ካርታ

ከ 5 ሰአት በፊት

“የፋኖ ታጣቂዎች” በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በሚገኝ “የአገው ተወላጆች” መኖሪያ ቀበሌ ላይ ፈጸሙት በተባለ ጥቃት ከአስር ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ሰባት ተፈናቃዮች እና የተፈናቃዮች ተወካዮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ለነዋሪዎቹ መፈናቀል ምክንያት በሆነው ጥቃት “ህጻናትን” ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ነዋሪዎች መገደላቸው እንዲሁም በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር ውጊያ ላይ የሚገኙት “የፋኖ ታጣቂዎች” በይካዎ ቀበሌ ላይ ጥቃት የፈጸሙት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም. እንደሆነ የቀበሌው ሊቀ መንበር አቶ አለማየሁ ታሌ እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ጥቃት የደረሰበት ይህ ቀበሌ በአብዛኛው “የአገው ተወላጆች” የሚኖሩበት እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት አካባቢው ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች አስረድተዋል።

የቀበሌው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት የማክሰኞ ዕለቱ ጥቃት ከመፈጸሙ አስቀድሞ “የፋኖ ታጣቂዎች እና የቀበሌው ሚሊሻዎች” ለአራት ቀናት ውጊያ ላይ ቆይተዋል ብለዋል።

የሁለቱ አካላት ግጭት የተነሳው የቀበሌው ሚሊሻዎች በመንግሥት የተሰጣቸውን የጦር መሳርያ ለፋኖ ታጣቂዎች እንዲያስረክቡ የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቃወማቸው እንደሆነ ነዋሪዎች እና የቀበሌው ሊቀ መንበር አስረድተዋል።

“በአካባቢው ፋኖ የሚባል ቡድን አለ። የመንግሥትን መሳሪያ አስረክቡን ይላል። መንግሥት ደግሞ አታስረክቡ ብሎናል። መሳሪያ አናስረክብም፣ እኛን አትንኩን እያልን ከ2015 ነሐሴ ጀምሮ ቆይተናል” የሚሉት የቀበሌው ሊቀ መንበር፤ ሰኔ 28/2016 ዓ.ም. ታጣቂዎቹ በቀበሌው ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የቋራ ወረዳ ባለሥልጣን፤ “የመንግሥት ደጋፊ ናቸው፤ ለመንግሥት አግዘዋል በሚል ነው ጉዳት ያደረሱባቸው” ሲሉ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተዋል።

ወረዳው የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይሎች ተደጋጋሚ ውጊያ ያደረጉበት እንደሆነ የሚናገሩት ባለሥልጣኑ፤ በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ቀበሌዎች እንዳሉ አስረድተዋል። ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆኑ የአካባቢው ቀበሌዎችን ብዛት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በተጀመረው ግጭት አካባቢው ሚሊሻዎች ለቀናት “ራሳቸውን ሲከላከሉ” እንደቆዩ የወረዳ ባለሥልጣኑ ጠቅሰዋል። በግጭቱ አምስተኛ ቀን የአካባቢው ሚኒሻዎች መሸሽ እንደጀመሩ የቀበሌው ሊቀ መንበር አቶ አለማየሁ እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አቶ አለማየሁ፤ “አራት ቀን ገጥመነው ማክሰኞ ዕለት ነው አምስተኛ ቀን። አንድኛውን ገቡ፣ የሚጨፈጭፉትን ጨፈጨፉ፣ የሚያቃጥሉትን አቃጠሉብን” ሲሉ ታጣቂዎቹን ከስሰዋል።

በዕለቱ ወደ ቀበሌው ሙሉ በሙሉ የገቡት ታጣቂዎች “በውጊያው ላይ ያልተሳተፉ” ነዋሪዎችን መግደላቸውን እንዲሁም ቤት እና አዝመራ ማቃጠላቸውን አስረድተዋል።

ቢቢሲ፤ ከግጭቱ በኋላ በተፈጸመው ጥቃት ቤተሰቦቻቸው እንደተገደሉባቸው የገለጹ አራት የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል። እነዚህ የዐይን እማኞች በጥቃቱ ህጻናት እና አዛውንቶች ጭምር መገደላቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የአካባቢው ነዋሪ ቄስ፤ “አርሶ አደር የሆኑ” ሁለት ወንድሞቻቸው በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ መገደላቸውን ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቱ፤ በዚሁ ጥቃት የተገደሉ ሁለት ህጻናት ልጆች እንዲሁም የእናታቸው ቀብር ሲከናወን መገኘታቸውን በመጥቀስ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

የሃይማኖት አባቱ፤ “ቄስ ስለሆንኩ ባርክ ተብዬ ሦስት [ሰዎች] በቤተክርስቲያን አሾልከን ቀብረናል፤ አይቻቸዋለሁ። አንዱ ሁለት ዓመት፣ ሁለተኛዋ 12 ዓመት ትሆናለች። አንዷ ትልቅ ሰው ናት የእነዚህ እናት ነች” ሲሉ ስለተገደሉት ሰዎች ተናግረዋል።

የ55 ዓመት እናቱ እንዲሁም አጎቱ የተገደሉበት ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ በሚኖርበት “ጎጥ” ውስጥ ቤተሰቦቹን ጨምሮ ሦስት ሽማግሌዎች እና ሁለት ሴቶች መሞታቸውን ተናግሯል። ነዋሪው፤ “የቀበሌው ሕዝብ ቤት አንድም የለም። እኛ ደንሳ ማሪያም ጎጥ ብቻ የተቃጠለው ቤት 170 ይሆናል” ሲል ሁኔታውን ገልጿል።

የ18 ዓመት ልጃቸው የተገደለባቸው ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፤ “ሥራ ላይ የነበረ” ልጃቸው የሞተው ታጣቂዎች “ከበው” ባደረሱበት ጥቃት መሆኑን አስረድተዋል።

በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ለመቅበር የሄዱ አንድ ነዋሪ “ሜዳ ላይ” ተቀብረው የአምስት ንጹሃን ሰዎችን አስከሬንን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን በቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የቀበሌው ሊቀ መንበር አቶ አለማየሁ በዚህ ጥቃት የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ብዛት “ከ80 በላይ” እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ደግሞ ሌሎች ነዋሪዎች የሟቾቹን ብዛት ከዚህ ከፍ ባለ አሃዝ የተለያዩ ቁጥሮችን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ ይህንን ሊቀ መንበሩም ሆነ ነዋሪዎች ያስቀመጧቸውን ቁጥሮች ከገለልተኛ አካል ማረገገጥ አልቻለም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍም ስለ ጥቃቱ እስካሁን ሪፖርት እንዳልደደረሰው ለቢቢሲ ገልጿል።

በሰዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት ባሻገር የነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ሰባቱም ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የወረዳው ባለሥልጣን፤ “ሀብት፣ ንብረታቸውን በሙሉ ዘርፈዋል፤ ከብቶች ላሞች ተዘርፈዋል፤ እህል አቃጥለዋል” ሲሉ ታጣቂዎቹን ከስሰዋል።

ጥቃቱ ሲፈጸም ለምን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንዳላስቆሙ ጥያቄ የቀረበላቸው ባለሥልጣኑ፤ “ከአቅም በላይ ነው። በወቅቱ አካባቢው ላይ ያለው ኃይል ዝቅተኛ ነበር። ጉዳዩን ክልል ድረስ አድርሰናል ግን ተጨማሪ ኃይል ማምጣት አልቻሉም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ “ከ10 ሺህ ያላነሱ” ነዋሪዎች ተፈናቅለው የቋራ ወረዳ መቀመጫ ወደሆነችው ገለጉ ከተማ መግባቱን ገልጸዋል። ወረዳው አስተዳደር የምግብ እርዳታ ማቅረቡንም አክለዋል።

በበጎ ፈቃደኝነት ተፈናቃዮዎችን በማስተባበር ላይ የተሰማሩ አንድ ነዋሪ የወረዳው አስተዳደር ለነዋሪዎቹ “የተወሰነ ብስኩት እና ወደ 50 ኩንታል እህል” ማቅረቡን አረጋግጠዋል።

ወደ ከተማዋ የገቡት ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ በነበረ ግቢ ውስጥ በሚገኙ ሁለት አዳራሾች ውስጥ እንዲቆዩ እንደተደረጉ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ይሁንና አዳራሾቹ ነዋሪዎቹን ሙሉ በሙሉ የመያዝ አቅም ስለሌላቸው የቀሩት ነዋሪዎች “ሜዳ ላይ” መውደቃቸውን አስረድተዋል።

የወረዳው ባለሥልጣን በተመሳሳይ፤ “[ተፈናቃዮች] የተጠለሉበት ቦታ ምቹ አይደለም። የተወሰነ ሼድ፣ ቆርቆሮ ያለበት ቦታ ነበር እዚያ ነው ያስቀመጥናቸው። ግን አብዛኞቹ ከዘመድ አዝማድ፣ ከሕብረተሰቡ ጋር ተጠግተው ነው ያሉት” ብለዋል።

የወረዳው አስተዳደር የምግብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን ያነሱት ባለሥልጣኑ፤ “የፀጥታ ችግር በመኖሩ [እርዳታ] ለማምጣት ችግር ውስጥ ነን። [እርዳታው] በእጀባ ነው የሚመጣው። እጀባ እስከሚመጣ ጠብቁ” የሚል ምላሽ መገኘቱንም ገልጸዋል።

ቢቢሲ ለክልሉ እና ለምዕራብ ጎንደር ዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ተቋማት ኃላፊዎች ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች አልተሳኩም።