ቶማስ ማቲው ክሩክስ
የምስሉ መግለጫ,ቶማስ ማቲው ክሩክስ በ2022 የሁለተኛ ደራጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ የምረቃ መጽሄት ላይ የወጣ ፎቶው

ከ 6 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የአገር ውስጥ የደኅንነት መሥሪያ ቤት የሆነው ኤፍቢአይ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ በነበረበት መድረክ ላይ ተኩሶ አቁስሏቸዋል የተባለው ግለሰብ ቶማስ ማቲው ክሩክስ እንደሚባል ይፋ አድረጓል።

ግለሰቡ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በፔንሲልቬኒያ ግዛት በምትገኘው በትለር ውስጥ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ተኩስ ከፍቶ ከትራምፕ በተጨማሪ ሁለት ሰዎችን ክፉኛ አቁስሎ አንድ ሰው መግደሉ ተነግሯል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት የ20 ዓመቱ ወጣት ጥቃት ፈጻሚ ተኩስ በከፈተበት ስፍራ በአልሞ ተኳስ የደኅንነት አባል ተገድሏል።

ኤፍቢአይ ባወጣው መግለጫ ክሩክስ በዶናልድ ትራምፕ ላይ በተፈጸመው የግድያ ሙከራ ውስጥ “ተጠቃሽ ግለሰብ” እንደሆነ እና ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አመልክቷል።

ጥቃት ፈጻሚው በአቅራቢያው ካለ ሕንጻ ጣራ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ጥቃት ፈጻሚው በአቅራቢያው ካለ ሕንጻ ጣራ ላይ

ጥቃት ፈጸሚው ማን ነው?

ቶማስ ማቲው ክሩክስ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ መገደሉን ተከትሎ በኪሱ ውስጥ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ስላልተገኘ፣ መርማሪዎች ማንነቱን ለመለየት የዘረ መል ምርመራ (ዲኤንኤ) መደረጉን ኤፍቢአይ ገልጿል።

ክሩክስ ነዋሪነቱ እዚያው ፔንሲልቬኒያ ውስጥ በትራምፕ ላይ የመግደል ሙከራ ካደረገበት 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቤቴል ፓርክ ነዋሪ ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ክሩክስ በሂሳብ እና በሳይንስ ውጤቱ ሽልማትን ማግኘቱን የአካባቢው ጋዜጣ ዘግቧል።

ቢቢሲ ማጣራት እንደቻለው ወጣቱ በዕድሜ ባለጸጎች መንከባከቢያ ማዕከል የምግብ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ይሠራ ነበር።

የግዛቲቷ የመራጮች መዝገብን ጠቅሰው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ክሩክስ ዶናልድ ትራምፕ ዕጩ የሚሆኑበት የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ ‘አክትብሉ’ የሚባለው የሊብራል ቡድን ለሚያካሂደው ዘመቻ የ15 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ወጣቱ ጥቃቱን በፈጸመበት ጊዜ ‘ዲሞሊሽን ራንች’ የሚባለው እና የጠመንጃ እና የውድመት የቪዲዮ ይዘቶች የሚቀርቡበት የዩቲዩብ ቻናል ከነቴራ ለብሶ እንደነበር ተዘግቧል። ቻናሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፣ የጦር መሳሪያዎች እና የተለያዩ ፈንጂዎችን የሚመለከቱ ቪዲዮዎችን ያቀርባል።

አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ስማቸውን ያልገለጹ የደኅንነት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ክሩክስ በዶናልድ ትራምፕ ላይ ጥቃት የፈጸመበትን የጦር ማሳሪያ አባቱ ከስድስት ወራት በፊት በሕጋዊ መንገድ የገዙት ነው።

የትራምፕን የቀኝ ጆሮ የሚታችው ጥይት
የምስሉ መግለጫ,የትራምፕን የቀኝ ጆሮ የሚታችው ጥይት

የጥቃቱ ምክንያት ምንድን ነው?

ፖሊስ እና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች በምርጫ ቅስቀሳ ላይ በነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ግለሰብ ማንነትን ከለዩ በኋላ ለድርጊቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ምርመራ እያደረጉ ነው።

ጉዳዩን በተለይ የያዘው የኤፍቢአይ ልዩ ቡድን አባል የሆኑት ኬቪን ሮይክ ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ “በአሁኑ ጊዜ ይህ ነው የምንለው የግድያው ሙከራ ምክንያት የለንም” በማለት ምርመራው ወራትን ሊወስድ እንደሚችል አመልክተዋል።

