ሞቃዲሾ

ከ 4 ሰአት በፊት

በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ የአውሮፓ ዋንጫ ሲመለከቱ በነበሩ ሰዎች ላይ አጥፍቶ ጠፊ በፈጸመው የቦምብ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገደሉ።

የሶማሊያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ትናንት እሁድ ሐምሌ 7/2016 ዓ.ም. በተፈጸውም ጥቃት ከ20 ያላነሱ ሰዎች ቆስለዋል።

የሶማሊያ ፖሊስ በመዲናዋ በሚገኝ ካፍቴሪያ ውስጥ እግር ኳስ ሲመለከቱ የነበሩ ሰዎችን ዒላማ ያደረገው ጥቃት የተፈጸመው መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ በማጋየት ነው ብሏል።

“ቶፕ የተባለውን ካፍቴሪያ ዒላማ ባደረገ መኪና ላይ የተጠመደ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ20 ያላሱ ሰዎች ቆስለዋል” ብሏል ፖሊስ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ላይ ባስነገረው መግለጫ።

ትናንት እሁድ ሐምሌ 7/2016 ዓ.ም. እንግሊዝ እና ስፔን ምሽት 4 ሰዓት ላይ የጀመረ የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ አድርገው ነበር።

በካፍቴሪያው የኳስ ጨዋታውን ሲመለከት የነበረው ሞሐመድ ታርሳን ኳስ እየተመለከቱ ሳለ በከፍተኛ ፍንዳታ ካፌው ተናወጠ ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግሯል።

በፍንዳታው ቀላል ጉዳት እንደደረሰበት የሚናገርው ሞሐመድ “የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ እንደተጠናቀቀ በጣም ከባድ አስፈሪ የሆነ ፍንዳታ ሰማን። ከዘያ ሁሉም እራሱን ለማዳን መሯሯጥ ጀመረ” ይላል።

“ዋናው መውጫ በሩ በእሳት ተሸፍኖ ነበር። ሰዎች ሁለት ሜትር የሚረዝም ግድግዳ ላይ እየተንጠላጠሉ ከካፌው ለመውጣት ሲተረማመሱ ነበር” ያለው ሞሐመድ በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኳስ ጨዋታውን ሲመለከቱ ነበር ብሏል።

ሌሎች የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ሶማልኛ እንደተናገሩት ደግሞ ከከፍቴሪያው አቅራቢያ ቆሞ የነበረው መኪና የጋየው የጨዋታው አጋማሽ ላይ ነበር።

ከፍንዳታው በኋላ እሳት እና ጭስ መመልከታቸውን እንዲሁም በካፍቴሪያው ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን የዓይን እማኞቹ ጨምረው ተናግረዋል።

ይህን ጨዋታ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ በሚደረግበት አካባቢ በሚገኘው ካፍቴሪያ ታድመው እየተመለከቱ ነበር።

ሞቃዲሾ

ዳልሳን የተባለና ከሞቃዲሾ የሚያሰራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከፕሬዝዳንቱ ቤተ-መንግሥት በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ካፍቴሪያ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ሁለት ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን ገልጿል።

ቴሌቪዥን ጣቢያው የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ቦምብ ተጠምዶበት የነበረው ተሸርካርካሪ ከካፍቴሪያው አቅራቢያ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ቆሞ ነበር።

ካፍቴሪያው በመንግሥት ሠራተኞች ዘንድ የሚዘወተር መሆኑ ተገልጿል።

ለዚህ ጥቃት እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም። ፖሊስ እንዲሁ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረገው አካል የለም።

ይሁን እንጂ በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አል-ሸባብ ይህን ጥቃት ሳይፈጽም እንደማይቀር ይገመታል።

እአአ 2010 በኡጋንዳ የዓለም ዋንጫ በሚመለከቱ ሰዎች ላይ አል-ሸባብ ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሞ ከ76 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።