ትራምፕ

15 ሀምሌ 2024, 12:55 EAT

“ድራማ ነው።”

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ይፋ በሆነ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ይህ ቃል በአሜሪካ የኤክስ ተጠቃሚዎች በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል።

ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ከዳር ዳር ከሞሉት የሴራ ትንተናዎች ጋር በተመሳሳይ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው።

ጥቃቱም ላይ ጥርጣሬ ጭሯል። ባለፉት 24 ሰዓታት ደግሞ ማስረጃ የሌላቸው፤ በመላምት የተሞሉ መረጃዎች በኤክስ ላይ ተለጥፈው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕይታዎችን አግኝተዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶች ላይ የሚደረጉ የግድያ ሙከራዎች ቀደም ሲል ጀምሮም ለሴራ ትንተና በር የከፈቱ ነበሩ።

እአአ በ1963 የተገደሉት የጆን ኤፍ ኬኔዲ ጉዳይ ደግሞ በዚህ ረገድ የሚስተካከለው የለም። የአሁኑ የሚለየው በቀጥታ ሚሊዮኖች እየተከታተሉት በመሆኑ መሠረተ ቢስ ወሬዎች መብዛታቸው አያስደንቅም።

ጎልቶ የወጣው ነገር ደግሞ ሁሉንም የፖለቲካ መንደር መነካካቱ ነው።

ጉዳዩ ቀንደኛ በሚባሉ የፖለቲካ ደጋፊዎች ዘንድ ብቻ የተገደበ አይደለም። ሳይፈልጉት ኤክስ ወደ እርስዎ ከማድረሱም በላይ በክፍያ ሰማያዊ ባጅ ያገኙ ተጠቃሚዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ታዋቂነት ለማትረፍ ጥረት አድርገዋል።

ከትራምፕ ጥቃት በኋላ በርካታ ሃሰተኛ መረጃዎች ተሰራጭተዋል

የ“ድራማ ነው” ሴራ ትንተና በስፋት መሰራጨት

የሴራ ትንተናዎች አንዳንድ ጊዜ ውሃ በሚያነሱ ጥያቄዎች እና ግራ መጋባቶች ነው የሚጀመሩት። ማዕከል ያደረጉት ደግሞ የደኅንነት ጥበቃ ስህተቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው።በዚህም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ በማንሳት የሚጀመሩ ናቸው።

ጥቃት አድራሹ እንዴት ወደ ጣሪያው ወጣ? ለምንስ አላስቆሙትም?

እነዚህ ምላሽ ባላገኙ ጥያቄዎች መሐል ደግሞ ያለማመን፣ ግምታዊ ሃሳቦች እና የሐሰት መረጃዎች ቦታውን ይይዛሉ።

“በትክክልም ድራማ ይመስላል። ከሕዝቡ መካከል የሚሮጥ ወይም የሚደነግጥ የለም። ማንም ትክክለኛ የጥይት ድምጽ አልሰማም። እኔ አላምንም። አላምነውም” የሚልን የኤክስ ጽሑፍ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።

ግለሰቡ መቀመጫውን በደቡብ-ምዕራብ የአየርላንድ የባሕር ዳርቻ እንዳደረገ ይጠቅሳል። ቆይቶ ደግሞ ተኩሱ እውነት መሆኑን ለጥፏል።

በቦታው እና ከውጭ የነበሩ የዐይን እማኞች የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ብዙዎች የነበሩበት ፍርሃት ግልጽ ሆነ።

ከመጀመሪያዎቹ በኋላ የተለቀቁት ቪዲዮዎች እና ምሥሎች ደግሞ ከሴራ ትንተናው ጋር ይበልጥ ጥቅም ላይ ዋሉ።

በተለይም በዋሽንግተን የሚገኘው በአሶሼትድ ፕሬስ (ኤፒ) ፎቶግራፍ አንሺ ኢቫን ቩቺ የተነሳው እና በብዙዎች ዘንድ የተወደሰው ፎቶግራፍ ላይ ከጀርባቸው የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ የቆመው ትራምፕ እጃቸውን ከፍ አድርገው ከፊታቸው እና ከጆሯቸው ደም እየፈሰሰ የሚያሳይ ነው።

መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገ አንድ ዩቲዩብ ምሥሉን “ፍጹም” በማለት ከመግለጽ ባለፈ “ባንዲራውን እና ሁሉም ነገር ፍጹም ሆኖ” እንዴት እንደተቀመጠ ገልጿል።

በኤክስ ላይ የነበረው ልጥፍ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዕይታዎችን ቢያገኝም በኋላ ላይ ግን ተነስቷል። ከተሳሳቱ እራስዎን ማረም አስፈላጊ ነው ሲልም በሌላ ልጥፉ አስታውቋል።

ሌሎች ደግሞ ጥይቱ ሲተኮስ ትራምፕ እጃቸውን ወደ መድረክ እንዳወጡ ጠቁመዋል። ይህንን የሚሉት ቀድሞ ዝግጅት የተደረገበት ክስተቱ “ድራማ ነው” ለማለት ነው። ለዚህ ግን ምንም ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም።

“ሐዘኔታን ለመፍጠር የተደረገ ነው? እነዚህን ሰዎች በምንም ነገር ማመን አይቻልም። ስለዚህ ለእሱ አልጸልይም” ሲል በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ሌላ ተንታኝ ጽፏል።

