ተሟገት የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

ቀን: July 14, 2024

በገነት ዓለሙ

የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት ዓመት መባቻ ዋዜማ ላይ ሰኔ መጨረሻ ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ‹‹የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት (ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም.)›› በዝርዝርና ‹‹በአንኳር ጉዳዮች›› መልክ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህም ጋር በሕግ ጭምር እንደ አዲስ ከመደራጀትና ነፍስ የመዝራት ለውጥና ተሃድሶ ውስጥ ከመግባት፣ እንዲሁም ለይስሙላና ለመንግሥት ‹‹ስም መጠሪያ›› የተሰፋ ቁና ከመሆን ይልቅ፣ አገር የሚታወቅበት/የሚኮራበት የዓለም አቀፍ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች መሥፈርታችን (Paris Principles for Human Rights) ከማሟላት ጋር ኢሰመኮ ያለፉትን የአምስት ዓመታት ጉዞ የቀን ሪፖርትም አቅርቧል፡፡ ይህ ‹‹የኢሰመኮ የ5 ዓመት ጉዞ›› ሪፖርት ራሱ የአዲሱ መንግሥታዊ የሰብዓዊ መብቶች ብሔራዊ ተቋም የተለየ፣ አዲስ ዓይነት የሪፖርት አቀራረብና የሪፖርቶች አጭር ታሪክ ነው፡፡ እነዚህ ሪፖርቶች የአሁኑ የሰኔ 2016 ዓ.ም. ሪፖርት በግልጽና ሆን ብሎ አጉልቶ እንደሚለው ‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ›› ወይም የቀረበ ብቻ ሳይሆን፣

‹‹ኢሰመኮ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላክ፣ እንዲሁም ለሕዝብ ይፋ መደረግ መጀመሩ፣ በዚህም ሁለት ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ…››

ሪፖርቶች ናቸው፡፡ ይፋ የተደረጉ ሪፖርቶች ናቸው፡፡ የብቻ የቀደመው ኢሰመኮ ከድኅረ 2012 ዓ.ም. አዋጅ ኢሰመኮ የሚለየው አንደኛው ምልክት ነው፡፡

ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰኔ 2016 ዓ.ም. የኢሰመኮ አምስት ዓመታት ጉዞም ሆነ (ኢሰመኮ ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም. ያስመዘገበው ውጤቶች አጭር ገለጻ) የዘመኑ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት (ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም.) እነዚህ ሁለቱ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ ከምን ጋር እንደገጠሙ/እንደተገጣጠሙ ሊሰወርብን አይገባም፡፡ ሁለተኛውን ሌላ የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን በገዛ ፈቃዱ አልቀጥልም ያለ ዋና ኮሚሽነር ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመበትና ይህም ሪፖርት ብቻ ሳይሆን ዋና፣ ምናልባትም ሰበር ዜና የሆነበትም አጋጣሚ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? ሊብራራ የሚገባው ግራ ቀኙን አገላብጦ ያየ ማብራሪያም ግምገማም የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ በሕግ የተደነገጉ የተወሰኑ የሥራ መደቦች የሁለት የሥራ ዘመን ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ተሿሚው ከኃላፊነት የሚነሳበትን ሥነ ሥርዓት የሚደነግገውን ሕግ ሳይጨምር ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የእኛው አገር የ1987 ዓ.ም. (አሁን ሥራ ላይ ያለው) ሕገ መንግሥት የዚህን የሥራ መደብ/የሥልጣን ቦታ) በሁለት ዓመታት የሥራ ዘመን የወሰነበት ምክንያትና አግባብ የሚገርምና አስቂኝም ትርጉም የለሽም ነው እንጂ፣ የኢትዮጵያ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሥራ ዘመን ሁለት ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ለሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዚዳንትነት ሊመረጥ አይችልም (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 70/4 ይላልና፡፡ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኦዲተር ጄኔራል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ተሿሚዎች/ዋና ተሿሚዎች የሥራ ዘመን አምስት ወይም ስድስት ዓመት ነው፡፡ ለአንድ ተጨማሪ የሥራ ዘመን እንደገና ሊሾሙ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ሕግ እንደሚደነግገው ‹‹…የመጀመሪያው የሥራ ዘመኑ ባለቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የትኛውንም የሥራ አመራር ቦርድ አባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ… በድጋሚ ሊያሾም ይችላል››፡፡ ይላል፡፡

