July 14, 2024 – Konjit Sitotaw

” ከ2013 ዓ/ም በፊት በአከባቢው ሰላም እና ፀጥታ ሲያስከብሩ የነበሩ ታጣቂ ተፈናቃዮች ከነትጥቃቸው ይመለሳሉ ” – ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዜዳንት ሌ/ ጀነራል ታደሰ ወረደ ትላንት መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በመግለጫቸው ፥ ” ለአመታት ከቄያቸው ተፈናቅለው በትግራይ የተለያዩ ከተሞች እና በሱዳን የሚገኙ የምዕራብ ትግራይ ነዋሪዎች እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም ወደ አከባቢያቸው ለመመለስ የተያዘው የጋራ እቅድ የዘገየው በጊዚያዊ አስተዳደሩ የተፈጠረ ችግር አይደለም ” ብለዋል።

” የነበረ ክፍተት ተገምግሞ ተፈናቃዮች ድህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቄያቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው ” ሲሉ አክለዋል።

ም/ፕሬዜዳንቱ ፥ ” የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ወደ አከባቢያቸው የመመለስ ስራ የራያ እና ፀለምቲ ተፈናቃዮች በመመልስ የተገኘው ልምድ መስረት በማድረግ ይፈጸማል ” ብለዋል።

” ተፈናቃዮችን የመመለስ ተግባሩን የሚያቆም አካል የለም ” ሲሉ ተደምጠዋል።

” የምዕራብ ትግራይ የህዝብ ብዛት እና የኢኮኖሚ የበላይነት ለመያዝ ያለመ የሰፈራ ስራ በአማራ መንግስት ተካሂደዋል ” ያሉት ሌ/ጀነራሉ ” ከሌሎች አከባቢዎች ወደ ምዕራብ ትግራይ ገብተው እንዲሰፍሩ የተደረጉ ታጣቂዎች እንዲወጡ ይሰራል ” ብለዋል።

” ከ2013 ዓ.ም በፊት በአከባቢው ሰላምና ፀጥታ ሲያስከብሩ የነበሩ ታጣቂ ተፈናቃዮች ከነትጥቃቸው ይመለሳሉ ”  በማለትም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ፥ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ቀላል እና ከባድ ወንጀሎች በመፈፀም ላይ እንዳሉ ተናግረው በአጭር ጊዜ ወንጀል ፈጻሚዎችን ወደ ተጠያቂነት ለመሸጋገር የሚስችል ስራ መጀመሩን አሳውቀዋል።

በከባባድ ወንጀል በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አመልክተዋል።

እነማ በህግ ቁጥጥር ስር ዋሉ? የሚለውን በዝርዝር አልተናግሩም።