ይህን ጨምሮ ብዙ በጣም የታዩ ልጥፎች የመጡት በመደበኛነ በፀረ-ትራምፕ አመለካከታቸውን በሚታውቁ ግራ ዘመም ተጠቃሚዎች ነው። ቀደም ብሎም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ነበሯቸው። ስለዚህ በቀላሉ ብዙዎችን ለመድረስ ይችላሉ።

አብዛኛውን ሃሰተኛ መረጃ ያሰራጩት በፊትም በተመሳሳይ ሃሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካውንቶች ናቸው

“ሰይጣናዊ ድርጊት”

ኤክስ ላይ ያሉ አንዳንዶች ደግሞ ሁሉንም ነገር በመካድ የሴራ ትንተና የሚታወቁ ናቸው። የኮቪድ ወረርሽኝን፣ ጦርነቶችን፣ የጅምላ ግድያዎችን እና የሽብር ጥቃቶችን ጨምሮ ሁሉንም ነገር እውነት አይደለም ይላሉ።

እንደዚህ ዓይነት መሠረታዊ ጉዳዮችን በማጋራት የሚታወቅ አካውንት ደግሞ “ይህ ሰይጣናዊ የሆነውን የልጆች ፆታዊ ጥቃትን ስትጋፈጡ የሚከፍሉት ዋጋ ነው” ሲል ጽፏል።

ለዚህ ደግሞ የኪውአነን የሴራ ትንተና ይጠቅሳሉ። በዚህ የሴራ ትንተና መሠረት ትራምፕ በድብቅ አገር የሚመራውን የደኅንነት እና የስለላ ተቋማት ጥምረት ላይ ጦርነት ከፍተዋል።

ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይያስቀምጡም የግድያውን “ትዕዛዝ” ያስተላለፈው “ከሲአይኤ የመጣ ሊሆን ይችላል” ከማለት ባለፈ ባራክ ኦባማን፣ ሂላሪ ክሊንተንን እና ማይክ ፔንስን ተሳታፊ ናቸው በማለት ከሰዋል። ለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባይገኝም ልጥፉ 4.7 ሚሊዮን ጊዜ ታይቷል።

ይህ የተለመደ አካሄድ ነው። የአሁኑ ለየት የሚለው ነገር ብዙም ተመሳሳይ ነገር ውስጥ የማይገኙ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በስፋት መሳተፋቸው ነው። ትራምፕን የማይወዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ደጋፊዎቹም ጭምር ናቸው ይህ ድራማ ነው የሚል የሴራ ትንተና ውስጥ የገቡት።

በሕዝብ የተመረጡ ፖለቲከኞችም ተሳታፊ ናቸው። የጆርጂያው ሪፐብሊካን ኮንግረስማን ማይክ ኮሊንስ “ጆ ባይደን ትዕዛዙን አስተላልፈዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የምርጫ ፍልሚያቸውን በመጥቀስ ፕሬዝዳንት ባይደን “ትራምፕ ዒላማ ናቸው” በማለት የሰጡትን አስተያየትን ደግሞ እንደማስረጃ ጠቅሰዋል።

ሌሎች ፖለቲከኞች እና መገናኛ ብዙኃን ትራምፕን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ቃላቶች ውጥረቱን አባብሶ ለዚህ የግድያ ሙከራ አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉ አንዳንድ የትራምፕ ደጋፊዎች መሠረት ያላቸውን ጥያቄዎች እንዲያነሱ አድርጓል። ትዕዛዙን ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ባይደን ናቸው ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ የተለየ ሃሳብ ነው።

የኮሊንስ ጽሑፍ ኤክስ ላይ ከ6 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ዕይታዎችን አግኝቷል። በኋላ ላይ ግን ባይደን በማንኛውም መንገድ መሳተፋቸውን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም የሚል መልዕክት ተያይዞበታል። የእሳቸው “ዒላማ ናቸው” የሚለው አስተያየት ከአውድ ውጭ መወሰዱንም አክሏል።

ከጥቃት አድራሹ ጋር የተያያዙት ሐሰተኛ ውንጀላዎች

የጥቃት አድራሹን ማንነት በተመለከተ በርካታ ማስረጃ አልባ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል።

ኤፍቢአይ ታጣቂው የ20 ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ ነው ብሎ ይፋ ከማድረጉ በፊት የበርካታ ሰዎች ስም እየጠፋ ነበር።

የእግር ኳስ ተንታኝ ማርኮ ቫዮሊ ከጥቃቱ ጀርባ አለ የተባለው እና አንቲፋ የተሰኘው ግራ ዘመም ቡድን አባል ነው ብሎ መጠቀሱን ተመልክቶ ኢንስታግራም ላይ ለማስተባበል ከጣሊያን በእኩለ ሌሊት ለመጻፍ ተገዷል።

እሱ ኢንስታግራም ላይ ለማስተባበል ሲሞክር እነዚያ ከእውነት የራቁ ውንጀላዎች ኤክስ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕይታዎችን አግኝተው ነበር።

ይህ ለኤለን መስክ ኩባንያ ፈተና ነው።

ሌሎቹ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በተመሳሳይ መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ አልተጥለቀለቁም። ይህ የሆነው በተጠቃሚዎቹ እና በኤክስ ፖለቲካ ዲስኩሮችን በማንሸራሸር ስለሚታወቅ ሊሆን ይችላል።

ቢቢሲ ከኤክስ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።