እና እንዲህ ያለ የሥራ ዘመኑ ለዚህን ያህል ዓመትና ለዚህን ያህል ቁጥር ተብሎ የተገደበ ሹመት/ምርጫ በደላው፣ ዴሞክራሲን ባደላደለ፣ እኩልነትን ባሕርይው ባደረገ አገር/ኅብረተሰብ ውስጥ የሁለቱን ወገን ፈቃደኝነት ነፃነት ይፈልጋል፡፡ ‹‹አሠሪ››ው፣ ‹‹…‹‹በድጋሚ ሊያሾመው›› አለዚያም በቃኝ ሊለው ይችላል ብቻ ሳይሆን፣ ሠራተኛው ወይም ሿሚው ወይም ተመራጩ አንድም በዚሁ በቃኝ አለዚያም ለሁለተኛው የሥራ ዘመን አወዳደራለሁ ማለት መብቱ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ አሠሪና ሠራተኛ፣ ሿሚና ተሿሚ፣ ቀጣሪና ተቀጣሪ የኮንትራት የውል ሕጉ እንደሚለው፣ እኩል/እኩያ ባልሆኑበት በገኃዱ ዓለም በፈረንጅ ቋንቋ እንደሚባለው ‹‹Making the conscious decision not to run for at second term›› ማለትም በዕውቀት፣ በንቃትና በግንዛቤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነፃ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሁለተኛው የሥራ ዘመን ግን ይብቃን ውሳኔ የትም ቦታና በየትኛውም ደረጃ ብርቅና ድንቅ ነው፡፡

ይህንን የምንነጋገርበትን ጉዳይ ‹‹ለማድነቅ›› ይረዳን፣ እንዲሁ ቀደም ሲል በምሳሌነት የጠቀስኩትን የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት በሁለት ጊዜ ብቻ የተገደበውን የስድስት ዓመት የሥራ ዘመን ‹‹አፈጻጸም›› ታሪክ ውስጥ አንዳንድ የሚገርሙ ኢትዮጵያን የገጠሙ ጉዳዮችን እንመልከት፡፡ ከዚህ በላይ እንዳልኩት ይህ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የሌለውን ሲበዛና ምናልባትም በብቸኝነት ‹‹የወግ የማዕረግና የክብር›› ብቻ የሆነውን የሥልጣን ቦታ ሹመት ለምን በጊዜ ገደብ መወሰን አስፈለገ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ነው፡፡

