የወባ ትንኞች

ከ 3 ሰአት በፊት

በአፍሪካ ዋነኛ የተበላውን መድሃኒት የሚቋቋም የወባ በሽታ በመስፋፋቱ ከፍተኛ ስጋት ተፈጠረ።

ተመራማሪዎች መድኃኒትን የተላመደ የወባ በሽታ ስርጭትን ለማስቆም አስቸኳይ እና ሥር ነቀል እርምጃ ካልተወሰደ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ ተጋልጠዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የወሳኙን የአርተማይሲኒን መድሃኒት ተፅእኖ መቋቋም የሚችሉ የወባ በሽታ በምስራቅ አፍሪካ ተስፋፍተዋል ተብሏል።

በአንዳንድ አካባቢዎች መድሃኒቱን የመላመድ ምጣኔው በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከአንድ በመቶ በታች ወደ 20 በመቶ በላይ ጨምሯል።

በአፍሪካ ለመጨረሻ ጊዜ የፀረ ወባ በሽታን መድሃኒትን የሚቋቋም ወባ በመከሰቱ ምክንያት በበሽታው የሚሞቱት ሕፃናት ቁጥር በሦስት እጥፍ እንዲጨምር አድርጎ ነበር።

ከ10 አገራት የተውጣጡ 28 ታዋቂ የወባ ሳይንቲስቶች በሳይንስ ጆርናል ላይ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

አርተማይሲኒን የወባ በሽታን የሚያስከትል ተወሳክ የሚገድል ሲሆን በበሽታው ሕክምና ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ተደርጎ ይወሰዳል።

አርተማይሲኒንን የሚቋቋም ወባ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ በሩዋንዳ፣ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በኡጋንዳ እና በኤርትራ መፈጠሩ ተነግሯል።

እነዚህ መድሃኒቱን የተላመዱ ወባዎች በአገራቱ እና ድንበር ዘለው ተሰራጭተዋል።

ወባ ይገድላል የሚል ጽሑፍ የያዘች ልጅ

አሁን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የወባ በሽታ የሚከሰተው መድሃኒቱን በተቋቋሙ ፓራሳይቶች ነው።

“በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውጤታማ ባልሆኑ የፀረ ወባ ሕክምናዎች ከመሞታቸው በፊት እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ በናይጄሪያ የሚገኘው የኢሎሪን ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ሕክምና ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ኦሉግቤንጋ ሞኩኦሉ ተናግረዋል።

እአአ በ2016 በሰሜን ኡጋንዳ መድሃኒቱን የሚቋቋም ወባ እምብዛም አልተገኘም ነበር። እአአ በ2019 ግን ከ20 በመቶ በላይ ደርሷል።

መድሃኒት የተላመደውን ዝርያ ይበልጥ ከትስፋፋ “ማስወገድ የማይቻል” ይሆናል ሲሉ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድኑ ተናግረዋል።

በታይላንድ የማሂዶል ኦክስፎርድ ትሮፒካል ሕክምና ምርምር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት የሆኑት ዶ/ር መሁል ዶርዳ ይህ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚከሰት ለጊዜው እርግጠኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

ነገር ግን በደቡብ ምስራቅ እስያም ተመሳሳይ የሆነ ነገር ታይቶ በአርተማይሲኒንን ላይ የተመሠረቱ ህክምናዎች ውቴታማ መሆን አቁመዋል።

ከታሪክ መማር

ተመሳሳይ ታሪክ ከዚህ በፊት ተከስቷል። በ 1970ዎቹ በሽታው በምስራቅ አፍሪካ ቀድሞ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ክሎሮኪን የተሰኘ መድሃኒት መቋቋም ጀመረ። በ 1980 ዎቹ ደግሞ ወደ ምዕራባዊ አፍሪካ ተስፋፋ።

በአህጉሪቱ በወባ ምክንያት የሚከሰት ሞት በሦስት እጥፍ ጨምሮ በ 1980 ከነበረበት 493 ሺህ ገደማ በ 2004 ወደ 1.6 ሚሊዮን አደገ።

“ይህ በድጋሚ አፍሪካ ውስጥ የምናየው ነገር እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ዶክተር ዶርዳ ተናግረዋል።

“የአርተማይሲኒን ሕክምና አልሳካ ማለት ከጀመረ የሞት ቁጥር ይጨምራል።”

ሊቃውንቱ በሽታውን የሚያሰራጩትን ተወሳክ እና ትንኞጩ ላይ ያነጣጠሩ ምክረ ሃሳቦችን ሰጥተዋል።

ፓራሳይቱ ህክምናውን የመቋቋም ችሎታ እንዳይኖረው ለማድረግ ሦስተኛውን መድሃኒት በአርተማይሲኒን ጥምር ህክምናው ላይ መጨመርን አንስተዋል።

ዶክተር ዶርዳ ይህ ገንዘብ ያስወጣል “ካልሆነ ግን እሳቱ ከመስፋፋቱ በፊት ከማጥፋት ይልቅ ለመቆጣጠር ብዙ ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ እናደርጋለን” ብለዋል።

ሌሎቹ ምክረ ሃሳቦች የሚከተለውን ጥሪ ያቀርባሉ፡

“እርዳታ በአፍሪካ የአርተማይሲኒንን የሚቋቋም ወባ ስርጭትን ለመግታት እና ለማጥፋት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ሲሉ በታንዛኒያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባልደረባ የሆኑት ዳይሬክተር ንቱሊ ካፖሎግዌ ተናግረዋል።