፤›› ብለዋል። የሰነድ ማስረጃውም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

ከሳሾች ለፖሊስ ካስገቡት ማመልከቻ በተጨማሪም የአቶ ተመስገን ጉዳዩ ሲጣራ መቆየቱን በመግለጽ፣ በመጨረሻም ተጠርጣሪው ግለሰብ ጉዳዩን በዕርቅ ለመጨረስና ያለባቸውን ዕዳ በአጭር ጊዜ ለመክፈል በመስማማት፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገርጂ ቅርንጫፍ ታኅሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀርቦ የሚመነዘር፣ ለከሳሽ አቶ ዓለምገናና አቶ ዘርጋው ወልደ ጨርቆስ ቁጥሩ 39111529፣ እንዲሁም ለከሳሽ አቶ አርጋው አየለ ሮማ ቁጥሩ 3911130 የሆነና እያንዳንዳቸው የአምስት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው፣ ተከሳሹ በባለቤትነት በሚያስተዳድሩት ቲኤፍ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተዘጋጁ ቼኮች ተቆርጠው ተፈርሞ እንደተሰጣቸው ይገልጻል።

ይሁንና አመልካቾች የቼኩ የመክፈያ ጊዜ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ወደ ባንኩ ያመሩ ቢሆንም፣ የባንክ ሒሳቡ በቂ ስንቅ ወይም ገንዘብ የሌለው በመሆኑ ክፍያው ሊፈጸምላቸው እንደማይችል ተገልጾ ቼኩም እንደተመታበት አብራርተዋል።

ሻጮች ሊካስ የማይችል የሞራልና የገንዘብ ጉዳት ሊደርስብን ችሏል ማለታቸውን ተከትሎ ፖሊስ በማጣራት፣ በተጠርጣሪው ግለሰብ አቶ ተመስገንና በድርጅታቸው ቲኤፍ ትሬዲንግ ላይ ደረቅ ቼክ መስጠት የወንጀል ክስ እንዲመሠርትላቸው፣ በተጨማሪም ከአገር እንዳይወጡ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ከሰነድ ማስረጃዎቹ ተመልክቷል።

በሌላ በኩል የአቶ ተመስገን ጠበቃ አቶ አወቀ መላክ በበኩላቸው፣ ደንበኛቸው ከቦሌ ኤርፖርት በሲዳማ የፖሊስ ኃይል ተወስደው ሐዋሳ ለሰባት ቀናት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር መቆየታቸውን፣ በወቅቱ የተቆረጠውንም ቼክ በወንድማቸው በኩል አቶ ተመስገንን ለማስፈታት በነበረ ጥረት በእርቁ ላይ ሊከፈል መቻሉን በመናገር ቼኩ በቂ ስንቅ እንዳልነበረው አረጋግጠዋል፡፡

በቀረበባቸው በደረቅ ቼክ የማጭበርበር ክስን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት አቶ ተመስገን፣ ‹‹ከቦሌ ገርጂ ቅርንጫፍ እንዲወጣ የተጻፈ ቼክ ሐዋሳ እንዲመታ ያደረጉት ሆን ብለው ከጥቅም ተጋሪዎች ጋር በመመሳጠር ነው፤›› ቢሉም፣ ቼኩ ሐዋሳ መመታቱን ከሚገልጸው ከበስተጀርባው ካረፈው ማኅተም በስተቀር፣ ንግግራቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ግን ለሪፖርተር ማቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሌላ በኩል አቶ ተመስገን ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ፖሊስ መምርያ ታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀርበው በሻጮች አቶ አርጋው፣ አቶ ዓለምገናና አቶ አማረ ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል ክስ አቅርበዋል።

በክሱ ላይም ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች የግል ተበዳይን የከሰል ማዕድን ማልሚያ ቦታ ሳይኖራቸው አለን በማለት፣ የከሰል ድንጋይ ማዕድን ድርሻ ሽያጭ አሥር ሚሊዮን ብር እንደሆነ በመጥቀስና በማታለል እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ብር በመቀበል፣ በጠቅላላው 10,750,000 ብር የወሰዱ በመሆኑ፣ በተጠቀሰው ወንጀል መጠርጠራቸውና ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም በተጠርጣሪዎች ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ማንኛውም የባንክ ሒሳባቸው እንዲታገድ በማለት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ በተጠርጣሪዎች ስም የሚገኙ ሁሉም ባንኮች እስከተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ድረስ ያላቸው ብር ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ መጠየቃቸውም ታውቋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ተጠርጣሪዎች እነ አቶ አርጋው የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የዕግድ ትዕዛዙ እንዲነሳላቸው ጠይቀው፣ ከከሳሽ ጋር ያላቸው ግንኙነትም የአክሲዮን ሽያጭ ግብይት እንጂ የማታለል ወንጀል እንዳልፈጸሙ ማስረዳታቸውን ሰነዶቹ ያስረዳሉ።

