ዳዊት ታዬ

July 14, 2024

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ አጠቃላይ አሠራር ወደ ተሻለ ደረጃ ያራምዳል ያላቸውን ፖሊሲዎች እንዲተገበሩ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እያደረጋቸው ያሉ ማሻሻያዎችና አዳዲስ ፖሊሲዎች በዋናነት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ያለሙ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ 

ባለፈው ዓመት አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳመለከተው የገንዘብ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች በዋናነት የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑም በግልጽ አስቀምጧል፡፡  

በወቅቱ በተሰጠው ውሳኔ መሠረት የገንዘብ ፖሊሲውን ለማስፈጸም እንዲተገበሩ ካደረጋቸው መመርያዎች መካከል አንዱ የባንኮች የብድር መጠን ዕድገት ከ14 በመቶ በላይ እንዳያልፍ የጣለው ገደብ ይገኝበታል። ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግም የ2016 በጀት ዓመት ተጠናቋል። ነገር ግን ይህ ውሳኔ በተለይ አነስተኛ ብድር ሲሰጡ የነበሩ ባንኮችን የማበደር አቅም በእጅጉ የሚጫን በመሆኑ በገደቡ ምክንያት ማበደር ይችሉ የነበረውን ያክል እንዳያበድሩ ተፅዕኖ አሳርፎባቸው አልፏል፡፡

የብድር ገደብ ውሳኔው የሚያስከትልባቸውን ጫና በመዘርዘር ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ባንኮች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቢያመለክቱም መልስ ሊያገኙ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

የሒሳብ ዓመቱ እንዲህ ባለ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ የ2017 የሒሳብ ዓመት አንድ ብሎ በተጀመረበት የመጀመርያው ሳምንት ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲና አሠራር ይዞ መጥቷል፡፡ ለአንድ ዓመት የተገበረውን የገንዘብ ፖሊሲ ውጤት ማምጣቱን፣ በተለይም ቀደም ብሎ ባስቀመጠው ግብ መሠረት የዋጋ ንረት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማስቻሉን ገልጿል፡፡ 

አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ እንደሚሸጋገር ነው፡፡ ይህንን ከገለጹ ከቀናት በኋላም በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተው አዲሱ አሠራር መተግበር ተጀምሯል፡፡ በአዲሱ የገንዘብ የፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረት ባንኩ በዋናነት የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን ለማሳየትና አጠቃላይ የገንዘብና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ-ነክ የወለድ ምጣኔ (National Bank Rate) የሚባለውን የፖሊሲ ተመን (Policy Rate) በመጠቀም የሚተገበረው ነው፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ እንደ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ሁኔታ እየታየ ከፍ ወይም ዝቅ በሚል ሁኔታ የሚሠራበት ሲሆን፣ በሚል ሁኔታ የሚሠራበት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንኩ ፖሊሲ-ነክ የወለድ ምጣኔ ለመጀመርያ ጊዜ 15 በመቶ ሆኖ ወደ ሥራ እንዲገባም ተደርጓል፡፡ ይህ የወለድ ምጣኔ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ የሚሠራበት ነው፡፡ 

ማለትም እየቀነሰ ያለውን፣ ነገር ግን አሁንም ከፍ ብሎ የሚታየውን የዋጋ ንረት፣ ዝቅተኛ የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገትና ካለፉት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ የመጣውን የባንክ ብድር ዕድገት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ-ነክ የወለድ ምጣኔ በአሁኑ ጊዜ ባንኮች እርስ በርስ በሚበዳደሩበት ብድር ላይ ከሚከፍሉት ወለድ ጋር የተቀራረበ ነገር ግን ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጧቸው ብድሮች ላይ ከሚያስከፍሉት ከ16 እስከ 20 በመቶ ከሚደርስ ወለድ ያነሰ በመሆኑ ይህ የብሔራዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ ተመን የሚመለከት አለመሆኑንም አመልክቷል፡፡ 

በዚህ ፖሊሲ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በረሃ ተስፋ (ዶ/ር) እንዲህ ያለው ፖሊሲ በሌላም አገር የሚተገበርና አስፈላጊም ነው ይላሉ፡፡ 

በአዲሱ ፖሊሲ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የባንክ ባለሙያ እንደገለጹትም ፖሊሲው አዳዲስ አሠራሮችን በኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲተገበር ከማድረግ ባሻገር ባለፈው ዓመት ተጥሎ የነበረውን የ14 በመቶ ገደብ ወደ ማንሳት ሊሸጋገር የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ቀደም ሲል የተጣለው የ14 በመቶ የብድር ገደብ ስለመነሳቱ ባይገልጽም በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ከተሸጋገረ ይህ ፖሊሲው የሚያስገኘው ውጤት ታይቶ ባንኮች ላይ የጣለውን የ14 በመቶ የብድር ገደብ ሊያስነሳ ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ይህም ባይሆን ግን አዲሱ ፖሊሲ ለባንኮች ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ስለመሆኑ የሚገልጹት እኝሁ ባለሙያ ባንኮች ተጨማሪ ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ዕድል የሚፈጥር ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የ14 በመቶ የብድር ገደቡ መመርያ ተፅዕኖ ያሳረፈባቸው ባንኮች አሁን ከብሔራዊ ባንክ ብድር የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥርላቸው እንደሚሆንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

ሌላው የባንክ ባለሙያ ደግሞ እንዲህ ያለው አሠራር እሳቸው በሚሠሩበት ባንክ በኩል ሲጠበቅ የነበረ ነው፡፡ እንደውም ዘግይቷል የሚሉት እኝህ ባለሙያ አዲሱ ፖሊሲ ከባንኮች አንፃር የሚኖረውን ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ አብራርተዋል፡፡

የዚህ ፖሊሲ ተግባራዊነት በኢንዱስትሪው ውስጥ ይታይ የነበረውን በተለይ ከገንዘብ እጥረት (ሊኪውዲቲ) ጋር የተያያዘ ችግር የሚያቀል ወይም የሚፈታ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም የማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ የሚባል ነገር ያልነበረ ሲሆን፣ አሁን ይህ እንዲሆን መደረጉም በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ ባንክ ብድር ስትወስድ በ18 በመቶ ወለድ ነው፡፡ ከብድር ጋር በተያያዘ የተዘበራረቀ አሠራር ነበር፡፡ ይህ ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን የብሔራዊ ባንክ ሬት መውጣቱ እስካሁን የብድር ሁኔታዎችን የተመለከተ መነሻ ስላልነበር አሁን መነሻ ኖሮት እንዲሠራበት ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

ከኢኮኖሚውም አንፃር ቢሆን ይህ አሠራር ጠቀሜታ አለው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የበለጠ የሚፈልገው ገንዘብ ወደ መንግሥት እንዲሰበሰብና ባንኮች ገንዘብ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲልኩ፣ በመሆኑ የወለድ ተመኑ ሲቀንስ ደግሞ በተለይ ባንኮች ገንዘቡን እዚያ ከማስቀመጥ ይልቅ (ስለማያዋጣ ማለት ነው) ለብድር ማዋል እንዲችሉ ያስችላል፡፡

እንዲህ ያለው አሠራር በሌሎች አገሮች የተለመዱ በመሆኑ በተለይ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የወለድ ምጣኔ ሬት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ መጠቀም የተሻለ በመሆኑ ይህ ፖሊሲ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚለውን እምነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ 

በአዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ሌላው የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያ ደግሞ አስተያየት የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው ስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት ከጁላይ 1 ቀን 2024 ጀምሮ ኦፕን ማርኬት ኦፕሬሽን እንተገብራለን ብሎ መግለጹን በማስታወስ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የ14 በመቶ የብድር ገደብ ጥሎ የነበረው የዋጋ ንረቱን ያባባሰውና ችግር የሆነው አንዱ የባንኮች ልቅ የሆነ የገንዘብ ሥርጭት ነው የሚል አንድምታ ነው፡፡  

በተለይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን የዋጋንረት የሰቀለው ባንኮች ብዙ ብድር በመስጠታቸው ነውና የብድር ገደብ ማስቀመጥ አለብን ተብሎ ስለመወሰኑም አስታውሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከብድር ገደቡ ጎን ለጎን ባንኮች ከእያንዳንዱ ከሚሰጡት ብድር ሃያ በመቶ ትሬዥሪ ቢል እንዲገዙ በመወሰን ይህንኑ አሠራር እየተገበረ ነው፡፡ 

