July 14, 2024

ርዕሰ አንቀጽ

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ዕውቅና›› በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሲሰጥ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሥነ ሥርዓቱን ‹‹ሚዲያ ለአገር›› በሚል ስያሜ ማዘጋጀቱ አይዘነጋም፡፡ በዚህ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ላሉና የንግድ ተብለው ለሚጠሩ ሚዲያዎች የተሰጠው ሽልማትም ሆነ ዕውቅና፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ተግሳፅ ቢጤ ማሳሰቢያ የተሰጠበት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ብዙ ይጠበቅባችኋል…›› ያሉት ሐሳብ ከሥነ ሥርዓቱ ቁምነገሮች አንዱ ነው፡፡ ሚዲያው እርግጥ ነው ብዙ መሥራት አለበት፡፡ ብዙ እንዲሠራ ደግሞ በሕግ የተሰጠው ነፃነት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ነፃነቱን በኃላፊነት ስሜት ሲያከናውን እውነትን መሠረት አድርጎ ይሠራል፡፡ መሥራት ሲሳነው ደግሞ ከማንም በላይ በሕዝብ የህሊና ችሎት ይዳኛል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1948 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19 ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አስመልክቶ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በ1987 ዓ.ም. ወጥቶ ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ተብሎ ይታወቃል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ሙሉ ለሙሉ ሳይሸራረፍ ከተመድ ድንጋጌ አንቀጽ 19 የተገለበጠ ሲሆን፣ በተለይ የፕሬስ ነፃነትን በሚገልጸው ንዑስ አንቀጽ 3 ሥር የቅድመ ምርመራ በማንኛውም ሁኔታ የተከለከለ መሆኑንና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መረጃ የማግኘት ዕድልን ይደነግጋል፡፡ በንዑስ አንቀጽ 4 ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል ይላል፡፡ ንዑስ አንቀጽ 5 ደግሞ በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን፣ የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በማያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል ይላል፡፡

እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሐሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት፣ በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመሥርተው በሚወጡ ሕጎች ብቻ እንደሚሆንና የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በእነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ እንደሚችሉ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ እንደሚከለከሉ፣ ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል በንዑስ አንቀጽ 6 እና 7 ተደንግጓል፡፡ በዚህ ኢትዮጵያ ፈርማ በተቀበለችው ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሚዲያው በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እውነትን ይዞ መሥራት ሲኖርበት፣ መንግሥትም ይህ ሕግ ያለ ምንም መሸራረፍ ሥራ ላይ እንዲውል የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን በዘመነ ኢሕአዴግ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ብቻ ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩት ዴሞክራሲያ መብቶች በመጨፍለቃቸው በርካታ ችግሮች መፈጠራቸው አይዘነጋም፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የወጣው አፋኙ የፕሬስ ሕግ (Draconian Press Law)  እና ሌሎች የተሻሻሉ ሕጎች፣ በሚዲያ ሥራና በሌሎች የመብት ሥራዎች ላይ ያደረሱት ጥፋት አይዘነጋም፡፡ በርካቶችን ለእስር፣ ለሥቃይና ለስደት የዳረጉት እነዚህ ሕጎች በ2010 ዓ.ም. በመጣው የለውጥ መንግሥት አማካይነት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በአዲስ መተካታቸው ይታወሳል፡፡ በተለይ በግል ሚዲያ ሥራ ላይ አሁንም ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የቀጠለው መረጃ ማግኘት አለመቻል ነው፡፡ አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት ለግሉ ሚዲያ መረጃ ለመስጠት ይተናነቃቸዋል፡፡ አልፈው ተርፈው ለግሉ ሚዲያ መረጃ አንሰጥም የሚሉ ተቋማት አሉ፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ካሉ ሚዲያዎች በስተቀር ለማስተናገድ ፍላጎት የላቸውም፡፡

ዘመኑ በቴክኖሎጂ የተራቀቀ በመሆኑና ሚዲያም የቴክኖሎጂው ተቋዳሽ ስለሆነ መረጃዎች በፍጥነትና በጥራት ለሕዝብ እንዲደርሱ ካልተደረገ፣ ሐሰተኛ መረጃዎች በስፋትና በብዛት ስለሚሠራጩ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ሐሰተኛ መረጃዎች የአገር ዕዳ እንዳይሆኑ ከተፈለገ፣ መንግሥት እጁ ላይ የሚገኙ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙኃን በፍጥነት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችና ከትራፊክ አደጋ ሪፖርቶች በዘለለ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ብልሹ አሠራሮችንም ሆነ ሌሎች ቀውስ የሚያስከትሉ ድርጊቶች በተመለከተ መረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡ በግጭት አካባቢዎች የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ፆታዊ ጥቃቶች፣ ዕገታዎችና ሌሎች የመብት ጥሰቶች ይዳፈናሉ፡፡ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ሳይቀሩ የሚሳተፉባቸው ሕገወጥነቶች ለሕዝብ ጆሮ እንዳይደርሱ ይታፈናሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሐሰተኛውን ከእውነተኛው ለመለየት የማያስችሉ መረጃዎች በየአቅጣጫው ይለቀቃሉ፡፡

የሚዲያ ዋነኛ ሥራ እውነተኛ መረጃ ለሕዝብ ማድረስ ሲሆን፣ ይህንንም ሥራውን ያለ አድልኦና ያለ ፍራቻ እንዲያከናውን ነፃነት ያስፈልገዋል፡፡ የነፃነት አስፈላጊነት ከማንኛውም አቅጣጫ የሚመጣን ተፅዕኖ ለመለከላከልና በኃላፊነት ስሜት መሥራት ለመቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከማንም በላይ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሚዲያው አራተኛ መንግሥትነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘው የሕግ አውጭ፣ የሕግ ተርጓሚና የሕግ አስፈጻሚ የመንግሥት አካላትን አሠራር በጥብቅ ለመከታተልና ጥፋት ሲኖር ለማጋለጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱ ወግና ማዕረግ ስለማይታወቅ ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር በወገንተኝነት ምንጣፍ ጎታች መሆን፣ ቅዋሜ ሲፈጠር ደግሞ የአኩራፊዎች መሰባሰቢያ መሆን የተለመደ ከሆነ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ ሲነሳ የድጋፍና የተቃውሞ ማስተጋቢያነቱ እንጂ፣ እንደ አንድ የተከበረ ሙያ በነፃነት ሥራውን እንዲያከናውን ድጋፍ አይቸረውም፡፡ ሚዲያው ሥራውን በነፃነትና በኃላፊነት ስሜት እንዲያከናውን ይደረግ፡፡ እስከዚያው ግን በሕዝብ የህሊና ችሎት እንዲዳኝ ዕድሉን ካገኘ በቂ ነው!