ኤንዞ ፈርናንዴዝ

ከ 3 ሰአት በፊት

የእንግሊዙ ክለብ ቼልሲ አማካዩ ኤንዞ ፈርናንዴዝ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን በተመለከተ “ዘረኛ” ዘፈን ሲዘፍን በማኅበራዊ ሚድያ መታየቱን ተከትሎ ምርመራ ከፈተ።

የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ዘፈኑ “ዘረኛ እና አግላይ” ግጥሞችን ያዘለ ነው ብሏል።

ማክሰኞ ዕለት መግለጫ ያወጣው የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ቅሬታ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

አንዳንድ የአርጀንቲና ተጫዋቾች ከኮፕ አሜሪካ ድላቸው በኋላ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን በተመለከተ ያዜሙት ነው የተባለ ዜማ በማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሪያ ሆኗል።

በቼልሲ የኤንዞ ፈርናንዴዝ የክለብ አጋር የሆነው እና ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አንድ ጨዋታ ያደረገው ዌስሊ ፎፋና በኢንስታግራም ገፁ ባጋራው መልዕክት “ግልብ ዘረኝነት” ነው ብሏል።

ቢቢሲ ስፖርት እንደተረዳው ቼልሲ ጉዳዩን በተለመከተ ምርመራ የከፈተ ሲሆን ምርመራውን አጥብቆ ይዞታል።

የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን [ኤፍኤፍኤፍ] ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ቀጥታ የተላለፈውን ቪድዮ በተመለከተ የአርጀንቲና አቻውን እንደሚያናግር አሳውቋል።

ባለፈው እሑድ ምሽት በኮፓ አሜሪካ ፍፃሜ አርጀንቲና ኮሎምቢያን 1-0 ከረታች በኋላ የብሔራዊ ቡድን አባላት አውቶቡስ ውስጥ ሲጨፍሩ እና ሲዘፍኑ ነው ኤንዞ ፈርናንዴዝ በኢንታግራም ገፁ በቀጥታ ያስተላለፈው።

በቪዲዮ ላይ የአርጀንቲና ተጫዋቾች የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወላጆቻቸው ከአፍሪካ ሆነው ሳለ የሚጫወቱት ግን ለፈረንሳይ ነው የሚል ይዘት አለው።

ከክስተቱ በኋላ ኤንዞ በኢንታግራም ገጹ ይቅርታን ጠይቋል። አማካዩ ዘፈኑ “እጅግ አግባብ ያልሆኑ ቃላቶችን ይዟል” ካለ በኋላ “በቪዲዮ ላይ የተባሉት አመለካከቴን እና ባሕሪዬን አይወክሉም” ካለ በኋላ ይቅርታ ጠይቋል።

ኤፍኤፍኤፍ ባወጣው መግለጫ ፕሬዝደንቱ ፊሊፔ ዲያሎ “የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አባላት ላይ የደረሰውን በፍፁም ተቀባይነት የሌለው እና አግላይ የሆነውን ዘፈን እናወግዛለን” ብለዋል።

መግለጫው አክሎ “ይህ በጣም አስደንጋጭ ክስተት ከስፖርት እና ከሰብዓዊ መብት እሴቶች ጋር የሚጣረስ ነው። የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀጥታ ለአርጀንቲና አቻው እንዲሁም ለፊፋ ጥያቄ ያቀርባል። ዘረኛ እና አግላይ የሆነውን ዘፈን በተለመከተ ሕጋዊ ቅሬታ ማስገባትም ይፈልጋል” ይላል።

የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሐሳብ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል።

በ2018 ዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ላይ ፈረንሳይ አርጀንቲናን መርታቷ ይታወሳል። በ2022 የዓለም ዋንጫ ደግሞ በፍፃሜው አርጀንቲና ፈረንሳይ በመርታት ባለድል መሆኗ አይዘነጋም።

አርጀንቲናዊው አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝ በአውሮፓውያኑ 2023 ነው ከፖርቹጋሉ ቤንፊካ በ107 ሚሊዮን ፓውንድ ቼልሲን የተቀላቀለው።