እነዚህ ሁለት ዕርምጃዎች በሞኒተር ፖሊሲው ሲቀመጡ ባንኮች ሊያበድሩ የሚችሉትን ገንዘብ እንዲቀንሱ ለማስቻል ነው አሁን ግን ገበያ መር ወደ ሆነ ኢንተረስት ቤዝድ ሞተሪ ፖሊሲ እንሸጋራለን ወደሚል መግባቱ እሳቸውም ጥቅሙ የጎላ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡ አንዱና ዋነኛው እንዲህ ያለው አሠራር ማዕከላዊ ባንኩ ሊኪዲቲውን በተሻለ መንገድ ማኔጅ ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡ የሚቀርበውን የገንዘብ መጠን ሊወስን ስለሚችልና ባንኮች እርስ በርስ የሚገበያዩትን ወለድ ደግሞ መነሻ ሬት ስለሚያደርግ ብሔራዊ ባንክ የተሻለ የሊኪውዲቲ ማኔጅመንት ይፈጥርለታል፡፡

ከዚህ ባሻገር በፖሊሲው ዙሪያ ገዥው እንደገለጹም እየቀነሰ የመጣው የብድር አሰጣጥ ለማሻሻል የሚል ነበርና የብድር አቅርቦቱ ይሻሻላል ማለት ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በዚህ አሠራር ለብድር የሚሆን ገንዘብ ስለሚጨምር ደንበኞች ብድር የማግኘት ዕድላቸው ይሰፋል፡፡ 

ይህ ሬት አሁን ባለው ተመን የሚወሰነው ሦስት በመቶ ከፍና ዝቅ የሚል ዕሳቤ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን የዚህ አሠራር አንዱና ዋነኛ ዓላማው ባንኮች ሊኪውዲቲ ሲያንሳቸው ከብሔራዊ ባንክ ሄደው ለዕለት የሚሆን ብድር እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ 

አዲሱ ፖሊሲ ሌላው ጠቀሜታ ነው ብለው የገለጹት ባንኮች ለብድር የሚፈልጉን ገንዘብ ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲቀመጥላቸው የሚከፍሉትን ከፍተኛ የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ መጠን ሊቀንስላቸው መቻሉ ነው፡፡ አንዱ ባንክ ሌላው ባንክ ውስጥ በማስቀመጥ ሲሠራበት የቆየው አሠራር የማይንቀሳቀስ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፈለውን ወለድ ከፍ እንዲል ሲያደርግ ስለነበር በብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የወለድ ምጣኔ በመወዳደር የሚያገኙት ገንዘብ የማይንቀሳቀስ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ ከሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ዲፖዚቱ ያነሰ በመሆኑ እንደሚጠቅማቸው ገልጸዋል።

በከፍተኛ የወለድ ምጣኔ የሚቀመጥ ገንዘብ በተለይ ትናናሽ ባንኮች የሊኪውዲቲ ችግር ስላለባቸው ከሌላ ባንክ በከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ገንዘብ ይወስዱ የነበረውንም አሠራር አዲሱ ፖሊሲ ይህንን የተለመደ አሠራር ሊያስቀር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ 

አዲሱ ፖሊሲ ጠቀሜታ በዚህን ያህል ደረጃ የሚገለጽ ቢሆንም ተፅዕኖ አይኖረውም ማለት እንደማይቻል የባንክ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ደግሞ የጠቀሜታውን ያህል ተፅዕኖውም እንዳለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት አዲሱ የመዋዕለ ንዋይ ፖሊሲ ሊኖረው የሚችል ተፅዕኖን በተመለከተ እነዚህ ማሻሻያዎች የብሔራዊ ባንክ የመዋዕለ ንዋይ ፖሊሲ ማዕቀፍን በማዘመን፣ የፖሊሲ መሣሪያዎቹን ከዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣምና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የዋጋ መረጋጋትን በማረጋገጥ ረገድ ታሪካዊ ዕርምጃን ያመለክታሉ ይላሉ፡፡ 

