ጥቁር ሰሌዳ እና አንገቱን ደፍቶ ከጀርባው የሚታይ መምህር

ከ 5 ሰአት በፊት

የኑሮ ውድነት እና የቤት ኪራይ ጫና ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በሚያስተምሩበት ተቋም ውስጥ ለተማሪዎቻቸው በተዘጋጁ የማደሪያ ክፍሎች ውስጥ መኖር ግድ ሆኖባቸዋል።

የዩኒቨርሲቲው መምህራን በክልሉ ውስጥ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ለሁለት ዓመታት የተከማቸባቸው የቤት ኪራይ ዋጋ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው ከባድ ያሉትን አማራጭ ለመውሰድ እንደገደዱ ይናገራሉ።

በተለይ አገታቸውን የሚያስገቡበት ቤት ኪራይን ለመክፈል እንደተቸገሩ በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው ጊዜያዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የጠየቁ አንዳንድ መምህራን ለጊዜው በተማሪዎች መኖሪያ (ዶርም) ውስጥ ለመኖር ተፈቅዶላቸዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ ከባድ ችግር ውስጥ የገቡት የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ያልተከፈለ ውዝፍ ደሞዝ እንዳላቸው ይናገራሉ። የመቀለ ዩኒቨርሲቲውም ለ17 ወራት እና ከዚያም በላይ ደመወዝ ያልተከፈላቸው ከ8,000 በላይ ሠራተኞች አሉኝ ይላል።

በዚህም የተነሳ በርካታ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች እየተዳረጉ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው መምህራን ይገልጻሉ።

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ብዙ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሥራቸውን ለቅቀው ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ስጋትም ተቋሙ አለው።

በክልሉ የዩኒቨርስቲ መምህራን ኑሮና ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት መምህራን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

‘ተማሪዎቼ እንዳያዩኝ ተደብቄ ነው የምገባው’

ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አንደኛው መምህር ለሰባት ዓመታት ያህል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት አገልግለዋል።

ምንም እንኳን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህር ቢሆኑም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የልጆቻቻው እና የራሳቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ከማይችሉበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

“ሁሌም ሥራ ውዬ ወደ ቤቴ ስመለስ ኪሴ ባዶ ስለሆነ ልጆቼ እጅ እጄን ሲያዩ እሳቀቃለሁ። ልጆቼ ያዩትን ነገር እንዳይጠይቁኝ ስለምሳቀቅ ወደ ውጭ ይዣቸው አልወጣም። በዚህም ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እየተዳከመ መምጣቱን ስለምረዳ፤ ሥነ ልቦናችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው።”

በአገሪቱ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ የተሻለ ነው ባይባልም ቀደም ባሉት ዓመታት ከቀን ወደ ቀን ለመሻገር ግን ከብዷቸው እንደማያውቅ የሚናገሩት መምህሩ፣ ከትግራይ ጦርነት በኋላ ግን ሁሉም ነገር በአስከፊ ሁኔታ መቀየሩን ይናገራሉ።

አንድ ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ የቤተሰባቸውን መሠረታዊ ነገሮች የሚሸፍንላቸው ወርሃዊ ደሞዝ በመቆሙ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል።

“በጦርነቱ ወቅት በየቀኑ በረሃብ የሚሞቱ ብዙ ሰዎች ነበሩ። እንደ ዕድል ሆኖ በረሃብ ካልሞቱት ግን ደግሞ ሆዳቸውን ሞልተው ለማደር ካልታደሉት የመንግሥት ሠራተኞች መካከል አንዱ ሆኜ ነው አሳለፍኩት።”

የጦርነቱን ወቅት የቤተሰባቸውን ቀዳዳ ለመሸፈን በየቀኑ ከዚህም ከዚያም እየተበደሩ መቆየታቸውን የሚናገሩት የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ፤ ሰላም ከወረደ በኋላ “ደመወዝ መከፈል ሲጀምር የተወሰነ ምሳ እና እራት በልቼ የምውልበት ዕድል አግኝቼ ነበር” ይላሉ።

ነገር ግን የሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ እና እና የገበያው ሁኔታ ያልተመጣጠነ እየሆነ፣ እንዲሁም ከዕለት ዕለት እየባሰበት የሄደው የዋጋ ንረት ኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ መጣ።

“ደሞዛችን ላይ የታየ ምንም ለውጥ አልነበረም። ስለዚህ ኑሮን መምራት፣ ልጆቼን ማስተማር፣ ልብስ መቀየር እና በልቶ ማደር ከባድ ሆኖ ተቸገርን።”

በጦርነቱ ወቅት የኖሩበት እና ያልከፈሉት የተጠራቀመ የቤት ኪራይ እዳ እንዲሁም አከራዮች ኪራይ በመጨመራቸው ከባድ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን በመጥቀስ ወጪያቸውን ለመቀነስ እና ከሁኔታ ጋር ተስማምቶ ለመኖር “ቤተሰቤን ይዤ ባለ አንድ ክፍል ቤት ተከራይቼ ገባሁ” ይላሉ።

