ካጋሜ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት

ከ 6 ሰአት በፊት

ከአምስት ዓመታት በፊት በተደረገ ምርጫ 99 በመቶ የመራጮች ድምጽን ያገኙት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ዛሬ የሚደረገውን ምርጫ ያሸንፉ ይሆን ብሎ መጠርጠር የዋህነት ነው የሚሆነው።

ካጋሜ እአአ 2017 ላይ በነበረው ምርጫ 95 በመቶ ድምጽ፤ 2003 በነበረው ደግሞ 93 በመቶ የመራጮችን ድምጽ አግኝተዋል መባሉን ተከትሎ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር የሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስለመሆኑ ጥያቄዎች ሲነሱበት ነበር።

ይህ ግን ለካጋሜ ምንም ነው። “100% ድምጽ ማግኘት ዴሞክራሲያዊ አይደለም የሚሉ አሉ። እነርሱ 15 በመቶ ብቻ ድምጽ አግኝተው አሸንፈናል የሚሉት ዴሞክራሲ ስላላቸው ነው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕሬዝዳንቱ አደባባይ በከፍተኛ ቁጥር ወጥቶ ድጋፉን ሲገልጽላቸው ለነበረ ሕዝብ፤ “በሩዋንዳ የሚሆነው ነገር የሩዋንዳ ጉዳይ ነው። ካስፈለጋቸው መጥተው መማር ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ቁመተ መለሎው የ66 ዓመት አዛውንት ለስለስ ባለ ንግግራቸው እና ከመጋረጃ ጀርባ ርህራሄ በሌለው ማንነታቸው በበርካቶች ይገለጻሉ።

ለካጋሜ የፖለቲካ ሕይወት ጅማሬ በሩዋንዳ በቱትሲ እና ሁቱ ጎሳዎች መካከል የነበረው ግጭት ምክንያት ሆኗል።

የፖል ካጋሜ መንግሥት በዘር ፍጅት ከደረሰው ጥፋት በመማር አሁን ላይ ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ እራሱን ሩዋንዳዊ ሲል እንጂ የጎሳ ማንነቱን መግለጽ የለበትም የሚል የጸና አቋም አለው።

ካጋሜ አገሪቱን በፈርጣማ ክንዳቸው መምራት ከጀመሩ ሦስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ካጋሜ ይፋዊ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2000 ቢሆንም፤ በትክክል የምሥራቃዊቷ አገር ሩዋንዳ መሪ መሆኑን የጀመሩት እርሳቸው የሚመሩት የቱትሲ አማጺያን ቡድን የሁቱ ጽንፈኛ መንግሥትን ገልብጦ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ከ1994 (እአአ) ጀምሮ ነው።

የፖል ካጋሜን መስል የያዙ ሩዋንዳውያን
የምስሉ መግለጫ,የፖል ካጋሜን መስል የያዙ ሩዋንዳውያን

የካጋሜ አስተዳደር ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ሰዎችን በማሳደድ የተዋጣለት ነው። ካጋሜን መተቸት ለእስር እና ባስ ሲልም ለሞት ይዳርጋል።

ጠንካራው የካጋሜ የስለላ መረብ ከአገር ውጪ ጭምር በርካታ ግድያዎችን እና አፈናዎችን እንደፈጸመ ይታመናል።

የቀድሞ የሩዋንዳ የደኅንነት ኃላፊን ጨምር በቀድሞ የበታች ሠራተኞቻቸው መገደላቸው ይገለጻል። የደኅንነት ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል ፓትሪክ ካሬጌያ ከካጋሜ ጋር ከተጣሉ በኋላ ከሩዋንዳ ሸሽተው በደቡብ አፍሪካ ተጠልለው ነበር።

ይሁን እንጂ እአአ 2014 ላይ ጆሃንስበርግ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተገድለው ተገኙ።

የኮሎኔል ካሬጌያ ወንድም ልጅ የሆነው ዴቪድ ባቴንጋ ከግድያው በኋላ ለጋዜጠኞች ሲናገር፤ “በገመድ ነው አንቀው የገደሉት” ብሏል።

ካጋሜ ብዙ ካነጋገረው ግድያ እራሳቸውን ለማራቅ ሲሞክሩ እንኳ አልተስተዋሉም። ምንም እንኳ በይፋ በግድያው እጄ የለበትም ቢሉም፤ ከቀድሞ የደኅንነት ኃላፊ ግድያ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “ሩዋንዳን ከድቶ ከቅጣት ማምለጥ የማይታሰብ ነው” ብለዋል።

የፖል ካጋሜ ደጋፊች
የምስሉ መግለጫ,የፖል ካጋሜ ደጋፊች

ከኮሎኔሉ ግድያ በኋላ በነበረ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፤ “ማንም ቢሆን ማን፤ አሁን ላይ በሕይወት ያሉትን ጨምሮ የእጃቸውን ያገኛሉ። ማንም ቢሆን። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው” ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ የአገራቸውን ደኅንነት ለማረጋገጥ ወደ ጎረቤት አገራት ወታደሮችን በድብቅ እስከመላክ ይደርሳሉ።

ፕሬዝዳንቱ የሁቲ አማጺ ቡድንን ለመውጋት ወታደር ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ልከዋል። ካጋሜ ኤም23 የተባለውን አማጺ ቡድን በመመሥረት እና በመደገፍ ይከሰሳሉ።

ካጋሜን አምባገነን ናቸው በማለት የሚተቹ እንዳሉ ሁሉ፤ በምዕራባውያን ፖለቲከኞች ጭምር አገሪቱን በማረጋገት እና መልሶ በመገንባት ይደነቃሉ።

ከ800 ሺህ በላይ ቱትሲዎችን እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን ከፈጀው የዘር ጭፍጨፋ በኋላ አገሪቱ አንድ ሆና ትቀጥላለች የሚል ግምት አናሳ ነበር።

ሩዋንዳ በጽዱ ከተሞቿ እና ሥነ ሥርዓት አክባሪ በሆኑ ዜጎቿ ትለያለች። ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ሙስና በሩዋንዳ ያነሰ ደረጃ ላይ ይገኛል። አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ያደረገችው ጥረት ባይሳካም ብዙ ርቀት ግን ተጉዛለች።

የምርጫ ፖስተር በጎዳና ላይ

“የይስሙላ ምርጫ”

“ድምጼን ለካጋሜ እሰጣለሁ” የምትለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ሜሪ ጄን ነች። “ይህው በሰላም ትምህርቴን እየተከታተልኩ ነው። ምስጋና ለፕሬዝዳንቱ ይሁን፤ ትምህርቴን በሰላም መከታተል የማልችልት ሁኔታ ይኖር ነበር” ትላለች።

ልክ እንደ ሜሪ ሁሉ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ 9 ሚሊዮን ሩዋንዳውያን ድምጻቸውን ለማን እንደሚሰጡ ግልጽ ይመስላል።

ዴሞክራቲክ ግሪን ፓርቲ የሚባል ተቃዋሚ ፓርቲ ፍራንክ ሃቢቤዛ የሚባሉ ዕጩ ያቀረበ ሲሆን፣ ፊሊፕ ማፓእማና የሚባሉ ፖለቲከኛ ካጋሜን ለመገዳደር የምርጫ ተሳታፊ ናቸው።

ይሁን እንጂ ምርጫውን ማን እንደሚረታ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው።

የሩዋንዳ ፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ቤልጄየማዊው ፊሊፕ ሬይንተጀንስ፤ “እውነት ለመናገር ምርጫው ለይስሙላ የሚደረግ” ነው ይላሉ።

“እውነት ለመናገር በዚህ ምርጫ ምን ሊከስት እንደሚችል አናውቅም። ነገር ግን ከዚህ ቀደም የነበሩት ምርጫዎች የውሸት ምርጫዎች ነበሩ” ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት በስደት በአሜሪካ የሚኖሩት የቀድሞ የሩዋንዳ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጆሴፍ ሰባራንዚ (ዶ/ር) የሩዋንዳን ምርጫ ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋር ያነጻጽሩታል።

“ምርጫው እንደ እግር ኳስ ነው። የምርጫው አዘጋጅ ተጋጣሚወን ይመርጣል። የጨዋታው ታዳሚዎችም ጨዋታውን ማን እንደሚያሸንፍ እያወቁ እንደማያውቁ የሚሆኑበት ድራማ ነው” ብለዋል።