ይህ ፖሊሲ ለውጥ፣ በተለይም የብሔራዊ ባንክ ተመንን ማስተዋወቅ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ብድር ረገድ በዕዳ ፋይናንስ ግብይቶች ላይ ከፍተኛ አንድምታ አለው። ሊታሰብባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ነጥቦች ብለው ካስቀመጡዋቸው መካከል የብድር ዋጋና የወለድ ተመን አደጋ አንዱ ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ተመን በአገሪቱ ውስጥ ባለው የብድር ወጪ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ተመኑን ከፍ ካደረገ፣ አበዳሪዎች በተበዳሪዎቻቸው ላይ የመበደር ወጪዎችን ሊጨምሩ ይችላሉ፣ ይህም በነባርና አዲስ የዕዳ ግብይቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።

ዕዳ እንደገና ፋይናንስ ለማድረግ ተግዳሮቶች ሊኖሩት እንደሚችል ጠቀመው፣ የወለድ ተመን ስለሚዋዥቅ ነባር ዕዳ ያለባቸው ተበዳሪዎች ዕዳቸውን እንደገና ፋይናንስ ለማድረግ ወይም ለማሸጋገር የሕግ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ከፍተኛ የወለድ ተመኖች የዕዳ አገልግሎት ወጪዎችን ይጨምራሉ፣ ይህም የተበዳሪው ግዴታዎችን የመወጣት ችሎታ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡

የገንዘብ ፖሊሲን ማጥበቅ፣ ብዙ ጊዜ ከፍ ያለ የወለድ ተመኖችን ያስከትላል፣ ይህም የበለጠ ወግ አጥባቂ የብድር አካባቢን ሊፈጥርና ብድር ማግኘትን የበለጠ ፈታኝ ሊያደርገው እንደሚችል ገልጸዋል። ይህም በተለይ ዝቅተኛ የብድር ብቃት በላቸው ተወዳዳሪዎች ላይ ጫና እንደሚያስከትል አስረድተዋል፡፡ 

የተንሳፋፊ ወይም ተለዋዋጭ የወለድ ተመን መኖር በብድር ውሎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የገለጹት ቆስጠንጢኖስ፣ ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ነክ ወለድ ምጣኔውን ሊያሻሽል ወይም ሊጨምር እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ ድንጋጌ በብድር ውሎቻቸው ላይ ሊያስቀምጡ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

የወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ መቀየር ብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን የመምራት ችሎታውን ለማሳደግ የሚያደርገውን ሥልታዊ ዕርምጃ ያመለክታል ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ተበዳሪዎችን፣ አበዳሪዎችንና ባለሀብቶችን ጨምሮ የገበያ ተሳታፊዎች እነዚህን ለውጦች በቅርበት መከታተልና እያደገ ያለውን የፋይናንስ ገጽታ ለመምራት ሥልቶቻቸውን ማስተካከል አለባቸው ብለውም ያምናሉ ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ በዋጋ ግሽበት ቁጥጥርና በኢኮኖሚ ዕድገት መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ በሚፈልግበት ጊዜ፣ በዕዳ ፋይናንስ ግብይቶች ላይ ያለው አንድምታ አደጋዎችንና ዕድሎችን ለመቆጣጠር ንቁና በመረጃ የተደገፈ አካሄድ አስፈላጊነትን ያጎላል፡፡

የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያውም እንደገለጹት፣ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ጠቀሜታ ቢኖረውም ይህንን አሠራር በሚተገበርበት ወቅት የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም የሚመጣ ከሆነ ለዋጋ ንረት መንስዔ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ይህንንም ሲያብራሩም በዚህ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ ወቅት የብርን የመግዛት አቅም የማዳካም ውሳኔ የሚከተል ከሆነ አገሪቱ ባንኮች የገንዘብ ክምችት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ይህም የዋጋ ንረትን ያስከትላል ብለዋል። ስለዚህ እንዲህ ያለውን ነገር እንዴት ማጣጣምና ማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጋት የሚቻለው የሚለው ጉዳይ ትልቅ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ፖሊሲው ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ሁሉም ይስማሙበታል፡፡