የሰፔን ቡድን አባላት

15 ሀምሌ 2024, 08:10 EAT

ተሻሽሏል ከ 4 ሰአት በፊት

ትላንት ምሽት በተጠናቀቀው የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን 2 ለ 1 በማሸነፍ የአውሮፓ ሻምፒዮን ሆነች።

በበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም በተከናወነው የፍጻሜ ጨዋታ፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ጎል ተጠናቋል።

የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች የተባለው ሮድሪ ከእረፍት መልስ በጉዳት ምክንያት ለስፔን ሳይሰለፍ ቀርቷል።

ከእረፈት መልስ ላሚን ያማል አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኒኮ ዊሊያምስ ከመረብ ላይ አሳርፏታል።

በውድድሩ ውጤታማ መሆን ያልቻለው ሃሪ ኬን በፍጻሜው ጨዋታም እንቅስቃሴው አርኪ አልነበረም። በኮቢ ማይኑ ተቀይሮ የገባው ኮል ፓልመር በ73ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ወደ ተጨማሪው ሰዓት ሊያመሩ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ማርክ ኩኩሬያ ያሻገረለትን ኳስ ኦያርዛባል ከመረብ አሳርፎ ስፔንን በድጋሚ ወደ መሪነት መለሰ።

ባለቀ ሰዓት የጨዋታዎችን ውጤት በመቀየር ለፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ በዴክላን ራይስ እና ማርክ ጉሄ አማካይነት ያደረጉት ኳስ በስፔኑ ግብ ጠባቂ ኡናይ ሳይመን እና ዳኒ ኦልሞ አማካኝነት ሊድን ችሏል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ስፔን የአውሮፓ ዋንጫን ለማንሳት ችላለች።

ስፔን ባለቀ ሰዓት ኦያርዛባል አስቆጥሮ የዋንጫ ባለቤት መሆኗን ከማረጋገጧ በፊትም ያማል፣ ዳኒ ኦልሞ እና አምበሉ ሞራታ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ተጠቅመው ቢሆን ጨዋታውን ቀድም ብለው መጨረስ ይችሉ ነበር።

እንግሊዝ ደግሞ ያለትልቅ ዋንጫ የዘለቀው የ58 ዓመታት ጥበቃዋ አሁንም ለመቀጠል የግድ ብሏል።

በውድድሩ ላይ ድንቅ የነበሩት ስፔናዊያን በወጣት ተጫዋቾች ታግዘው በአውሮፓ መድረክ ላይ ነግሰዋል።

ቅዳሜ ዕለት 17ኛ ዓመቱን ያከበረው ላሚን ያማል ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ ጎል ለማስቆጠር ከጫፍ የደረሰባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋል ያማል የውድድሩ ወጣት ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል።

ሌላኛው ስፔናዊ ወጣት ኒኮ ዊሊያምስ ደግሞ በጨዋታው ጎል ከማስቆጠር በላይ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።

የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ተጫውቶ በጉዳት ለመቀየር የተገደደው አማካዩ ሮድሪ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሏል።