ቴል አቪቭ

ከ 51 ደቂቃዎች በፊት

የእስራኤል ጦር በመዲናዋ ቴል አቪቭ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ አንድ ሰው መገደሉን አስታወቀ።

ለድሮን ጥቃቱ የየመን የሁቲ አማጺያን ኃላፊነቱን ወስደዋል።

የእስራኤል ጦር አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ በሰው ስህተት አየር ላይ ተመትቶ መጣል ያልቻለው ድሮን በቴል አቪቭ ፍንዳታ መፍጠሩን አስታውቋል።

የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት በፍንዳታው አንድ ሰው መገደሉን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ገልጧል።

በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስደው ቴል አቪቭን ዒላማ ስላደረገው ወታደራዊ እርምጃቸው ዝርዝርን እንደሚያወጡ ገልጸዋል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ የአየር ቅኝቶቹን ማጠናከሩን የገለጸ ሲሆን የቴል አቪቭ ከንቲባ ደግሞ መዲናዋ በተጠንቀቅ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

አንድ የዓይን እማኝ ሃሬትዝ ለተባለ መገናኛ ብዙሃን ሲናገር ፍንዳታው ሲያጋጥም “ሕጻዎች ተንቀጥቅጠው ነበር” ብሏል።

አሎን የተባለው የአካባቢው ነዋሪ፤ “የጎረቤቶቼ መስኮት መስታወት ተሰባብሯል። በጣም በርካታ ሕንጻዎች ተጎድተዋል” ብሏል።

የሁቲ አማጺያን ይህን የድሮን ጥቃት የፈጸሙት የእስራኤል ጦር ከፍተኛ የሄዝቦላ አመራርን በደቡብ ሌባኖስ የመግደሏ ዜና ከተሰማ በኋላ ነው።

ሐማስ መስረከም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ሄዝቦላ እና እስራኤል የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ነበር።

መቀመጫውን በሌባኖስ ያደረገው ሄዝቦላ እና የየመኑ ሁቲ ለፍልስጤማውያን አገራቸውን በመግለጽ እስራኤልን ሲያጠቁ ቆይተዋል።

እነዚህ ሁለት ቡድኖች በኢራን መንግሥት የሚደገፉ ሲሆን ከዚህ ቀደም እስራኤልን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

የሁቲ አማጺያን ቀይ ባሕር ላይ መዳረሻቸውን እስራኤል ያደረጉ መርከቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የዓለም የባሕር ንግድ ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ ቆይቷል።

ከእስራኤል ጦር ጋር ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ሊገባ ከጫፍ ተቃርቧል የሚባልለት ሄዝቦላም እንዲሁ ባለፉት ወራት ሮኬቶችን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ሲተኩስ ቆይቷል።