ትራምፕ ከጥቃቱ በኋላ

15 ሀምሌ 2024, 11:38 EAT

ፔንሲልቬኒያ ግዛት ውስጥ ቅዳሜ ሐምሌ 7/2016 ዓ.ም. የግድያ ሙከራ የተፈጸመባቸው ዶናልድ ትራምፕ “ልሞት ነበረ” ሲሉ ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገሩ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ቃለ ምልልስ በተደረገባቸው የመግደል ሙከራ ሊሞቱ ይችል እንደነበር እና “በዕድል ወይም በእግዚአብሔር ጥበቃ” መትረፋቸውን ተናግረዋል።

“ከሁሉ የሚያስደንቀው ነገር ፊቴን በትክክለኛው ሰኣት ማዞሬ ብቻ ሳይሆን በተገቢው ሁኔታ መሆኑ” ጆሯቸውን ጨርፎ በሄደው ጥይት ከመሞት እንዳዳናቸው ገልፈዋል።

በምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ለመታደም ከተገኙት ሰዎች መካከል በጥቃቱ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል።

የግድያ ሙከራ ከተፈጸመባቸው ከ32 ሰዓታት በኋላ ለሪፐብሊካን ፓርቲ ስብሰባ ዊስኮንሲን ግዛት ሜልዋኬ ከተማ የተገኙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ “እዚህ መሆን አልነበረብኝም። ሟች ነበርኩ” በማለት ለኒው ዮርክ ፖስት ተናግረዋል።

“በሆስፒታል የነበረው ዶክተር እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቶ እንደማያውቅ ነው የነገረን። ሁኔታን ተዓምር ሲል ገልጾታል” ብለዋል።

ትራምፕ በአሜሪካዋ ፔንስልቬኒያ ግዛት በትለር በተባለች ከተማ ከደጋፊዎቻቸው ፊት ቆመው ንግግር እያደረጉ ሳለ ከአምስት ያላሰኑ ጥይቶች ወደ እርሳቸው የተተኮሱ ሲሆን፤ በቀኝ በኩል ያለው ጆሯቸው በጥይት መትቷል።

ተደጋጋሚ የተኩስ ድምጾቹ እንደተሰሙ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ የደኅንነት ቡድን (ሴክሬት ሰርቪስ) አባላት የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ለመከላከል በፍጥነት ወደ መድረክ በመውጣት ትረምፕን ዝቅ አድርገው በመሸፈን ከሚተኮሰው ጥይት መጠበቅ ችለዋል።

ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸመው ቶማስ ማቲው ኩሩክስ የተባለው የ20 ዓመት ወጣት ከሴክሬት ሰርቪስ አባላት በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል።

ከተጠርጣሪው በተጨማሪ አንድ የ50 ዓመት ግለሰብ ከሚተኮስ ጥይት ቤተሰቡን ለመሸፈን ሲሞክር ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል። ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሕክምና እየተደረገላቸው ነው።

በአሁኑ ወቅት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በጥይት የተመታው ቀኝ ጆሯቸው ላይ ህክምና ከተደረገ በኋላ ተሸፍኖ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ዛሬ ሰኞ ጀምሮ ለቀጣይ አራት ቀናት የሪፐብሊካን ፓርቲ አጠቃላይ ጉባኤ ይጀምራል። በዚህ ጉባኤ ላይ ፓርቲው በይፋ ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በይፋ ዕጩ አድርጎ ያቀርባቸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እንዲሁም የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታን ሊይዙ የሚችሉ አብረዋቸው የሚወዳደሩ አጋራቸውን በዚሁ ጉባኤ ላይ ያስታወቃሉ።

ምንም እንኳ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ቢደረግም ዊስኮንሲን የሚደረገው የፓርቲው ጉባኤ በታቀደለት ጊዜ እንዲካሄድ ተወስኗል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጉባኤውን ከሁለት ቀናት በኋላ ለማድረግ ሃሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፤ “ለተኳሹ ዕድል መስጠት የለብኝም በሚል ጉባኤው በታቀደለት ቀን እንዲደረግ ወስኛለሁ” ብለዋል።

ትራምፕ ለፓርቲ ጉባኤ ሜልዋኬ ከተማ ሲደርሱ በከፍተኛ አጀብ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የምስሉ መግለጫ,ትራምፕ ለፓርቲ ጉባኤ ሜልዋኬ ከተማ ሲደርሱ በከፍተኛ አጀብ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በፓርቲ ጉባኤ ላይ የሚያደርጉት ንግግር ተቀናቃኛቸውን ጆ ባይደንን ከመተቸት ይልቅ አገሪቷን ወደ አንድነት ማምጣት ላይ ያተኮረ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ ከ50 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ከተፈጸመ በኋላ ጆ ባይደን እሁድ ሐምሌ 8/2016 ዓ.ም. ከዋይት ሃውስ ጽህፈት ቤታቸው ባደረጉት ንግግር፤ ጥቃቱን አውግዘው አገራዊ አንድነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

“አመጽ መልስ ሊሆን አይችልም” ያሉት ባይደን “ጨዋነት፣ ክብር እና ፍትሃዊነት” የአሜሪካ ፖለቲካ መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የ20 ዓመቱ ወጣት እሳቸው ላይ የመግደል ሙከራ ለማድረግ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን እንደማይታቅ ጨምረው ተናግረዋል።

አሜሪካውያንን ያስደነገጠውን ክስተት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የአገሪቱ የደኅንነት ተቋማት ምርመራ እኣደረጉ መሆኑን አሳውቀዋል።