
15 ሀምሌ 2024, 12:34 EAT
ባለፈው ሳምንት በናይሮቢ አንድ ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ የተቆራረጠ የሴቶች አካል በማዳበሪያ ተጥሎ ከተገኘ በኋላ ከ40 በላይ ሴቶችን መግደሉን ያመነ ግለሰብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ባለቤቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን መግደሉን ያመነው የ33 ዓመት ተጠርጣሪ የተያዘው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ቢያንስ የስምንት ሴቶች አስከሬን ከተገኘ በኋላ ነው።
ኮሊንስ ካሃሊሲአ የተባለው ተጠርጣሪ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ሴቶችን ብቻ እየለየ ሲገድል እንደቆየ ቃሉን መስጠቱን የኬንያ ፖሊስ አስታውቋል።
ተጠርጣሪው በሰጠው ቃል “ውብ የሆኑ ሴቶችን” መግደል እንደሚመርጥ ጨምሮ ተናግሯል።
የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዋና አዛዥ ሞሐመድ አሚን ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 8/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ “ለሰው ልጅ ሕይወት ምንም ደንታ የሌለው ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር አውለናል” ብለዋል።
ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ያዋለው ከገደላቸው ሴቶች ከአንዷ ሞባይል ወደራሱ ስልክ ገንዘብ ከላከ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊስ ኃላፊው በመግለጫቸው ተጠርጣሪው ኮሊንስ የሚኖረው የሴቶቹን አስክሬን ሲጥል ከነበረበት የቆሻሻ መጣያ ስፍራ 500 ሜትር ርቀት ላይ ነው ብለዋል።
የዚህ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋል የተሰማው ባለፉት ቀናት ከቆሻሻ መጣያው ስፍራ የበርካታ ሴቶች የተቆራረጡ አካላት በማዳበሪያ ተጥሎ ከተገኘ በኋላ ነው።
- በኬንያ በቆሻሻ መጣያ ስፍራ የበርካታ ሴቶች አካል ተቆራርጦ ተጥሎ ተገኘ14 ሀምሌ 2024
- የግድያ ሙከራ የተፈጸመባቸው ትራምፕ ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለክስተቱ ተናገሩ15 ሀምሌ 2024
- ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል በመሞከር ስለተጠረጠረው ወጣት እስካሁን ምን ይታወቃል?15 ሀምሌ 2024
ቅዳሜ ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. ፖሊስ በመዲናዋ ናይሮቢ ከሚገኝ የቆሻሻ መጠያ ስፍራ የተቆራረጡ የስምንት ሴቶች አካላት በተለያዩ ከረጢቶች ተጥሎ ማግኘቱን አስታውቋል።
ይህ የሴቶች አካላት ተጥሎ መገኘት ኬንያውያንን ያስቆጣ ሲሆን፣ መንግሥት ክስተቱን መርምሮ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ አስታውቆ ነበር።
ፖሊስ ጨምሮም ከተጠርጣሪው ቤት ለወንጀል ድርጊት ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበሩ ያላቸው ገጀራ፣ ጓንት እና ከረጢቶች እንዲሁም የሟቾች ሞባይል ስልኮች፣ ሲም ካርዶች እና መታወቂያዎችን ተገኝተዋል ብሏል።
ጫና ውስጥ የሚገኙት የአገሪቱ ፕሬዝዳንትም “እኛ በሕግ የበላይነት የምንመራ ዲሞክራሲያዊ አገር ነን። በናይሮቢ እና በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል በተፈጸሙት ምሥጢራዊ ግድያዎች ውስጥ የተሳተፉ አካላት በሕግ ይጠየቃሉ” ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ አንዳንዶች በሰዎቹ ግድያ ውስጥ የመንግሥት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የሚል መላምት እየሰጡ ይገኛሉ።
በቅርቡ በፀረ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ የነበሩ በርካታ ሰዎች አድራሻ የማይታቅ ሲሆን፣ የመብት ተሟጋቾች አድራሻቸው የጠፋ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ ነው ይላሉ።
በተቃውሞ ወቅት በኬንያ ፖሊስ አባላት ታፍነው ተወስደዋል ከተባሉት መካከል ሕይወታቸው አልፎ የተገኙ ሰዎች አሉ።
ዛሬ ሰኞ ደግሞ የሴቶች አስክሬን ተጥሎ ከተገኘበት ስፍራ በቂ ፍለጋ እና ምርመራ ሳይደረግ ፖሊስ አካባቢውን በእሳት ማቃጠሉ መረጃ የማጥፋት ተግባር ነው ሲሉ አንዳንድ ነዋሪዎች እየተቃወሙ ነው።
የኬንያ ፖሊስ በበኩሉ የሰዎቹ ሕይወት ያለፈው ከባዕድ አምልኮ ወይም ከግድያ ወንጀል ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል ሲል ግምቱን ሰጥቶ ነበር።