የክሩክስ አባት ማቲው ክሩክስ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት “ምን መዓት እየተካሄደ መሆኑን” ለመረዳት እየሞከሩ መሆናቸውን እና ስለልጃቸው ከመናገራቸው በፊት “ከሕግ አስከባሪዎች ጋር እስክነጋገር ድረስ መጠበቅ አለብኝ” ብለዋል።

ከጥቃቱ በኋላ ፖሊስ ክሩክስ ከወላጆቹ ጋር ወደሚኖርበት ቤት የሚወስደውን መንገድ መዝጋቱ የተዘገበ ሲሆን፣ አንድ ጎረቤት ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ካለምንም ማስጠንቀቂያ ፖሊሶች እኩለ ሌሊት ላይ መጥተው ከቤታቸው አስወጥተዋቸዋል።

የአካባቢው ፖሊስ በክሩክስ መኖሪያ ቤት ዙሪያ የቦምብ ምርመራ መካሄዱንም አመልክቷል።

ወደ አካባቢው የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ በፖሊስ ተሽከርካሪዎች ተዘግተው ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ሲሆን፣ መግባት እና መውጣት የተፈቀደው ለነዋሪዎች ብቻ ነው።

ትራምፕ ከተመቱ በኋላ

ምን ያህል ሰዎች በጥይት ተመቱ?

ክሩክስ ትራምፕን ዒላማ አድርጎ ፈጽሞታል በተባለው ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፣ ሁለት ሌሎች ሰዎች ደግሞ በጥይት ተመትተው ቆስለዋል።

ሁሉም የጥቃቱ ሰለባዎች አዋቂዎች ሲሆኑ፣ ሦስቱም የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳን ለመታደም በስፍራው የተገኙ ነበሩ። የጥቃቱ ሰለባዎች ስም ግን እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ይፋ አልተደረገም።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የገንዘብ ጉዳዮች ኃላፊ የጎፈንድሚ ገጽ ከፍተው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ቤተሰቦች ድጋፍ የሚውል ገንዘብ ማሰባሰብ ጀምረዋል።

እስከ እሁድ ምሽት ድረስም ከ340,000 ዶላር በላይ ገንዘብ መሰባሰብ ተችሏል።

ከጥቃቱ በኋላ ትራምፕ ትሩዝ በተባለው የራሳቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ባሰራጩት መልዕክት፣ ጥይቱ ቀኝ ጆሯቸውን እንደመታቸው እና ጉዳቱ ከቆዳቸው ባሻገር የዘለቀ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ትራምፕ በጥይት ከተመቱ በኋላ የጥበቃ መኮንኖች ከመድረክ አጅበው ሲያወርዷቸው በፊታቸው እና በጆሯቸው ላይ ደም ይታይ ነበር።

ፓርቲያቸው ሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ኮሚቴ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ትራምፕ “ደህና” መሆናቸውን በመጥቀስ የሕግ አስከባሪዎች ለፈጸሙት ተግባር አድናቆቱን ገልጿል።

የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ አልሞ ተኳሾች በጥቃቱ ስፍራ
የምስሉ መግለጫ,የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ አልሞ ተኳሾች በጥቃቱ ስፍራ

ጥቃት ፈጻሚው ምን ዓይነት መሳሪያ ነው የተጠቀመው?

ከጥቃቱ በፊት ክሩክስ ይሆናል ተብሎ የሚታመን፣ አንድ ጠመንጃ የታጠቀ ግለሰብ ትራምፕ ላይ ከተተኮሰበት በአካባቢው ካለ ሕንጻ ጣራ ላይ አይቶ እንደነበረ አንድ የዐይን ምስክር ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቲኤምዜድ ያገኘው ቪዲዮ ተኩሱ የተከፈተበትን ቅጽበትን አሳይቷል።

ጥቃት ፈጻሚው ቀላል ክብደት ያለው ከፊል አውቶማቲክ የሆነ ጠመንጃ እንደተጠቀመ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

ነገር ግን ጥቃት ፈጻሚው ምን ዓይነት የጦር መሳሪያ እንደተጠቀመ እና ምን ያህል ጥይቶችን እንደተኮሰ ኤፍቢአይ ወዲያውኑ ማወቅ እንዳልቻለ ገልጾ ነበር።

የፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ አገልግሎት አልሞ ተኳሽ ጥቃት ፈጻሚውን ወጣት ተኩሶ መግደሉን ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ አረጋግጧል።

ኋላ ላይ የወጡ የቪዲዮ ምሥሎች የታጠቁ የፖሊስ መኮንኖች በሕንጻው ጣሪያ ላይ ተሰማርተው ተመትቶ ወደ ወደቀው ጥቃት ፈጻሚ አስከሬን ሲጠጉ አሳይቷል።