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ (ሁለተኛው) ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ከኢፌዴሪ ምሥረታ ከነሐሴ 1987 ጀምሮ የመጀመሪያውን የስድስት ዓመት የሥራ ጊዜ እስከ 1993 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ዘለቁ፡፡ 1993 ዓ.ም. ደግሞ በገዥው ግንባር በተለይም ከሁሉም በላይ በሆነው በሕወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል የመንግሥት ሥልጣንን፣ ሕግ የማውጣት የመንግሥት ሥልጣንን ጭምር ተቃዋሚ ማጥቂያ፣ የፖለቲካ ዱላ ማድረግን የተለመደ አሠራር ገኃድና ግላጭ አወጣው፡፡ 1994 ዓ.ም. መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ላይ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ እንደገና መሾም ይፈቅዱ እንደሆን፣ አለዚያም ሿሚው ይህንን ይፈልግ እንደሆነ በጨዋ ደንብ የሚለይበት ጊዜ ሲመጣ በዕለቱ ያየነውና ነጋሪት ጋዜጣን በመሰለ ኦፊሺያል ሰነድ የተመዘገበው የተመሰከረው የመንግሥት ሥልጣን እንዴት ይሉኝታ ቢስ ሆኖ፣ ልጓም አጥቶ፣ መረን ለቆ፣ አፍጥጦና አግጥጦ የፖለቲካ መሣሪያ እንደሚሆን ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 የሚዘልቅ ጊዜ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በየዓመቱ ሥራውን የሚጀምረው የፌዴራሉ መንግሥት ሁለቱም ምክር ቤቶች (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት) በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ከተከፈቱ በኋላ ነው፡፡ የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ስምንተኛ ዓመት ቁጥር አንድ (አዲስ አበባ መስከረም 28 ቀን 1994) አዋጅ ቁጥር 255/1994ን የለፈፈ/ያወጀ የሕግ መንገሪያ ኦፊሺያል ጋዜጣ ነው፡፡ የዚህ አዋጅ ስያሜ ወይም አጭር ርዕስ ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅ›› ነው፡፡ አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ በአዋጅ አንቀጽ 15 ከመስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ፊርማ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ይላል፡፡ የ1994 ዓ.ም. የመስከረም ወር አራት ሰኞዎች ነበሩት፡፡ መስከረም 7፣ 14፣ 21 እና 28 የዋሉት፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጀመሪያ በፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ሁለቱም የፌዴራል ምክር ቤቶች መከፈታቸው ከተበሰረ/ከታወጀ በኋላ ሥራውን የሚጀምርበት የመጀመሪያው ቀን፣ ማለት የመስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ (መስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም.) ግን አዲስ ፕሬዚዳንት አሳወቀ፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በዚያው ዕለት የፈረሙበት አዲስ አዋጅ አወጣ፡፡ ድንገት የአዲሱ ፕሬዚዳንት አሰያየምና የአዲሱ አዋጅ አወጣጥ ፍጥነት አይደንቀን ይሆናል፡፡ የአዲሱ አዋጅ ይዘት ግን የሚገርም፣ የፍትሕ ሕዋስ ላለው አገር ደግሞ የሚከነክን፣ የሚቆረቁርና የሚያቃጥል፣ የሚያንገበግብ ነው፡፡ የአዋጁ ርዕስ ራሱ እንደሚናገረው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅ ነው፡፡ መግቢያው እንደሚያረጋግጠውም የአዋጁ መውጣት አስፈላጊነት ‹‹የፌዴራሉን ፕሬዚዳንታዊ ተቋም ሕገ መንግሥታዊ አቋም ለማጠናከርና የቀድሞ ፕሬዚዳንት የሥራ ዘመኑ ካለቀ በኋላ ያገለገለበትን ዘመን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊጠበቁለት የሚገባቸውን መብቶችና ጥቅሞች ማስከበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ›› ነው፡፡ በአጠቃላይና በአጭሩ ከአዋጁ አራት ክፍሎች ውስጥ ሁለቱ በብቸኝነት እንደሚወስኑት አዋጁ ‹‹የቀድሞ ፕሬዚዳንት›› አዋጅ ነው፣ ‹‹የቀድሞ ፕሬዚዳንትነት መብቶች ስለማቋረጥ›› ሕግ ነው፡፡

