JULY 14, 2024

ናታን ዳዊት

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ በሒደት እንደሚያቆም በግልጽ ከማስታወቁም ባሻገር ይህንኑ ለማስፈጸም እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች ወደሚፈለገው ግብ እያደረሱት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ድጎማውን እየቀነሰ ሙሉ በሙሉ ለማቆም ቀነ ገደብ በማስቀመጥ በዚሁ መሠረት እየሠራም ነው፡፡ ከዚህ ውሳኔው ጋር በተያያዘ የወሰደችው ዕርምጃዎች በየዓመቱ ለድጎማ ያወጣ የነበረውን ቢሊዮን ብሮች ሊያድን ችሏል፡፡ በሌላ አነጋገር መንግሥት ለድጎማ ያወጣ የነበረውን ገንዘብ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪ ባለቤቶችና ሕዝቡ እንዲከፋፈልና የመንግሥትን ጫና እንዲቀንስ አድርጓል፡፡

እንዲህ ባለው አካሄድ መንግሥት ከድጎማ ሲወጣ የአገር ውስጥ የነዳጅ ግብይት ዓለም አቀፉን ዋጋ መሠረት ያደረገ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ለነዳጅ የሚደጉመው ድጎማ ይቆማል፡፡ የዓለም ዋጋ ሲጨምር ይጨምራል፡፡ ከቀነሰም ቅናሹን አስልቶ በአገር ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋን ቀንሶ በመወሰን  ግብይቱ ይከናወናል እንደማለት ነው፡፡ ከድጎማ ወጥቶ ገበያን መሠረት ወዳደረገ የግብይት ሥርዓት ሲሸጋገር በዚያው ልክ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች ይመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ ለዋጋ ጭማሪ ወይም ለዋጋ ንረት እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በመሆኑ የነዳጅ ሽያጭ ገበያን መሠረት ወዳደረገ ሥርዓት የሚገባ ከሆነ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የሚባሉ አሠራሮችን መተግበር የግድ ይላል፡፡ በየትኛውም ግብይት ውስጥ ዋጋ ከፍና ዝቅ እያለ ግብይቶቹን ወደ ማካሄድ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እንደለመድነው ነዳጅ ስለጨመረ በምርትና ሸቀጦች ላይ ዋጋ በመጨመር የሚደረግ አሠራር በጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ያመላክታል፡፡ በትክክል የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን አስልቶ ዋጋን የማስተካከል አሠራር በመለማመድ መተግበርንም ይጠይቃል፡፡ የዋጋ ተመንና የትርፍ ህዳግ ምጣኔ በዘፈቀደ በሚካሄድበት አገር ኢኮኖሚያዊ የዋጋ ማስተካከያና የተመጠነ ትርፍ ይዞ መሥራት ከባድ ሊሆን ቢችልም የግድ መፈጸም አለበት። 

ከባህላዊ አሠራርና ከዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ ወጥቶ በአግባቡ በውድድር እንድንሠራ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች እየመጡ በመሆናቸው ለዚህ ራስን ማዘጋጀት ተገቢ ይሆናል፡፡ እንደ ቀድሞ በነዳጅ ጭማሪም ሆነ በሌላ ምክንያት የተደረገ የዋጋ ጭማሪ (ያውም ኢኮኖሚያዊ ያልሆነ) የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ በምርትና አገልግሎቶች ላይ ይህ ቅናሽ ሊታይ ይገባል፡፡ በአንድ ወቅት ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሆነ ጊዜያዊ ክስተት መቀረፉ አይቀርምና ይህም ችግር ካለፈ በኋላ በዚያው ዋጋ ከመሸጥ መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ የተሰቀለ ዋጋ አይወርድም እየተባለ መቀጠል እንዳይቀጥልና ሸማቹ የበለጠ እንዳይጎዳ የሚከለክል አሠራር ማበጀትም ያስፈልጋል፡፡ 

