ዝንቅ‹‹… እንዲያው በአጠቃላይ የጉድ አገር ነሽ››

ቀን: July 14, 2024

በአንድ ወቅት ነቢይ መኰንን ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ነበር። ከአንዲት ደቡብ አፍሪካዊት ጋር ጨዋታ ይጀምራሉ፦

“ከየት ነህ?”

“ከኢትዮጵያ”

“ኦ! ዳኛቸው ወርቁ ደህና ነው?”

“ዳኛቸው አርፏል። ካረፈ ሁለት አመቱ”

“ያሳዝናል። ድንቅ ደራሲ ነበር”

“አዎ ታላቅ ደራሲ ነበር”

“ታዲያ ሌሎች የኢትዮጵያ ደራሲዎች እየጻፉ ነው?”

“አዝናለሁ። እየጻፉ አይደለም”

ምነው? ለምን?”

“ውዥንብር ውስጥ ናቸው”

“ታዲያ ለምን ውዥንብራቸውን አይጽፉትም?”

***

ነቢይ ማዕከላዊ እያለ ነው። ከበላይ አንድ ትእዛዝ መጣ። የኢትዮጵያን ችግር እያንዳንዳችሁ በስድስት ገጽ ዘርዝራችሁ ጻፉ። ወረቀትና ብዕር ታደለ። ሁሉም አእምሯቸውን ጨምቀው ብዕርና ወረቀት ለማግኘት ታተሩ። ነቢይ ብቻ ዝም ብሎ ተቀምጧል።

“አንተ ለምንድነው የማትጽፈው?”

“እኔ ስድስት ገጽ አልፈልግም። በሁለት መስመር የኢትዮጵያን ችግር መግለጽ እችላለሁ”

ሁሉም የነቢይን ግጥም ለመስማት አቆበቆቡ። ነቢይ ለሁሉም እንዲሰማ ጮክ ብሎ እንዲህ አለ፦

“እንኳንስ ስድስት ገጽ መቶ ገጽ ማይበቃሽ

እንዲያው በአጠቃላይ የጉድ አገር ነሽ”

***

ነቢይ ከመንግሥቱ ለማ ጋር አንድ ሁለት እያሉ ነው። መንግሥቱ ለነቢይ እንደ መምህር mentor ነበሩ። ሁለቱ እየተጨዋወቱ እያለ አንድ ሰው ወደ ግሮሰሪው ሲዘልቅ መንግሥቱ ለማን ሰላም አላቸው። መንግሥቱ ለማ ግን ነገሬም አላሉት። ወደ ጨዋታቸው ተመለሱ።

ሰውዬው በደንብ ከጠጣ በኋላ ተደፋፈረና ተመልሶ ወደ እነ መንግሥቱ መጣ።

“ጋሽ መንግሥቱ አውቀውኛል ግን? ያወቁኝ አልመሰለኝም”

መንግሥቱ ለማ ጥያቄውን ችላ ብለው

“Is imperialism still digging its own grave?” አሉት። ይኼኔ ሰውዬው ልክ እንደ ውሻ ጭራውን ሸጉቦ ድራሹ ጠፋ። ከፊታቸው ዘወር አለ። ይሄኔ ነቢይ

“አልገባኝም” አላቸው።

“አየህ” አሉት መንግሥቱ “ይሄ ግለሰብ ካድሬ ነበር። ኢምፔሪያሊዝም ይውደም እያለ መፈክር የሚያስፈክር። ግን ካድሬነቱ ተገፍፎ እስር ቤት ወርዶ ተፈትቶ ከዛ ኢምፔሪያሊስት ናት ወደሚሉት አሜሪካ ደርሶ የመጣ ሰው ነው። ለዚያ ነው is imperialism digging its own grave ስለው ቃል ሳይመልስ ወጥቶ የሄደው”፡፡

ይህ የመጨረሻው ጨዋታ ውስጥ ነቢይ የለበትም። ነገር ግን ነቢይ ነጭ ጥቁር ግራጫ በተሰኘ የግጥም መድበሉ መግቢያ ላይ አካትቶታል። የመንግሥቱ ለማ ሌላ ጨዋታ ነው። አንድ የደርግ ባለሥልጣን መንግሥቱ ለማን በአንድ ጉዳይ እንዲጽፉ ያዛቸዋል። መንግሥቱ አሻፈረኝ እምቢ አሉ። አያችሁ እውነተኛ ደራሲ ውስጡ ፈንቅሎት እንጂ በትእዛዝ አይጽፍም። ኋላ ባለሥልጣኑ ማስፈራራት ጀመሩ፦

“አልጽፍም ካልክ ምን እንደሚከተልህ ታውቃለህ?”

“ምን ይመጣል?”

“ትታሰራለህ ትገረፋለህ”

“ያኔማ እጽፋለሁ። ስለሚያመኝ እጽፋለሁ”

አያችሁ እውነተኛ ድርሰት፣ ሐቀኛ ጥበብ የሚመነጨው ከሕመም ነው”

– ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው በገጹ እንደከተበው