ክርክሬና ጭብጤ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችንም ሆነ ሌሎች የቀድሞ የአገር ሹማምንትን መብትና ጥቅም የሚጠብቅ ሕግ ለምን ይወጣል አይደለም፡፡ እንዲያውም በአንፃራዊነት በደህና ጊዜ የወጣው የኢፌዴሪ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ (ቁጥር 131/91) ይህንን አስቀድሞ ባለመደንገጉ የሚወቀስ ነው፡፡ ከጊዜ በኋላ እጅግ በጣም ዘግይቶ በ2001 ዓ.ም. የወጣውና የተነጋገርንበትን፣ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅን ጭምር የሻረው ከኃላፊነት የተነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ወዘተ መብቶችና ጥቅሞች አዋጅ አስፈላጊነትም የሚያሳየው የዚህን አስፈላጊነት ነው፡፡ የአገርንና የማንንም የፍትሕ ሕዋስ የሚያሽፍተው የአንድን ሰው ሁለተኛ የሥራ ዘመን አስቦ፣ አንድን ነጠላ ግለሰብ ጉዳዬ ብሎ፣ ይህንን ግለሰብና ፖለቲካውን ጠላቴ ብሎ ሕግ ማውጣት ነው፡፡ አዋጁ እስከ ዕለተ ሞታቸው መዳረሻ ድረስ እያሳደደ የተከተላቸው፣ የሕጉ አፈጻጸም በተነሳና በታወሰ፣ ባጋጠመ ቁጥር ሕጉ የነጋሶ አዋጅ ይባል የነበረውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በምሳሌነት ባነሳነው የሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጉዳይ ውስጥ እያለን አሁንም የአጠቃላይ የተቋም ግንባታው አካል ተደርጎ መወሰድና መርሁና አቅጣጫው ብቻ ሳይሆን ነቂስ ዝርዝሩ ሁሉ የታወቀ ሆኖ መንደፍ፣ በሕግና ደንብ መወሰን ያለበት ገና ያልቀና (አንቻርትድ) መንገድ አለ፡፡ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንቶች መካከል እስካሁን ሁለቱን የስድስት ዓመት የሥራ ዘመን ያጠናቀቁት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ሙላቱ ተሾመን የአንድ ተርም (የአንድ የሥራ ዘመን) ብቻ ፕሬዚዳንት ያደረጋቸው ለውጡ/ሪፎርሙ ነው? ወይስ አሁንም ተድበስብሶ ቢቀር የማይቆጨን የእሳቸው በፈቃደኝነት አልፈልግም ማለት ወይስ መንግሥት አልፈልጋቸውም ብሎ፡፡ እንዲህ ያለ መመለስ የማይቻል ጥያቄ፣ ጥርጣሬ ጭብጥ ይዞ መኖር ለፖለቲካች ጤና ጥሩ አይደለም፡፡

ፖለቲካችን ይህንን ሁሉ ማጥራት፣ ይህንንም ዓይነት ‹‹የኮሪደር ልማት›› መሥራት አለበት፡፡ አራተኛው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያው የስድስት ዓመት የሥራ ዘመን መገባደጃ ጊዜ ውስጥ ናቸው፡፡ ይህንን ስጽፍ አምስት ዓመት ከ260 ቀናት ገደማ ላይ ናቸው፡፡ ሁለተኛው የፕሬዚዳንቷ የሥራ ዘመን የሚጀምረው እንደ እኔ ሥሌት ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ያኔ ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› ውስጥ እንዳንገባ፣ እንዳንዝረከረክ፣ ማፈሪያና የሰው መሳቂያ እንዳንሆን የአሠራሩን ሥነ ሥርዓትና ቅደም ተከተል ጥርት አድርጎ መንደፍና በሥፍራውና በቦታው ማስቀመጥ ትልቅና ትንሽ ጉዳይ ሳይባል የተቋም ግንባታ ሥራ ነው (በነገራችን ላይ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. አሜሪካ በጆ ባይደንና በዶናልድ ትራምፕ መካከል በተደረገው የምርጫ ክርክር ውስጥ የታየው ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት የጤና ሁኔታ ያስከተለው ቀውስ አሜሪካን በመሰለ የ250 ዓመት (ሁለት ፈሪ ዴሞክራሲ እንኳን ‹‹ክፍተት›› መኖሩን እያሳየን ነው፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት በገዛ ፈቃዳቸው ዕጩነታቸውን አልፈልግም ብለው ከውድድር ካልወጡ፣ አሜሪካን የመሰለ ዴሞክራሲ እንኳን ሌላ መላ አጥቶ፣ ሌላ ሃይ ባይና ከልካይ ጠፍቶ ጉዳዩ በራሱ በዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥና እሱ ፈቃድ ላይ እየተትረከረከ ነው፡፡ ይህ ግን ለእኛ ለኢትዮጵያ መፅናኛ ሊሆን አይገባም፡፡ ገለልተኛ ተቋም የመገንባት ዋና ሥራችን ይህንን ሁሉ ከቁጥር ማስገባት፣ እያንዳንዱን መረማመጃችንን፣ የእግር መገዳችንንና የዓይን ብርሃናችንን ይበልጥ ማልማት አለብን)፡፡

ይህንን ሁሉ ለማንሳት መነሻና ምክንያት ወደ ሆነን ወደ ኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በአንድ የሥራ ዘመን ብቻ ስለተወሰነ ጉዳዬና ያንን የመሰለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በቀረበበት፣ ሪፖርቱም የያዛቸውና ያካተታቸው ነገሮች ከፍተኛ ዜና በሆኑበት፣ ማዕቀፍና ዓውድ ውስጥ ራሱን የቻለ ዜና ስለሆነው ጉዳይ እንመለስ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ሪፖርት ከተደረገባቸው ጉዳዮችና ቁም ነገሮች በላይ ትኩረት እንድሰጥ ያደረገኝ እዚያው ላይ ከፍ ብዬ እንዳልኩት ‹‹ሁለተኛውን ሌላ የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን በገዛ ፈቃዱ አልቀጥልም ያለ ዋና ኮሚሽነር ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመበትና›› ይህም ራሱ ዜና የሆነበት ያልኩት ነገር ነው፡፡ አዎ፣ ይህንንም ግምት ወይም መደምደሚያ መጠየቅ፣ መሞገት ይቻላል፣ ይገባልም፡፡

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያልተጠበቀና ድንገተኛ በሕመም ምክንያት የሥራ መልቀቂያ ማቅረብ ብዥታ ፈጥሯል፡፡ ለውጡን የመቃወም ተቃውሞውን የማገዝ፣ የመደገፍ ዓይነት ነገር ሆኖ ሲመነዘር/ሲተረጎም ተሰምቷል፡፡ የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊም ከሥራቸው የመልቀቅ/የመሰናበት ወሬም ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ ጥርት ብሎ አልተነገረም፡፡ ኢትዮጵያ በምትገኝበት የተጣመደ ፖለቲካ ውስጥ ብርቱካን ሚደቅሳና መዓዛ አሸናፊ ብቻ ሳይሆኑ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስም (እስከ ጥር 2015 ዓ.ም. መጀመሪያ ድረስ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር ሆነው የሠሩት፣ አሁን በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬተሪያት ውስጥ የሚሠሩት) የዓብይ መንግሥት መጀመሪያ ያሰባሰበው ድጋፍ በዚህ ዘርፍና መልክም የእምቧይ ካብ እንደሆነ መከራከሪያ ሲሆን፣ ሦስቱ ምሳሌዎች ይህንን በመሰለ የፖለቲካ አቋም በያዘ ተቃውሞ ውስጥ ሲጠቀሱ እንሰማለን፡፡ እነዚህ የተጠቀሱትን ተሿሚዎች የሚመለከተው ነገር በላ ልበልሃ ውስጥ የመግባቱ ችግር ምንጭ የታወቀው የመንግሥት ዝምታ፣ ድብስብስነት መሆኑ፣ ይህንን የሚመክት የአሠራር ግልጽነት ባህል አለመዳበሩ መሆኑ አያከራክርም፡፡

