የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ውይይቱን ባካሄደበት ወቅት

ዜና የትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲዎችና የማኅበረሰብ ቁርኝትን በሚመለከት የሚወጡ ፖሊሲዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተጠየቀ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: July 14, 2024

የትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት የዩኒቨርሲቲዎችና የማኅበረሰብ ቁርኝትን በተመለከተ የሚያወጣቸው ማስፈጸሚያ የፖለቲካ ሰነዶች፣ ተግባራዊ መሆናቸውንና ክፍተቶቻቸውን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ጥያቄ ቀረበለት፡፡

ጥያቄው የቀረበው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ሐሙስ ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹የዩኒቨርሲቲ የማኅረበሰብ ተሳትፎ›› በሚል ርዕስ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር ውይይት ሲያደርግ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ከማኅረበሰብ ቁርኝት ጋር ተያይዞ ያወጣቸውን የፖሊሲ ሰነዶች ለውጤት ያበቁና ያላበቁ ዩኒቨርሲቲዎችን በመፈተሽ፣ በዘርፉ ያሉትን ክፍተቶች መለየት እንደሚያስፈልግ፣ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃን መስቀል ጠና (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎችና የማኅረበሰብ ቁርኝት እንዳያድግ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ የክትትልና የድጋፍ አነስተኛ መሆን እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ክፍተቶችን ለመሙላት ተቋማት እርስ በእርስ ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የማኅረበሰብ ቁርኝት ቢኖርም፣ የቅንጅት መላላት እንደሚታይ ገልጸው፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ዩኒቨርሲቲን የገንዘብ ማፈሻ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ሰጪ፣ ማኅረበሰቡ ደግሞ ተቀባይ›› የሚል አመለካከት ከዚህ በፊት እንደነበረ፣ ይህም አመለካከት ዩኒቨርሲቲዎች የዕርዳታ ማዕከል ናቸው የሚል ዕሳቤ እንደፈጠረ አክለው ገልጸዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲዎች መምህራንም ሆኑ ተመራማሪዎች ምርምር በማድረግ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት አለባቸው ተብለው በአዋጅ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ከማኅበረሰቡ አገልግሎት ጋር ያልተገናኙ ተግባራት ሲከናወኑ እንደሚገኙ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በተለይ የማኅበረሰብ አገልግሎት ትርጓሜው በራሱ የተሳሳተ የሚሆንባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብ አገልግሎት ለማከናወን ዩኒቨርሲቲያቸው ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ያለው የማኅበረሰብ ፍላጎት ምንድነው የሚለውን በመለየት ችግር ፈቺ የሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ማስቀመጥ ሲቻል፣ ማኅበረሰቡም ለዩኒቨርሲቲዎች ያለው አስተሳሰብ እንደሚቀየርና ምን ዓይነት ነገሮችን ማስረፅ እንደሚኖርበት ያስባል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰቡ ቁርኝት ለዩኒቨርሲቲዎች ያለው አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ገልጸው፣ በተለይ የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት የሚችሉ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎች ማውጣት ከቻሉ፣ ተማሪዎቹ የትም ሄደው የማኅበረሰቡ ደጋፊ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎች ማኅበረሰቡን ያካተቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወጥተው እንዲሠሩ ማድረግ፣ የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈቱና ከ17 የልማት ግቦች ውስጥ አንዱን አካተው እንዲሠሩ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲያቸው ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የማይችል አገልግሎት ምንም ጥቅም እንደሌለው፣ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት አገልግሎት የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ በተወሰነም ቢሆን መቀየር የሚችል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የማኅበረሰብ ቁርኝት በትክክል በመሥራት ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ዩኒቨርሲቲ፣ ማኅበረሰቡም እንደ ማኅበረሰብ፣ ተማሪዎቻቸውንም እንደ ተማሪነታቸው የሚያገኟቸው ጥቅሞች ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የማኅበረሰቡን ቁርኝት በተመለከተ ምን መሥራት ይኖርባቸዋል? ምንስ ይጎድላቸዋል? ለዚህ የሚያስፈልገወው ነገር ምንድነው? የሚለውን መለየት አለባቸው፤›› ያሉት፣ በአሜሪካ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት መምህር እንደነበሩ የተገለጸው አሰፋ ገብረ አምላክ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