በአንዲት ክፍል ውስጥ “እንጀራ እንጋግራለን፣ ምግብ እናዘጋጃለን፣ ልጆቻችንንም ይዘን እዚያችው ክፍል እንተኛለን” በማለት በርካታ ቤተሰብ ያላቸው ባልደረቦቻቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ከባድ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ደሞዛቸው አስር ሺህ ብር የማይሞላው እኚህ መምህር የቤት ኪራይ ቢያንስ 5,000 ብር ከፍለው በቀረው ውሃ እና ኤሌክትሪክ፣ ምግብ እና የልጆችን ትምህርት ወጪን መሸፈን ፈተና ሆኖባቸዋል።

“ከዚች ደሞዝ ላይ አሁን ባለው ገበያ እህል ተገዝቶ ለዕለት አስቤዛ የሚሆን ነገር ማትረፍ አይቻልም። ህመም ካጋጠመም መታከሚያ አይኖርም። ልጆችም የመማር ዕድላቸው እየጨለመ እየሄደ ነው” ሲሊ ያማርራሉ።

እንግዲህ ይህ ሁኔታ ነው መምህሩን እና ሌሎች ባልደረቦቻቸውን ተማሪዎቻቸው በሚኖሩበት የዩኒቨርሲቲው ዶርም ውስጥ መጠለያ እንዲሰጣቸው እንዲጠይቁ ያስገደዳቸው።

ያሉበት ችግር በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖሩ ቢያደርጋቸውም በዚህ ሁኔታ ግን ደስተኛ አይደሉም “ሥራ ውዬ ለተማሪዎች ወደተዘጋጀው ማደሪያ ስሄድ ሳስተምራቸው የዋልኩትን ልጆች እዚያ አገኛቸዋለሁ፤ ይህም ምቾት አይሰጠኝም . . አልፎ አልፎ ተደብቄ የምገባበት ሁኔታ አለ።”

ይህ ሁኔታ ሥነ ልቦናን የሚጎዳ፣ ሞራልንም የሚያዳክም ነው የሚሉት መምህሩ፤ ውጤቱም መምህራኑን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የተማሪዎችም ፈተና ነው ይላሉ።

“እኔ የማስተምረው ዜጋ በሥነ ልቦና እና በኢኮኖሚ ከተማሪው ያልተሻልኩ ከሆንኩ ትምህርት በኑሮ ላይ በገቢ ላይ ለውጥ አያመጣም የሚል ግንዛቤን ይፈጥራል።”

ነገር ግን በዚህ ጊዜ መምህሩ ከተማሪው የተሻለ ነገር ስለሌለው ከባድ ጫና አለው በማለት፣ ያሉበት ሁኔታ የፈጠረባቸው ስሜት ፈታኝ መሆኑን ይገልጻሉ።

“የበታችነት ስሜት ይሰማኛል። በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት በሥነ ልቦናው የተዳክመ መምህር ተማሪው ፊት ቆሞ ማስተማር በጣም የሚያስጨንቅ ነው። የዩንቨርሲቲ መምህር ተብለህ የተቀደደ ጫማ እና ልብስ ለብሰህ ስትገባ ያሳፍራል፤ እናም የበታችነት ስሜት ይሰማሃል። ይህን ያክል ነው ስነ ልቦናችን የተጎዳው።”

በተጨማሪም አገር ብዙ ሃብት አፍስሳ ያስተማረቻቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራን ባለው የኑሮ ሁኔታ ተዳክመው እና ተስፋ ቆርጠው ወደ ስደት ለመሄድ የሚያስቡ እንዳሉ ይናገራሉ። ይህም በጣም የሚያሳዝን እና ትልቅም ኪሳራ ነው ይላሉ።

እሳቸውም ቢሆኑ ስደትን ባያስቡትም መምህርነቱን በመተው ወደ ሌላ ሙያ ፊታቸውን ማዞር ያልቻሉበት ዋነኛው ምክንያት “ሌላ ሥራ ለመጀመር አቅም ስለሌለኝ፣ ከወጣሁ ቶሎ ሥራ ላላገኝ ስለምችል እና ቤተሰቦቼም ችግር ውስጥ ይገባሉ” በሚል ስጋት መሆኑን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ መምህራን በርካታ መሆናቸውን የሚጠቅሱት የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው፤ ኑሯቸው በተለያዩ መስኮች አገር እና ሕዝብን የሚያገለግሉ ሙያተኞችን እንደሚያስተምር ባለሙያ ሳይሆን ከዚያ ባነሰ ሁኔታ መሆኑን በምሬት ይናገራሉ።

ለተማሪዎቻቸው የሚሆን ዕውቀትን ከመቀመር፣ ጥናት እና ምርምር ላይ ከማተኮር ይልቅ ስለዕለት ከዕለት ኑሯቸው፣ ስለ ቤተሰባቸው ቀጣይ ሕይወት እንዲሁም ከአከራይ ጀምሮ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች የሚጠብቁትን ዕዳቸውን እያሰቡ መሆናቸው በሰቀቀን ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