የአሁኑን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የዳንኤልን (ዶ/ር) ጉዳይ ግን የእነዚህን የተጠቀሱትን ሰዎች ነገር ባድበሰበሰው፣ በመሳጠረው ጉዳይ ውስጥ አንድ ላይ ማደባለቅ አይቻልም፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ ዳንኤል (ዶ/ር) መጨረሻ ሰኔ 2016 ዓ.ም. መሰናበቻ ላይ የገለጹልንን፣ ሥራቸውን ሲጀምሩ፣ የኮሚሽነርነቱን ሹመት እንዲቀበሉ እነሆ ሲባሉ፣ እሳቸውም ይሁን ብለው የመጀመሪያ ደረጃ መልስ ሲሰጡ፣ በኋላ ሲሾሙ፣ የሥራ ውላቸው ውስጥ የሥራ ውል የሥራ ዘመን የመጀመሪያው አምስት ዓመት ብቻ ይሆናል የሚል ሆኖ ስለመቆረጡ፣ በሌላ አነጋገር የመጀመሪው የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ካበቃ በኋላ እንደገና የመራዘሙ ነገር በስምምነት ዝግ ስለመሆኑ የሰማነው ነገር የለም፡፡ እንኳንስ ከመንግሥት ከእሳቸውም ለምን ይህንን በይፋ አልሰማንም ብለን የመቀናጣት/የመዘባነን ባህልም ገና የለንም፡፡ ይህ ሁሉ የሥራ ውሉ ሲመሠረት፣ ሹመቱ ሲፀድቅ ለምን እውነቱ በሙሉ፣ ሁሉም እውነት አልተነገረንም ማለት ወይም እንደሚባለው ‹‹Full Disclosure›› መጠየቅ ነውርም ጥጋብም ባይሆንም፣ ይህ ባህል ግን መለመድ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ 

ዳንኤል (ዶ/ር) የሹመቱ የሥራ ዘመን ለመጀመሪያው አምስት ዓመት ብቻ የተወሰነበትን በእሳቸው በራሳቸው አነሳሽነት የቀረበውን ምክንያት ያው አሁን ነግረነውናል፡፡ እኛም፣ ይህ ጽሑፍ ራሱ ደጋግሞ የሚያነሳውን የሚብከነከንበትን የተቋም ግንባታ ተገን መሠረት ያደረገ አቋምና ምክንያት ነው፡፡ ይህ ምክንያት ጥርጣሬ ከል ባይሆንም፣ ጥርጣሬያችንን ሁሉ የሚያስወገድ ባይሆንም ውሸት ግን አይደለም፡፡ ዳንኤል (ዶ/ር) በጥቂቱም ቢሆን እንደሰማነው የኒውዮርክ ሥራቸውን ለቀው የመጡት እስኪ ለአንድ የሥራ ዘመን ልየው ብለው ነው ብለን እዚያው ‹‹ቦታችን›› ብንመለስ እንኳን፣ ይህም ራሱ ቀላል ግዳጅ አይደለም፡፡ አምስት ዓመቱ ባስተናገደው ውጣ ውረድ ውስጥ ለዚያው የሰብዓዊ መብቶች መከራና ጣጣ ውስጥ በመሀሉ ‹‹ሳስበው ሳስበው ደከመኝና ተውኩት›› አላሉም፡፡ መንግሥት ራሱስ ‹‹ገፍቷቸው፣ በቃህ ብሏቸው ይሆን ብሎ መጠርጠርም ትክክለኛውን ምላሽ ለማፈላለግም መጣርም የአባት ነው (የእናትም ጭምር)፡፡ ይህንን ጥርጣሬ ቀጥልበት ብቻ ሳይሆን በእሱ ብቻ ይሁንብህ የሚሉ እንዲያውም ይህንኑ ብቻ አምነውና አምልከው የሚያስቀምጡ ብዙ ሰበቦች፣ ወሬዎች አሉ፡፡

