አስተያየት

July 14, 2024

በገብሬ ይንቲሶ ደኮ (ፕሮፌሰር)

ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂዎች በክብር እንግድነት ተጋብዤ፣ ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ያስተላለፍኩት መልዕክት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችም ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ።

 በ2016 ዓ.ም. በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዤ መልዕክት ለማስተላለፍ በመቻሌ የተሰማኝን ክብርና ደስታ እየገለጽኩ የተከበራችሁ ተመራቂዎች የልፋታችሁ ዋጋና የስኬታችሁ ማብሰሪያ ለሆነው ምረቃ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ። የዛሬው ደስታ የእናንተ የተመራቂዎች ብቻ ሳይሆን የወላጆችና የቤተሰብ፣ የዘመድና የጓደኛ፣ የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የአገርም ጭምር ስለሆነ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን።

የዩኒቨርሲቲ ምረቃ ቀን የማይረሳ ልዩ ቀን ነው። እኔ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቅሁት የዛሬ 36 ዓመት ቢሆንም የምረቃዬን ቀን እስከ ዛሬ አስታውሳለሁ። በዕለቱ በደስታና በሐዘን የተቀላቀለ ስሜት ውስጥ ነበርኩ። ደስታው የመነጨው ብዙ ችግር አሳልፌ ኮሌጅ በመበጠሴ ነበር። በዚያን ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ሰው ኮሌጅ በጠሰ ይባል ነበር። ያዘንኩት ደግሞ በድህነት የተነሳ በዚያች ልዩ ቀን ደስታዬን የሚጋራ አንድም የቤተሰብ አባል አብሮኝ ባለመኖሩ ነበር። ድህነትን ከቤተሰቤ ለማጥፋት የቆረጥኩት በዚያን ዕለት ነው። ህልሜ ዕውን ሆኖ በእርግጥም ድህነትን ከቤታችን አጠፋሁ። እናንተም አንድ የቤተሰብ ችግር ለመፍታት ወይም አንድ ትንሽ ቁምነገር በሕይወታችሁ ዘመን ለመሥራት ዛሬ ለራሳችሁ ቃል ግቡ። ለቃላችሁ ታማኝ ሆናችሁ ከጣራችሁ ይስካላችኋል፡፡ በውጤቱም ዘመናችሁን ሙሉ ስትደሰቱ ትኖራላችሁ። ፈጣሪ ለዚህ ያብቃችሁ!!

ውድ ተመራቂዎች

ሁላችሁም ለዛሬው ደማቅ የስኬት ማብሰሪያ ቀን እንዲሁ በዋዛ አልደረሳችሁም። የተለያዩ የተማሪ ሕይወት ፈተናዎችን አልፋችኋል። እኔም ደርሶብኝ ስለነበር ችግሮችን አሳምሬ አውቃለሁ። ደብተር መግዣና ሻይ መጠጫ ይቸግራል፣ መጽሐፍ መግዛት የማይታሰብ ይሆናል፣ ፈተና ይከብዳል፣ ውጤት ይቀንሳል፣ ሕመም ያንገላታል፣ ናፍቆት ይጫጫናል፣ በቂ ምግብ ያለማግኘትና ሌሎችም ችግሮች ያጋጥማሉ። እኔ ያኔ ፈተናው ሲደራረብኝ ለስቃይ የተፈጠርኩ ብቸኛ ሰው የሆንኩ ያህል ይሰማኝ ነበር። በዚህ ስሜት ውስጥ ያለፋችሁ ብዙ ትኖራላችሁ።

‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንዲሉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከጎናችሁ የማይጠፉ ሰዎች ደግሞ ይኖራሉ። መረዳዳት አንድ ትልቁ የሚያኮራ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው። በዚህ አጋጣሚ ለተማሪዎች የድጋፍ እጃቸውን ለዘረጉ ሁሉ በተመራቂዎች ስም የከበረ ምስጋና አቀርባለሁ። እናንተም ተመራቂዎች ሥራ ስትይዙና አቅም ስትገነቡ አቅም ላጡ በአጠቃላይና ለችግረኛ ተማሪዎች በተለይ እጃችሁን በመዘርጋት የመረዳዳት ባህላችንን ታስቀጥሉ ዘንድ አደራ እላለሁ።

የዩኒቨርሲቲ ምረቃ በተለይ በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቅ ትልቅ የሕይወት ሽግግር ምዕራፍ ነው። ከምረቃ በኋላ በጣም ወደሚያጓጓ፣ ግን ምንም ወደማታውቁት አዲስ ሕይወት ትገባላችሁ። ሥራ ትይዛላችሁ፣ ትዳር ትመሠርታላችሁ፣ ልጅ ትወልዳላችሁ፣ የዕድር አባል ትሆናላችሁ፣ ሌላም ሌላም። የማያጓጉ ገጠመኞችም ይጠብቃችኋል። ደመወዝ ሳይደርስ ቀለብ ያልቃል፣ የቤት ኪራይ ዋጋ ይጨምራል፣ ልጆች ይታመማሉ፣ ሱሰኛ የትዳር ጓደኛ ያበሳጫል፣ የማይታወቅ አጎት ደውሎ የመታከሚያ ገንዘብ ይጠይቃል፣ ሌላም ሌላም።