አቶ ተመስገን፣ ‹‹ድርጅታቸው የያዘውን አክሲዮን ለሌላ ግለሰብ አስተላልፈው ምንም ግንኙነት እንደሌለን በማስመሰል ለፖሊስ ያመለከቱት ፍጹም ሐሰት ነው፣ ይህ በተጠርጣሪዎች (ሻጮች) ዘንድ የሚገኘው ቼክ እንዳይመነዘር ወይም እንዳይመታ በማሰብ ብቻ በተጠርጣሪዎች ላይ ያልተገባና ሐሰተኛ ክስ በመመሥረት ጫና ለማምጣት የታሰበ ነው፤›› የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውንም ሰነዱ ያስረዳል።

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቦሌ ምድብ ችሎት መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ የፖሊስ የምርመራ ሥራ ለማገዝ በሚል ተላልፎ የነበረው የዕግድ ትዕዛዝ ሊቀጥል የሚችልበት አግባብ እንደሌለ መመልከቱን በመግለጽ፣ ዕግዱ እንዲነሳላቸው አድርጓል።

በክሱ ላይ ተጠርጣሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል በወቅቱ አቶ አርጋው በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር ውለው ለ20 ቀናት መቆየታቸውንና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ መለቀቃቸውን ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቦሌ ፖሊስ መምርያ ታኅሳስ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ፣ በከባድ የማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ለምርመራ የሚፈልጋቸውን ሦስቱን ተጠርጣሪዎች፣ የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምርያ በቁጥጥር ሥር አውሎ እንዲያስረክበው የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የያዙ ሦስት የፖሊስ አባላት ወደ ክልሉ  ሄደው ቢጠይቁም፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ፖሊስ መምርያ ትብብር ሊደረግላቸው እንዳልተቻለ ታውቋል፡፡

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽንም እንዲሁ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፈው የትብብር ደብዳቤ፣ አቶ ተመስገን በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በክልሉ በምርመራ ማጣራት ሒደት ላይ እንደሚገኙ፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሰቡ በተገኙበት እንዲያዙ ትዕዛዝ መስጠቱንና ተጠርጣሪውን እንዲረከቡ አንድ ኢንስፔክተርና አንድ ሳጅን የፖሊስ አባላትን መላካቸውን ሰነዱ ያስረዳል፡፡

በሲዳማ ክልል ከሳሽ የሆኑት አቶ አርጋው እንደሚያስረዱት፣ የፖሊስ አባላቱ በሥፍራው በደረሱበት ወቅት በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ሰው በስህተት ሌላ ሰው በመሆኑ መለቀቁን እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ተመስገን በሰጡት ምላሽ በእርግጥም የተያዘው ሰው በስህተት ሌላ ሰው እንደነበረና እሳቸው በቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉም አረጋግጠዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ከሲዳማና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች በወንጀል ክሶቹ ላይ ምርመራ እያካሄዱ ያሉ የፖሊስ አባላት ጋር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና የሞባይል ስልክ መልዕክት ቢልክም፣ ምላሽ ለማግኘት ባለመቻሉ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

አቶ ተመስገን መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፍትሕ ሚኒስቴር ቦሌ ምድብ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ያላግባብ የተነሳው ዕግድ ተመልሶ እንዲታገድላቸው፣ መዝገብ ተመርምሮ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሠረት አቤቱታ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ከሰነዱ መረዳት ችሏል።

በአቤቱታቸው ከከባድ የማታለል ወንጀል በተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ለፖሊስ ሐሰተኛ መረጃ በመስጠት እናታቸውን ለማሳከም ወደ ውጭ ሊሄዱ ሲሉ ከቦሌ ኤርፖርት እንዲመለሱ መደረጋቸውን አስታውሰው፣ ያልታወቀ ቦታ ታፍነው መወሰዳቸውንና ታፍነው ባሉበት ወቅትም አቶ አርጋውና አቶ ዓለምገና እያንዳንዳቸው ከወንድማቸው ላይ አምስት ሚሊዮን ብር መቀበላቸውን ተናግረዋል፡፡