መንግሥት ኢሰመኮ ሪፖርቶች ላይ ሁሉ ደስተኛ አለመሆኑ አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት ሚዲያዎች፣ ከዚያም በላይ ደግሞ የመንግሥት ደጋፊነት ጋር የተያያዙ ሚዲያዎች በኢሰመኮ ሪፖርቶች/ወይም የእሱ ሪፖርት ገደፋቸው፣ አለፋቸው በሚላቸው ጉዳዮች ምክንያትና ሰበብ ኢሰመኮ ላይ የሚሰነዘረው የማይናቅ ጣል ጣል የማድረጊያ ብቻ ሳይሆን፣ የጥላቻ አስተያየት ወደ እዚህ መከራከሪያ (መንግሥት ሂድ አለው፣ ልቀቅ አለው) ሲገፈትር ይታያል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ቅራሚ ግንዛቤን ይዞ ያዙኝ ልቀቁን ማለት እንጂ፣ ሊጡን ሐሳብ የበሰለ ትኩስ ኬክ አድርጎ ማቅረብ እንጂ እውነትና ማስረጃን ተከትሎ ሀቁን ማፈላለግ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን፣ በአጠቃይ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ተቋማትን እንደገና በአዲስ ለውጥና ሽግግር ጉዞ ውስጥ የምትፀንስበት፣ የምትወልድበት፣ ወልዳ አሳድጋም ለወግ ማዕረግ ለማድረስ የተከተለችው አሠራርና ጎዳና ከእነ ውጣ ውረዱ፣ ከእነ ደፋ ቀናውና ከእነ መንገራገጩ፣ ወዘተ የዳንኤል በቀለና የባልደረቦች፣ እንዲሁም የመላው የተቋሙ ሠራተኞች የተከተሉት መሆኑ፣ ይህም ችግሮችን፣ ስህተቶችንና ጥፋቶችን እያስወገደ ሊከተሉት የሚገባ የአገር ኩራት፣ የአገር መታፈሪያ ምልክት ሆኖ መቀጠል ያለበት ይመስለኛል፡፡

ስለሥራው ይዘት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ፣ ከዚያም ይልቅ ስለአመራሩ የሥልጣን ዘመን አንስተን፣ በስፋት የተነጋገርንበት፣ ይህንንም ራሱን የመብትና የነፃነት፣ እንዲሁም የእኩልነት ጉዳይ አድርገን የወሰድንለት፣ የመሰከርንለት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ ባለቤትነቱ የመንግሥት መሆኑ ግን እዚያ ግቢና የወገንተኛነት ቅርቃር ውስጥ እንዲቀበር/ተቀብሮ እንዲቀር አላደረገውም፡፡ በሹመት፣ በበጀት ከመንግሥት ጋር የሚያስተሳስረውን ድርና ማግ ሳይበጣጥስ፣ እንዲያውም እዚያው ውስጥ ሆኖ በሰፊው ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማትን ግሎባል አሊያንስ (Global Alliance of National Human right Institutions/ GANHRI) የኤ/A ደረጃ የተጎናፀፈ ተቋም ነው፡፡ የዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማትን ከፍተኛውን የፕሪሚየር ሊግ የከፍታ ደረጃ ውስጥ ገብቶ፣ ተሳትፎና እንቅስቃሴ የሚያደርግ የዚህ ዘርፍ ዕድገታችን አብሪና አኩሪ ምልክት ነው፡፡ ይህንን አንፃራዊ ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ለውጥና ዕርምጃ መንግሥት ሚዲያና አመራር ውስጥ፣ መንግሥት ዕይታ ውስጥ ጭምር ማጣታችን፣ ማጣት ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም አልሞክርላችሁም ብሎ መቸገራችንና መከራ ማየታችን ግን የሚገርም፣ የተቋም ግንባታ ጥረታችን ድቅድቅ ጨለማው ዋናው ግዛት ነው፡፡ በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በአጠቃላይ በዚህ ዘርፍ የምናየው የለውጥ ዝናብ መንግሥት ሚዲያውና ሚዲያው አስተዳደር ውስጥ ይደገም፣ መደገም ቀርቶ ያካፋ ይሆን? ዴሞክራሲያችን በሕግ አምላክ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