በአጠቃላይ መጪው ጊዜ የነዳጅ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ግብይቶችና አገልግሎቶች ውስጥ ገበያን መሠረት ያደረጉ ኢኮኖሚያዊ የዋጋ ማስተካከያዎችን በማድረግ መሥራትን የሚጠይቁ በመሆናቸው የቢዝነስ ባህላችንም ከዚሁ አንፃር ሊቃኙ ይገባል፡፡ የዲጂታል መታወቂያ፣ የዲጂታል ግብይት ሥርዓትና መሰል አዳዲስ አሠራሮች በሙሉ ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈን ብቻ ሳይሆን ገበያን ለማረጋጋት ጭምር አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ በየትኛውም ዘርፍ ከመጡትና እየመጡ ካሉ አሠራሮች ጋር ራስን አለማምዶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡   

ለዚህ ደግሞ ነዳጅ በዓለም ዋጋን ባገናዘበ መልኩ ግብይቱ የሚፈጸም ከሆነ መንግሥትም ይህንን ከፍተኛ የአገር ሀብት የሚፈስበት ምርት በትክክል በማቅረብ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የሚኖረውን ትክክለኛ ዋጋ በማስላት ያልተቋረጠ አገልግሎት ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ ነዳጅን አልደጉምም ካለና የምሸጠውም በዓለም ዋጋ ነው ካለ ወደ እሱም ሆነ ወደ ኅብረተሰቡ የሚተላለፍ ነገር ሳይኖር የወቅቱን ዋጋ በማስላት ግብይት እንዲፈጸም ለማድረግ ደግሞ ከድጎማው ሙሉ ለሙሉ እስኪወጣ መጠበቅ የለበትም፡፡ ከአሁኑ መዘጋጀት አለበት፡፡ ብቁ ባለሙያዎችና ቴክኖሎጂዎችንም መታጠቅ ያስፈልጋል፡፡ ሀብቱ እንዳይባክን በአግባቡ መቆጣጠር እንደተጠበቀ ሆኖ ግብይቱ እንዲፈጸም ማድረግም ከዚህ በኋላ ትልቁ ሥራው ሊሆን ይሆገባል፡፡ 

አሁን ባለንበት ሁኔታም ቢሆን የነዳጅ ዋጋ ትመናና ትግበራ ብዙ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡ አንድ ሊር ቤንዚን 82 ብር ከ60 ሳንቲም ሆኗል፡፡ የነጭ ናፍጣ የአንድ ሊትር መሸጫ ዋጋ 83.74 ብር ሆኗል፡፡ ይህ በሊትር ከሦስት ብር በላይ ጭማሪ መደረጉን ያመለክታል፡፡ ሙሉ በሙሉ መንግሥት ከድጎማ ይወጣል ተብሎ በሚጠበቅባቸው ቀሪ ሁለት ዓመታት ውስጥ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ከሄደ እንዲህ ያለው ጭማሪ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ 

ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ ተፅዕኖ የሚያሳርፍባቸው ግብይቶች አላስፈላጊ በሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች እንዳይታመሙ በተለይ የነዳጅ ዋጋን ተከትሎ የሚፈጠሩ ለውጦች በአግባቡ እንዲፈጸሙ መረጃው በአግባቡና በቶሎ መገለጽ ይኖርበታል፡፡ ይህ ዘግይቶ የሚተገበር ታሪፍ በመሀል ላይ አገልግሎቱን የሚሰጡ የትራንስፖርት ድርጅቶች ወይም ታክሲዎች በዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ ኅብረተሰቡን ሲጫኑ ታይቷል፡፡ 

አሁን ባለው ሁኔታም ሆነ ወደፊት በዓለም የነዳጅ ተመን መሠረት በየጊዜው ከፍና ዝቅ ሊል የሚችለውን የነዳጅ ዋጋ ተከትሎ ፈጣን የትራንስፖርት ዋጋ ተመንን ማስታወቅ ይጠይቃል፡፡ 

በተወሰኑ ወራት ልዩነቶች የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ እየተደረገ ባለበት ወቅት ሲታዩ የነበሩ ችግሮች ከወዲሁ እየታረሙና እየተስተካከሉ ካልሄዱ ነገ ዋጋ ከፍና ዝቅ ይሚልባቸው አጋጣሚዎች ሊበዙ የሚችሉ ከሆነ በዚያው ልክ በፍጥነት የነዳጅ የመሸጫ ዋጋን ብቻ ሳይሆን እንደ ትራንስፖርት ያሉ ታሪፎችን በወቅቱ የነዳጅ ዋጋ መሠረት አሥልቶ ማስታወቅ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ ሊሆን ያግዛልና እዚህ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፡፡