ካጋሜ ሩዋንዳን ከ1994 ጀምሮ ሲመሩ ቆይተዋል።
የምስሉ መግለጫ,ካጋሜ ሩዋንዳን ከ1994 ጀምሮ ሲመሩ ቆይተዋል።

ፖል ካጋሜ

እአአ 1957 በማዕከላዊ ሩዋንዳ ባለጸጋ ከሆኑ ወላጆች የተወለዱት ካጋሜ፤ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነበር ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው ያፈናቀላቸው።

የቱትሲ ጎሳ ተወላጅ ለሆኑ ወላጆቻቸው አምስተኛ ልጅ የሆኑት ካጋሜ፣ የሁለት ዓመት ልጅ ሳሉ በአገራቸው እአአ በ1950ዎቹ ማብቂያ ላይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ኡጋንዳ ተሰደዱ።

ካጋሜ ከወላጆቻቸው ጋር ሲሰደዱ ምንም እንኳ ዕድሜያቸው ገና ሁለት ዓመት ቢሆንም፣ ቤቶች ሲቃጠሉ እና ሰዎች በታጣቂዎች ሲገደሉ መመልከታቸውን እንደሚያስታውሱ ይናገራሉ።

ካጋሜ በወጣትነት ዘመናቸው በ1970ዎቹ በኪጋሊ የፖለቲከኞች መናኽሪያ ወደሆነ ሆቴል በመመላለስ የፖለቲከኞችን ሃሜት ይሰሙ ነበር።

ይህ ተግባራቸው ካጋሜ በስለላ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ፍላጎት እንዲያድርባቸው አደረገ።

በኡጋንዳ ወታደራዊ የስለላ ሥልጠና የወሰዱት ካጋሜ፣ የዮዌሪ ሙሴቬቬን አማጺ ቡድን ተቀላቀሉ። ሙሴቬኒ የመሩት አማጺ ቡድን ሥልጣን ሲቆጣጠር ካጋሜ ተመለከቱ።

ከ1980ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ ካጋሜ በታንዛኒያ፣ ኩባ እና አሜሪካ ወታደራዊ ሥልጣናዎችን ከወሰዱ በኋላ አብዛኛዎቹ ቱትሲ የሆኑ አባላት ያሉበትን አማጺ ቡድን በመምራት እአአ 1990 ላይ ወደ ሩዋንዳ ዘመቻ ጀመሩ።

“ሩዋንዳ በጠንካራ አስተዳደር የምትመራ አገር ናት” የሚሉት ቤልጂየማዊው የፖለቲካ ተንታኝ፤ “ችግሩ በሩዋንዳ ለተቃዋሚዎች ቦታ የለም። የመናገር ነጻነት መብት የለም። የአገሪቱ ችግር ፖለቲካዊ አስተዳደሩ ነው” ይላሉ።

ካጋሜ ግን በዚህ አይስማሙ። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለእርሳቸው እና ለፓርቲያቸው ድጋፍ ለመስጠት ሕዝቡ በነቂስ አደባባይ መውጣቱ ሕዝቡ ለእርሳቸው ያለውን ፍቅር እንደሚያሳይ ይገልጻሉ።

አገሪቱን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በፈርጣማ ክንዳቸው የመሩት ካጋሜ በቅርብ የተደረገው ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ እስከ 2034 ድረስ አገሪቱን እንዲመሩ የሚያስችላቸው ነው።

ምዕራባውያኑ “ሥልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ ቆይተሃል ይሉኛል። ይሄ እነሱን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም። ይህ የሩዋንዳ ሕዝብ ጉዳይ ነው” ይላሉ።

ከሚወዷት አገራቸው በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚገኙት የቀድሞ አፈ ጉባኤ ዶ/ር ሰባራንዚ ወደፊት አገራቸው ሊገጥማት የሚችለው ነገር ያሳስባቸዋል።

“በታሪክ እንደተማርነው የአገር መሪዎች ከአገሪቱ ተቋማት በላይ ጠንካራ ሲሆኑ፤ የሥልጣን ለውጥ አመጽ የተቀላቀለበት ይሆናል” ብለዋል።