እነዚህ ሁሉ ዩኒቨርሲቲ የማትማሩት የሕይወት ዘርፎች ናቸው። ባትማሩም ፈተናው አይቀርላችሁም። ደግነቱ እነዚህን ፈተናዎች በስኬት ለማለፍ የሚረዱ ባህላዊና ሞራላዊ ዕሴቶች አሉ። እነሱም ትዕግሥት፣ አስተዋይነት፣ መልካምነት፣ ሰላማዊነት፣ ሐቀኝነት፣ ታታሪነት፣ መተሳሰብ፣ መከባበር፣ መተማመን፣ መቻቻልና ቅንነት ናቸው። እነዚህን አንድ ላይ ‹ፖዜቲቭ ኢነርጂ› እንላቸዋለን። የእነዚህ ተቃራኒዎች ‹ነጋቲቭ ኢነርጂ› ናቸው። ቀጣይ ሕይወታችሁ የተሳካ የሚሆነው ፖዘቲቭ ኢነርጂ ሲኖራችሁ ብቻ ነው።

ውድ ተመራቂዎች

አገራችን ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ፣ ድንቅ ባህሎች፣ የተፈጥሮ ሀብትና ሰፊ የልማት ተስፋ ያላት ቢሆንም በእኛ ዘመን የተለያዩ ችግሮች እየገጠሟት ይታያል። ድህነትና ግጭት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። እነዚህ ችግሮች በየትውልዱ የቤት ሥራዎች በሚገባ ሳይሠሩ በመቅረቱ የተነሳ ተንከባለው ወደ እናንተ ትውልድ የመጡና ሌላም የተጨማመረባቸው ናቸው። እነዚህ ችግሮች ዛሬም ካልተፈቱ ወደ መጪው ትውልድ ማለትም ወደ ልጆቻችሁ መሻገራቸው አይቀርም። የዛሬውን ትውልድ መጉዳቱ ሳያንስ ጭራሽ በይደር ወደ ልጆቻችሁ የሚሸጋገር አንድም ችግር ሊፈቀድ አይገባም።

ስለዚህ እናንተ የተማራችሁ ወጣቶች አገራችንን አንገት ያስደፉ ከባድ ችግሮችን ለመቅረፍ መዘጋጀት አለባችሁ። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 71 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ30 በታች ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት ማለት ነው። ሊሠራ የሚችል በቂ የሰው ኃይል አላት። የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር በመጨመሩ የተነሳ የተማረ የሰው ኃይል በከፍተኛ ቁጥር ጨምሯል። አገራችን መሬትና ውኃን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች አሏት። እነዚህን በመጠቀም እናንተ በቁጭት ከሠራችሁ ድህነትን መቀነስ ብሎም ማጥፋት ይቻላል። ግጭትና ጦርነት አውዳሚና አክሳሪ መሆናቸውን አውቃችሁ ሌላውን ማሳወቅም ከእንግዲህ የእናንተ ኃላፊነት ነው። ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የልማት መልዕክተኞችና የሰላም አምባሳደሮች በመሆን ታሪክ ለመሥራት ተዘጋጁ።

ውድ ተመራቂዎች

ሁላችሁም ህልም አላችሁ፣ የሆነ ቦታ ለመድረስ ምኞት አላችሁ ወይም ታቅዳላችሁ ብዬ አምናለሁ። ከምኞታችሁ አንዱ ዕውቀታችሁን በከፍተኛ ትምህርት፣ በማንበብና በተግባር ማዳበር መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ያለዕውቀት የሚሳካ ምኞት አይኖርምና። ዕውቀት ትርጉም የሚኖረው ከተመረቃችሁ በኋላ በራሳችሁ ላይ ለውጥ ማሳየት ከቻላችሁ ብቻ ነው። ተመርቃችሁ ወደመጣችሁበት አካባቢ ስትመለሱ የተማረ ሰው ቁመና መያዝ አለባችሁ። ሥራና ገንዘብ ባይኖራችሁ እንኳ አነጋገራችሁ፣ አለባበሳችሁ፣ ንጽህና አጠባበቃችሁ፣ አስተሳሰባችሁና ሥነ ምግባራችሁ መማራችሁን ማንፀባረቅ አለበት።

በመጨረሻ የምመክራችሁ ነገር ቢኖር ነገ የእናንተና የልጆቻችሁ ናትና ለማንም አሳልፋችሁ አትስጡ። ለነገ መደላድል የሚሠራው ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ዛሬ ፍቅር ላይ ሥሩ፣ አብሮነትን አጠናክሩ፣ ለሰላም ዋጋ ክፈሉ፣ ትኩረታችሁ ልማት ላይ ይሁን፣ ከፋፋይ አስተሳሰብና ድርጊት ተጸየፉ፣ ከነጋቲቭ ኢነርጂ ርቀታችሁን ጠብቁ፣ እና ጠባቂ ሳትሆኑ ራሳችሁን ለመቻል በተቻለ መጠን ጥረት አድርጉ።

                                   በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gebred@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