ራፋ ሳላማ
የምስሉ መግለጫ,ራፋ ሳላማ

ከ 4 ሰአት በፊት

የእስራኤል መከላከያ ኃይል የሐማስ ከፍተኛ አመራር የሆነው ራፋ ሳላማ ቅዳሜ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. በጋዛ በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደሉን አስታወቀ።

የወታደራዊ አመራሩን ግድያ በተመለከተ ሐማስ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

እስራኤል ይህን የሐማስ ከፍተኛ አመራር ለመግደል በወሰደችው የአየር ጥቃት ከ90 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና ከ289 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

እስራኤል ሰብዓዊ ስፍራ ተብሎ በተከለለ አካባቢ ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው የሐማስ አመራሮች በስፍራው ተደብቀው ስለሚገኙ መሆኑን ገልጻ ነበር። ሐማስ ግን ይህ ሐሰት ነው በማለት የጥቃቱ ዒላማ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ብሏል።

የዓይን እማኖች በቅጻሜው ጥቃት ቢያንስ አምስት የጦር ጀቶች በምዕራብ ዃን ዩኒስ የሚገኝውን አል ማዋሲ አካባቢን በቦምብ ደብድበዋል ብለዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደተረሰባቸው ተጎጂዎች በአቅራቢያው ወደሚገኘው ናስር ሆስፒታል ተወስደዋል።

በተጎጂዎች የተጨናነቀው ሆስፒታል ግን በታካሚዎች ብዛት ሥራ መስራት አለመቻሉ ተገልጿል።

በሆስፒታሉ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ሞሐመድ አቡ ራያ አብዛኛዎቹ ታካሚዎቻቸው በበርካታ ፍንጣሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ብለዋል።

“በገሃነም ውስጥ የመሆን ያህል ነው” ሲሉ ሁኔታውን የገለጹት ዶ/ር ሞሐመድ በሆስፒታሉ ሕይወታቸው ካለፉ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ሳላማ የተባለው ግለሰብ የሐማስ የዃን ዩኒስ ብርጌድ አዛዥ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ቡድኑ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ካቀነባበሩት እና ከመሩት መካከል አንዱ ሳላማ መሆኑን የእስራኤል መንግሥት ይገልጻል።

ሳላማ ሐማስን የተቀላቀለው እአአ 1990ዎቹ መጀመሪያ ሲሆን በሞሐመድ ሲነዋር ስር የዃን ዩኒስ ብርጌድ አዛዥ ሆኖ ከተሾመ ሰነባብቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሳላማ በሐማስ ጦር ክንፍ ውስጥ ትልቅ ስልጣን ያላው ሞሐመድ ዳይፍ የቅርብ የሥራ ባልደረባ መሆኑን የእስራኤል ጦር ጨምሮ ገልጿል።

የጦሩ ቃል አቀባይ የሳላማ ግድያ “የሐማስን ወታደራዊ አቅም በእጅጉ ያዳክማል” ብሏል።

የእስራኤል ዋነኛ ዒላማ የነበረው ሞሐመድ ዳይፍ በዚህ ጥቃት ስለመገደሉ እስራኤል እስካሁን ማረገጋጫ አላገኘሁም ብላለች።

የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አመራር የሆነው ሞሐመድ ደይፍ በእስራኤል ለአስርት ዓመታት ሲፈለጉ ከቆዩ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው።