ፅዮን ታደሰ

July 14, 2024

የኩባንያውን የ2016 ዓ.ም. ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት

ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 ዓ.ም. 732 ሺሕ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተደረጉበትና አንዳቸውም እንዳልተሳኩ አስታወቀ፡፡

የኩባንያውን የ2016 ዓ.ም. ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ያቀረቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በጀት ዓመቱ ሲጀመር በሳይበር ደኅንነት ላይ ያሉ ችግሮች ምን እንደሆኑ እንደሚለዩ ገልጸዋል። በዚህም ሁሉንም የሳይበር ጥቃቶች ሊያስከትሉት የሚችሏቸው ችግሮች በአንዴ እንደማይፈቱና በጊዜ ሒደት መፍትሔ የሚያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በ2016 በጀት ዓመት 732 ሺሕ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም፣ አንዱም የጥቃት ሙከራ አለመሳካቱን አመላክተዋል። ለዚህም ምክንያቱ የሳይበር ደኅንነትን የሚቆጣጠርና 24 ሰዓት የሚሠራ ቡድን በመኖሩ፣ ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በመከናወናቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

በ2015 በጀት ዓመት 72 ሚሊዮን የነበረው ጠቅላላ የደንበኞች ቁጥር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ 78.3 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስታውቀዋል። በተጨማሪ በገጠር አካባቢዎች 462 አዳዲስ የሞባይል ኔትወርክ ሳይቶች መዘርጋታቸውን፣ ከሌሎች አገሮች ጋር የነበረው ግንኙነትም በ21 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

በ2016 ዓ.ም. 93.7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ መገኘቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመው፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ21.7 በመቶ ወይም የ16.7 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ብለዋል። የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ምርትና አገልግሎቶችም 198 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም ተናግረዋል።

የተቋማቸውን የፋይናንስ ሪፖርት መሠረት አድርገው ገለጻ ያደረጉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ 21.79 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ መገኘቱንና በውጭ ኦዲተር እንዳልተመረመረ ጠቁመዋል።

እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ቴሌብር በበጀት ዓመቱ የደንበኞቹን ቁጥር 47.5 ሚሊዮን ያደረሰ መሆኑን፣ በሦስት ዓመት ውስጥም 2.5 ትሪሊዮን ብር የገንዘብ ልውውጥ እንዲደረግ ማስቻሉንና 1.8 ትሪሊዮን ብር በ2016 ዓ.ም. የተደርገ ዝውውር መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም 2.9 ሚሊዮን ደንበኞች ቴሌብርን በመጠቀም 9.5 ቢሊዮን ብር ብድር ማግኘታቸው ተነግሯል።

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ማጠናቀቅ ያልተቻሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በሪፖርታቸው የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የፋይበር መቆረጥና መሰረቅ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ችግር ተዘዋውሮ ለመሥራት ችግር እንደነበሩ ገልጸዋል።

አክለውም በአዲሰ አበባ ከተማና በሌሎችም አካባቢዎች የሞባይል ጣቢያዎች ለማስፋት በሚፈለገው ፍጥነት የመሬት አቅርቦት አለማግኘትና ጭራሽም ማግኘት አለመቻሉ፣ ማስፋፊያ ሊደረግባቸው እየተገባ ያልተደረገላቸው ቦታዎች እንዲኖሩ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ግጭት ኩባንያው ምን ያህል ገቢ እንዲያጣ እንዳደረገው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም የኢንተርኔት አገልግሎት አለመጀመሩ፣ በኮሪደር ልማቱ የተፈጠረው የአገልግሎት መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ለመፍታት የተከናወኑ ሥራዎችን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበው ነበር።

የበጀት ዓመቱ ሲጀመር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የብድር አቅርቦት ድርድር ሲደረግ ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ድርድሩ መጠናቀቁንና በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ የአሜሪካ የፋይናንስ ኩባንያ ብድሩን ለመስጠት መስማማቱን አስታውቀዋል። ይህንንም ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማፅደቅ ስለሚኖርባቸው እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል።

‹‹በግጭት ምክንያት አገልግሎት ማቅረብ ያልተቻለበትን የአማራ ክልል በገቢ ደረጃ ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጠረ የሚለውን ለክተናል፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ‹‹ነገር ግን ቁጥሩን መግለጻችን ጥቅም አይኖረውም፤›› በማለት ኩባንያው ያጣውን ገቢ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ተጨማሪ ወጪ በማውጣት ጊዜያዊ መስመር መዘርጋታቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ በሚደረግበት ወቅት የአገልግሎት ጥራት መጓደልም ሆነ መቋረጥ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል።