

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሰሞን አርባ ምንጭን ሲጎበኙ
ዜና አወዛጋቢው የሙስና አተረጓጎም በኢትዮጵያ
ቀን: July 14, 2024
በቅርቡ የወጣው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እ.ኤ.አ. የ2023 የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርት (Country Reports on Human Rights Practices: Ethiopia)፣ ኢትዮጵያን በሙስና ጉዳይም ክፉኛ ይወቅሳታል፡፡ በዚህ ሰነድ ኢትዮጵያ ሌላው ቀርቶ ለተራቡ ሰዎች የተላከ የሰብዓዊ ዕርዳታ እህል የሚዘረፍባት አገር ናት ሲል ጠንከር ባለ አገላለጽ ይፈርጃታል፡፡ በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ሕግ ቢኖርም መንግሥት ግን ሕጉን በአግባቡ ወይም በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ አያደርገውም ሲልም ሪፖርቱ ያብራራል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአገሪቱ ዕርዳታ ማስተባበሪያ መሥሪያ ቤት ወይም የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለሥልጣናት ጭምር፣ በሙስና ተጠርጥረው እስር ቤት እንደሚገኙ ይኸው ሪፖርት ከትቦታል፡፡
ሙስና በኢትዮጵያ ያልገባበት ዘርፍ አለመኖሩን ያለ ይሉኝታ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2022 አራት የብሔራዊ ፀጥታና ደኅንነት መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች በሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው መታሰራቸውን ጠቅሶ፣ የፍትሕ አካላት ጭምር የሙስና ተጠቂ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ከዚያ አንድ ወር ቀደም ብሎ 41 የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ባልደረቦች በሙስና መታሰራቸውን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ በየትኛውም ዘርፍ በየትም ቦታ ሙስና የተንሰራፋ ወንጀል ስለመሆኑ ይጠቁማል፡፡ ይህንኑ የሙስና ወንጀል ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጋር ለማገናኘት የሞከረው ሪፖርቱ/ ኢትዮጵያን ሰላም እየነሱ ካሉ ቀዳሚ ችግሮች አንዱ ሙስናና ምዝበራ መሆኑን ነው በግልጽ ያስቀመጠው፡፡
የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ወርኃዊ ጋዜጣ የግንቦት ወር መጨረሻ ዕትምም ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ርዕሰ አንቀጽ ከትቦ ነበር፡፡ ‹‹ሙስና ለሰላም መደፍረስ በር ይከፍታል!›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ርዕሰ አንቀጹ፣ ሙስና የሰላም ዕጦት ምንጭ ስለመሆኑ በሰፊው አትቷል፡፡
‹‹ሰላም ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት ምሰሶ፣ ለሰው ልጆች አንድነት፣ መቻቻል፣ መከባበርና አብሮነት ደግሞ ዋልታና ማገሩ ነው፡፡ ሰላም ትልቅ ዋጋ ያለው በምንም ዓይነት መስፈርት ሊለካ የማይችል ውዱ የፍጥረታት ሁሉ ሀብት ነው፡፡ ስለሰላም ውድነት ለመገንዘብ ዛሬ በሰላም ዕጦት የሚሰቃዩትን እንደ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያና ሌሎችም የዓለማችን አገሮች መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ለዚህ የሰላም ዕጦት እንደ ዋነኛ መንስዔ ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል ደግሞ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይገኙበታል፡፡ ሙስና የመንግሥትና የግል ሀብትን በሥርቆት ለግል ጥቅም አሊያም ለቡድን ጥቅም የማዋል ድርጊት ነው፡፡ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተመጋገቡና እየሰፉ ከሄዱ ግዙፍ የመንግሥት ሀብት የግለሰቦች ኪስ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ሥራ አጥነት እንዲበራከት፣ የጥቅም ግጭቶች እንዲስፋፉ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሸረሸር፣ አገራዊ ስሜት እንዳይኖር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲከሰቱ፣ ሕገወጥ ንግድ በተለይ የጦር መሣሪያ ንግድ እንዲስፋፋ፣ መተማመን እንዲጠፋና ግጭቶች እንዲፈጠሩ በጥቅሉ ለሰላም መደፍረስ በር ይከፍታል፤›› በማለት ነው ይህ ርዕሰ አንቀጽ የሙስና ችግር አደጋ የት ድረስ እንደሚሄድ ያስቀመጠው፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በየዓመቱ በሚያወጣው የአገሮች የኢንቨስትመንት ምቹነት (Investment Climate Statements: Ethiopia) እ.ኤ.አ. የ2023 ሪፖርት ላይም ኢትዮጵያ በሙስና ጉዳይ ዝቅተኛ ደረጃ ይሰጣታል፡፡ በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ኮሚሽኑም ሆነ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለፓርላማው መሆኑን፣ ይህ የሆነው ደግሞ በገለልተኝነት ያለ ተፅዕኖ የሕዝብን ጥቅም እንዲያስጠብቁ ታስቦ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው የሙስና ደረጃ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽና እንዳረጋገጠ ይጠቁማል፡፡ እ.ኤ.አ በ2022 ዓመት ከ180 አገሮች ኢትዮጵያ 94ኛ ደረጃ ላይ እንደሰፈረች በመጥቀስ፣ አገሪቱ ከቀደመው ዓመት በሰባት ደረጃዎች ያነሰ ውጤት እንዳመጣች ያመለከተው ሪፖርቱ በሙስና መንሠራፋት በኩል ኢትዮጵያ እየባሰባት እንደመጣ ያመለክታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 የአሜሪካ ንግድ ማኅበረሰብ ተቋም በኢትዮጵያ አንድ የግምገማ ጥናት ማድረጉን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ የአገሪቱን የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሚፈትኑ ችግሮች መካከል በአስተዳደር በኩል የሚታየው የግልጽነትና የሙስና ችግር አራተኛው ፈታኝ ችግር እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ የተመድ የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን ፈራሚ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ኅብረትን ሙስና መከላከል ኮንቬንሽን ፈራሚ፣ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ የፀረ ሙስና አሶሴሽን አባል እንደሆነች ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙስና በመንግሥታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግዥ አሠራር፣ በገንዘብና በፍትሕ ተቋማት ጭምር እንዳለ ያምናል፡፡ መንግሥት የፀረ ሙስና ኮሚቴ በሚል በቅርቡ ከፌደራል እስከ ክልሎች በተለያዩ ተዋረዶች ኮሚቴ ስለማቋቋሙም የሚያወሳው ሪፖርቱ፣ ይህም ቢሆን ግን ችግሩን በመዋጋቱ ሒደት እየተፈተነ ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡
ዓርብ ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት ግን ሙስናን መከላከል ላይ ጥሩ ሥራዎች ስለመሥራቱ ተናግሯል፡፡ ኮሚሽኑ በዓመቱ 2.1 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም 46.4 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የከተማና ገጠር መሬት ከሙስናና ምዝበራ ወንጀል መታደጉን ይፋ አድርጓል፡፡ የ175 ሺሕ አመራሮችንና የሥራ ኃላፊዎችን ሀብት ምዝገባ ማከናወኑን ያመለከተው ኮሚሽኑ በግዥ፣ በንብረት ማስወገድ፣ ገቢ አሰባሰብ በመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ክዋኔዎች ሒደት ሊፈጸሙ ይችሉ የነበሩ በርካታ የሙስና ነክ ወንጀሎችን መታደግ ስለመቻሉ ይዘረዝራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በፓርላማ ማብራሪያ ሲሰጡ ሙስናን በተመለከተ፣ ‹‹ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምልከታ ነው ያለኝ፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ በፊት ሙስናን አልታገልንም እያሉ መንግሥትን ሲወተውቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሁን ባለሁበት የሥራ ቦታ ግን ጉዳዩን በሚዛን ነው የማየው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ የሙስና አሳሳቢነትን በሚመለከት ደግሞ፣ ‹‹ሌብነት ነቀርሳ ነው፣ ሌባ ሰው ምንም ቢሆን ዋጋ የለውም፡፡ ለራሱም ለልጆቹም ዋጋ የለውም፣ ልንዋጋውና ልናቆመው ይገባል፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቢናገሩም የሙስና ደረጃው ሥርዓታዊ ነው መባሉን ግን ክፉኛ ሲቃወሙት ነው የታዩት፡፡
በተለይ በተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካዩ አብርሃም በርታ (ዶ/ር) ሙስናን በተመለከተ አሳሳቢ ያሏቸውን ችግሮች በትኩረት ሲያነሱ፣ ችግሩ የመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ሥር ሰዶ መግባቱን ያስቀመጡበት ሁኔታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋጠ አይመስልም ነበር፡፡
አብርሃም (ዶ/ር)፣ ‹‹ብዙ አገሮችን ለውስብስብ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ከሚዳርጉ ችግሮች አንዱና ዋናው ሥር የሰደደ መንግሥታዊ ሌብነት ነው፡፡ ሙስና የአገራችንን መዋቅር የሚበላ የሕዝብን ማኅበራዊ ትስስር የሚበጣጥስ፣ የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽር፣ አገር እንዳታድግ የሚይዝ ማኅበረሰባዊ ካንሰር ነው፡፡ አገራችን የምትገኝበት የሙስና ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የፌደራል ኦዲት መሥሪያ ቤት የሚያቀርበው ሪፖርትና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይህንኑ አሳሳቢ የምዝበራ ደረጃ ያረጋግጣሉ፤›› የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ይህን ለመቀበል ያልወደዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ሙስና ሥርዓታዊ ሆኗል መባሉን ክፉኛ ተቃውመውታል፡፡
‹‹ይህ ፓርላማ ሙስናን እንድንታገል ይፈልጋል ወይ? ትፈልጋላችሁ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙስናን እንድንታገል ይፈልጋል ወይ፡፡ አዎ በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር ነው፡፡ በቀደም የንብረት ማስመለስ አዋጅ መጥቶ ነበር፡፡ ምንም በማያውቁ አክስቶች፣ ምንም በማያውቁ አያቶች የሚንቀሳቀሱ ትልልቅ ገንዘቦች አሉ፡፡ ይኼንን ገንዘብ ከየት አመጣኸው ብሎ መጠየቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አይችልም፡፡ ሕግ የለም፡፡ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅስ ሰው ማስረጃ ማቅረብ አለበት በሚል ተወያይተን ሕግ ስናወጣ ከውጭ አገር በሬሚታንስ አሥርና ሃያ ዶላር የላኩ ሰዎችን ለመቅጣት ነው ተባለ፡፡ ይህ አይደለም ሌቦች አሉ፡፡ የሚወጡ ሕጎች ጤነኞችን ለመንካት አይደለም፣ አጥፊዎችን ለማረም እንጂ፡፡ ዕርምጃን በሚመለከት በሺሕ የሚቆጠር ሀብት ተመልሷል ብዙ ሰዎች ታስረዋል፡፡ ግን በቂ አይደለም ከዚያ በላይ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ብሩ ስላላቸው ለዩቲዩበሮች ይከፍሉና ያንጫጩታል፡፡ ገና ሕጉ ሳይወጣ አየሩ ይንጫጫል፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸው ሙስናን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ቢሆንም ተቃዋሚዎቻችን ያሏቸውና ሙሰኞች እንቅፋት እንደሆኑባቸው አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት በኩል ያለው ቁርጠኝነት ግን ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ አበክረው የተከራከሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሁለት መንገዶች የተከበረው ምክር ቤት ሚዛናዊ እንዲሆን እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡
‹‹አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት መቶ በመቶ ከፈለጋችሁም አንድ ሚሊዮን በመቶ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው መንግሥታዊ ሌብነት አያካሂድም፡፡ የፈለገ ዓለም ተቋም የፈለገ ዓለም ሳይንቲስት መርምሮ መንግሥታዊ ሌብነት አንድ ብር ሊያገኝብን አይችልም፡፡ እኛ የኢትዮጵያን ሀብት አናሸሽም፡፡ ለዚህ ነው ከተማችንን የምንሠራው፡፡ ሲሸሽማ እንዴት እንደነበር እናውቃለን፡፡ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ይህ መንግሥት አንድ ብር አይዘርፍም፡፡ ያገኛትን ገንዘብ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ተቃዋሚዎቻችን ሥራችንን መደበቅ ሲያቅታቸው ከየት አምጥተው ሠሩት በሚል ይከሱናል፡፡ መንግሥታዊ ሌብነት በኢትዮጵያ የለም፡፡ ይህ ማለት ግን በሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎችና ግለሰቦች አይሰርቁም ማለት አይደለም፡፡ ሁለተኛው ምክር ቤቱ እንዲያስተውል የምፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሙስና በየትም የአፍሪካ አገር ካለው ሙስና ጋር የማይወዳደር መሆኑን ነው፡፡ በሌላ የአፍሪካ አገር አንድ የፓርላማ አባል የሚበላው ደመወዝ እዚህ ካላችሁ 10/15 ሰዎች ሊበልጥ ይችላል፡፡ የአንዳንድ አፍሪካ አገሮች መሪዎች የሳምንት ደመወዛቸው የእኔን የዓመት ደመወዝ ሊያክል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚያገለግሉ ሰዎች በውስጣቸው ሌብነት ኖሮ ፓርላማውም አስፈጻሚውም በየደረጃው ያለ አመራር ራሱን ጎድቶና ተቸግሮ ነው አገሩን የሚያገለግለው፡፡ ለዚህ ነው ህዳሴ ግድብን የምንገነባው፣ ለዚህ ነው 25 ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ የምንገነባው፡፡ ብንከፋፈለው እኮ ብሩ ያልቃል፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥታቸውን ተከላክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሙስና ተጋላጭነት መኖሩ ሁሉንም ያግባባል፡፡ በኢትዮጵያ ሙስና በአሳሳቢ ደረጃ ጨምሯል የሚለው ሥጋትም ብዙዎችን ያግባባል፡፡ ይሁን እንጂ ሙስናው ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ይፈጸማል ወይም ‹‹ስቴት ካፕቸር›› የሚባለው ደረጃ ላይ ደርሷል የሚለው ጉዳይ ግን ያሟግታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ ይህን ውንጀላ ክፉኛ ተቃውሞታል፡፡
ከሰባት ወራት ቀደም ብሎ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት፣ ስለ የፖለቲካ ገበያ (Political Market Place) ፈተና ሰፊ ሐሳቦችን ሲያነሱ ተደምጠው ነበር፡፡ በወቅቱ ሙስና፣ ምዝበራ፣ በሥልጣን መባለግና ንቅዘት የመሳሰሉ ጉዳዮች የፖለቲካ ገበያ (Political Market Place) የሚል ጥቅል ትርጓሜ ተሰጥቷቸው ማብራሪያ ሲሰጥባቸው ነበር፡፡ ‹‹ትልቁ የዚህ አገር ፈተና የፖለቲካው ገበያ ነው፡፡ መገረዝ ያለበት አስተሳሰብ እሱ ነው፡፡ ለብልፅግና ባለን ጉጉትና ሥራ ላይ እንቅፋት የሚሆን የፖለቲካ ገበያ በማንኛውም መንገድ መገረዝ አለበት፡፡ አደገኛና ጉዟችንን የሚያቆም ስለሆነ፡፡ የፖለቲካ ገበያው ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ የኢትዮጵያን ብልፅግና ጉዞ አደጋ ውስጥ ከቶታል፤›› በማለት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ስለፖለቲካ ገበያ ዘርዘር ሲያደርጉም በሕግ የሚከወን ፖለቲካ እንዳለ በመጠቆም፣ ሌላኛው የዚህ ተቃራኒ ደግሞ፣ ‹‹በገንዘብና በጥቅም የሚሸቀጥ ፖለቲካ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሙስናና ምዝበራ በሥርዓቱ ላይ የደቀነውን አደጋ በሰፊው አስረድተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካ እንደ ቀሸጥ ለገበያ እየቀረበና ለግል ፍላጎት መጠቀሚያ እየሆነ ነው ብለው፣ ነገር ግን ፓርቲያቸው ብልፅግና ትልልቅ የሙስና ችግር ውስጥ የለም ብለዋል፡፡ ‹‹በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ብልፅግናን ለሙስና የመጠቀም ችግር የለም፤›› ሲሉ በጊዜው ሲናገሩ መደመጣቸው ይታወሳል፡፡ ከሰሞኑ በፓርላማው በነበረው ውይይት ወቅትም ይህንኑ በመድገም ስቴት ካፕቸር ወይም መዋቅራዊ ሙስና በኢትዮጵያ የለም ብለዋል፡፡
ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ዳጉ ፕሮግራም ላይ ተወያይ ሆነው የቀረቡ ሦስት ከሙስና ጋር የተያያዘ ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎች አስተያየትም የሙስናው ደረጃና አድማስ መስፋቱን ያመለክት ነበር፡፡ በፀረ ሙስና ኮሚሽን የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ጋሻው ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ 25 ዘርፎች ላይ የሙስና ተጋላጭነት ጥናት መካሄዱን አመልክተው ነበር፡፡ በጥናቱ መሠረት በፕሮጀክቶች አስተዳደር አካባቢ፣ ፕሮጀክቶች መዘግየት፣ በፕሮጀክቶች ለተጨማሪ ወጪ መዳረግ፣ ከግዥ አፈጻጸም ጋር በተያያዙ የአሠራር ሒደቶች ሙስና እንደሚያጋጥም ጠቁመዋል፡፡
‹‹አገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት አሁንም ችግሩ አልቀረም፡፡ የሙስና ሥጋት ተጋላጭነት ጥናቱ ይህን ነው ያመለከተው፤›› ብለው፣ ይህ ጥናትም ለየተቋማቱ ተሰጥቶ የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅተው የመከላከል ሥራ እንዲጀምሩ መወሰኑን አመልክተዋል፡፡
ሌላኛው ተወያይና ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መንግሥታዊ ተቋማት ላይ የሚፈጸም ሙስናን መካከል ሥራ ክፍል የመጡት ዋና ኢንስፔክተር ቢቂላ ታደለ በበኩላቸው፣ በመሬት ዘርፍ የተገኙ ከባድ ጥፋቶችን በጉልህ አውስተዋል፡፡ ‹‹መሬት አካባቢ ነው አብዛኛው ወንጀል የሚፈጸመው፡፡ ከወረዳ ጀምሮ ነው ወንጀሉ የሚፈጸመው፡፡ አርሶ አደር ያልሆነ ሰውን እየመዘገቡ መሬት ይቸበችባሉ፡፡ አርሶ አደር ከሆነ 500 ልጅ ከሆነ ደግሞ 150 ካሬ ሜትር ይቀራመታሉ፤›› በማለት የጠቀሱት ዋና ኢንስፔክተሩ ከሰነድ ዝግጅት ጀምሮ በተዋረድ ያሉ ሠራተኞች በዚህ ወንጀል እንደሚሳተፉ አመልክተዋል፡፡
በመሥሪያ ቤት በተለይም በግዥ አካባቢ የሚፈጸሙ ወንጀሎችም ብዙ መሆናቸውን፣ በተለይ የግዥ መመርያን ክፍተቶች በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ውስጥ በተለይ ኢሚግሬሽን አካባቢ የሚፈጸሙ ወንጀሎችም ከፍተኛ መሆናቸውን፣ ቪዛና ፓስፖርት በመፈጸም ሒደት እንዲሁም በወረዳዎች መታወቂያ ለማግኘት ሲኬድ መብትን በነፃነት ለማግኘት ዜጎች እንደሚቸገሩም አክለው አውስተዋል፡፡
የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት የሕግ ተመራማሪው አቶ ታደለ ተካ በበኩላቸው፣ በፍትሕ አካባቢ ያለውን የሙስና ደረጃ አስረድተዋል፡፡ ‹‹እኛ በሕጎችና አፈጻጸማቸው ላይ ምርምሮች እናካሂዳለን፡፡ ሙስናን በተመለከተ ከኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ ተፅዕኖው አንፃር እያስከተለው ያለውን ጉዳት መንግሥት የሚቀበለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሙስና ወንጀሎች የሚፈጽሙ አካላትን ተከታትሎ ለፍትሕ በማቅረብ ሒደት፣ ሕጎቹን ተግባራዊ በማድረግ ሒደት፣ ከፍትሕ አካላት ጀምሮ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ችግሮች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ጥቆማዎች ይቀርባሉ ነገር ግን እነዚያ ነገሮች ምላሽ አያገኙም፤›› በማለት በዚህ ረገድ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል፡፡
ተወያዩ አክለውም ምርመራ ከተጀመረ በኋላ ሒደቱ እንደሚቋረጥ፣ ሆን ተብሎ እንዲጓተት እንደሚደረግ እንዲሁም ያላግባብ ክስ የሚቀርብበት ሁኔታ እንዳለ በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ ለቀረቡ ክሶች ተገቢ ምላሽ የመስጠት ችግር መኖሩን፣ የሙስና ፈጻሚዎችን ከለላ ለመስጠት የሚደረግ ሙከራም እንዳለ አመልክተዋል፡፡
‹‹የሙስና ወንጀል በሚስጥር የሚፈጸም መሆኑ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪም በጥቅምና በዝምድና ከሕግ ለማስመለጥ የሚደረገው ሙከራም ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሙስና ወንጀልን በተመለከተ ራሱን የቻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ በኢትዮጵያ የለም፡፡ አጠቃላይ የወንጀል መከላከል አካል ሆኖ ነው እየተሠራበት ያለው፤›› በማለት በዚህ ጉዳይ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን በተጨማሪ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሙስና መኖሩ ባያከራክርም የሙስናው ደረጃና ዓይነት ግን እያወዛገበ ነው የሚገኘው፡፡ ጉዳዩ ላይ አንድ ዓይነት አገራዊ መግባባትም ሆነ የአተረጓጎም መቀራረብ ሳይኖር ችግሩን ለመቅረፍ የሚካሄዱ ጥረቶች እንዴት ይሰምራሉ የሚለው ከወዲሁ እየተነሳ ያለ ሥጋት ነው፡፡
ሙስናና ምዝበራ በድብቅ ሳይሆን በይፋ የሚፈጸም ወንጀል እየሆነ መምጣቱን ብዙዎች ሲያስተጋቡት ይደመጣል፡፡ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ኅዳር 30 ቀን ጠብቃ ዓለም አቀፉ የፀረ ሙስና ቀንን ታከብራለች፡፡ በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ንቅናቄ እየተባለ ብዙ ዘመቻና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲካሄድም ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 ላይ እንደተደነገገው ከሆነ ደግሞ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ሆኖ ተጠያቂነት ባለው መንገድ መከናወን እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት እንደሚችልም ተደንግጓል፡፡ ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለበትም በግልጽ ተቀምጧል፡፡
ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ለብዙ ነገሮች የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ማንም ሹመኛ ወይም ባለሥልጣንና የመንግሥት አገልጋይ ሁሉ የሕዝብ ወይም የአገር ሀብት የዘረፍኩት ደመወዜ ስለሚያንስ ወይም ልጆቼ የሚበሉት ስለቸገራቸው ነው ሊል እንደማይችል ድንጋጌው መነሻ ይሆናል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ በ1993 ለተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚሽን መነሻ የሆነ የሕግ ድንጋጌ ሲሆን፣ በሙስና መከላከል እንዲሁም መንግሥታዊ የአሠራር ሥርዓት ሥነ ምግባርች ማስፈን ሒደት ለወጡ ሕጎችም ወሳኝ መሠረት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ የሚያደርገው ስለፈለገ ሳይሆን ይህን መሰል ጥብቅ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታም ስላለበት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡
ሙስናን በተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ ብቻ መከላከሉን ውጤታማ እንደማያደርገው ይነገራል፡፡ ሙስናን የሚከላከል ራሱን የቻለ ኮሚሽን ወይም ተቋም ማደራጀት ብቻውን በፀረ ሙስና ትግል ላይ ድል ለመቀዳጀት በቂ እንዳልሆነም ይነገራል፡፡ ሙስና ዓይነቱ እጅግ የበዛ አፈጻጸሙም እጅግ የረቀቀ የወንጀል ድርጊት በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ትግል ማድረግ እንደሚጠይቅ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡ ሙስና የኢኮኖሚ ወንጀል ብቻ አይደለም፣ ሙስና የማኅበራዊ ነቀርሳም ብቻ አይደለም፣ ሙስና ፖለቲካዊ ንቅዘትን የሚያመጣና የአገር ሁለንተናዊ መሠረትን የሚያናጋ መሆኑም ይወሳል፡፡