እነዚህን መምህራን ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት መንግሥትም ሆነ ዩኒቨርሲቲውም ለመምህራን የሚሆን መኖሪያ ማመቻቸት እና እስካሁን ያልተከፈላቸውን ደሞዝ መክፈል አንድ እርምጃ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

መቀለ ዩኒቨርስቲ

‘እንኳንም ትዳር እና ልጆች አልኖሩኝ’

በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የዓዲ ሓቂ ግቢ መምህር የሆኑት ሌላኛው መምህር ደግሞ “ብሩህ ተስፋ የነበረው ሕይወት፣ ጥሩ የሥራ መንፈስ ነበረኝ። በትምህርት እና በሙያዬ ራሴን በማሳደግ እና በመማር ላይ አተኩሬ ነበር” ይላል።

የዩኒቨርሲቲ መምህር ተብሎ የተሻለ ማኅበራዊ ተቀባይነት እና ክብር ነበረኝ የሚለው መምህሩ፤ በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜውን በምርምር እና በማስተማር አሳልፏል።

በዚህ ሙያ ለስምንት ዓመታት ያህል በመቀለ ዩኒቨርሲቲ እና በአገሪቱ በሚገኙ በተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አስተምሯል።

አሁን ግን በአገሪቱ ውስጥ ባለው አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት እንዲሁም በኢኮኖሚ መዳከም ምክንያት በተከሰተው የዋጋ ንረት እና በወር የሚያገኘው ደሞዝ መሠረታዊ ፍላጎቱን ሚያሟላ አቅም ስለሌለው “በሚያስጨንቅ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እገኛለሁ” ብሏል።

“የምፈልገውን ምግብ መብላት፣ ራሴን አድሼ ወደ ሥራ መመለስ ወደምችልበት ቦታ መሄድና ምርምሬን እና ትምህርቴን ማከናወን እየከበደኝ ነው።”

የተፈጠረው ቀውስ እና የሰላም እጦቱ ብዙ ሰዎችን ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል፤ በትግራይ ያለውን ሁኔታ የከፋ የሚያደርገው ጦርነቱ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ መሆኑን መምህሩ ያምናል።

በተለይም የመንግሥት ሠራተኛው ከደረሰበት የሕይወት እና የንብረት ውድመት ባለፈ ዕዳ በመክፈል ላይ ተጠምዷል በማለት፤ እሱም “የ18 ወራት የቤት ኪራይ ዕዳ 38,000 ብር” እንዳለበት ይናገራል።

መምህሩ በፊት ይከፍለው የነበረው የቤት ኪራይ ዋጋ ጨምሮ 3,500 ብር ሆኗል። ይህም ካለበት ዕዳ ጋር ተደምሮ በወር ወደ ስድስት ሺህ ብር እንዲከፍል ስለተጠየቀ ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር እንደገጠመው ይነገራል።

የተጠየቀውን ገንዘብ ከፍሎ በተከራየው ቤት ውስጥ ለመኖር ቢወስን የሚቀረው ገንዘብ መሠረታዊ ፍላጎቱን በትንሹ አሟልቶ የሚያኖረው ባለመሆኑ አስቸጋሪ የሚለውን አማራጭ ተቀብሎታል። ይህም ሳይወድ በአስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት እንደ ሌሎቹ ባልደረቦቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ማደሪያ መግባት።

ይህ ሁኔታ ግን ለህሊናው እረፍትን የሚሰጠው አልሆነም “የሚያስከትለው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ተማሪዎች በምኖርበት አካባቢ ሲያገኙኝ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም” ይላል።

ተማሪዎቹ ይህንን እያዩ የወደፊት ዕጣቸው ከዚህ የተሻለ እንደማይሆን እንዲያስቡ እና “ትምህርት የተሻለ ኑሮ ካላመጣ ፋይዳው ምንድነው?” የሚል አስተሳሰብ ሊፈጠርባቸው ይችላል የሚል ስጋት አለው።

በዚህ ሁኔታ ብቻውን ለእራሱ የሚሆን አቅም እንደሌለ ሲመለከት ቤተሰብ እና ልጆች ያላቸው የባልደረቦቹ ሁኔታ ከእሱም የከበደ መሆኑን ይናገራል። በዚህም ምክንያት “አሁን ላይ ሆኜ እንኳንም ትዳር እና ልጆች አልኖሩኝ እላለሁ” ይላል።

“በእርግጠኝነት መናገር የምችለው መምህሩ እና ተመራማሪው. . . በዚህ ሥራ ላይ መቀጠልን አይፈልጉም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አንዳንዶች ከአገር ለመውጣት. . . እየቋመጡ ነው። በዚህ ከቀጠለ ዩኒቨርሲቲው በማንኛውም ጊዜ ሊዘጋ ይችላል።”

እሱም ቢሆን ከመነሻው በደስታ እና በብሩህ ተስፋ የተቀላቀለውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህርነቱን በመተው ወደ ሌሎች ዘርፎች ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት አለው።

“እኔም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተንቀሳቀስኩ ለመሥራት፣ ካልሆነ የተሻለ ገቢ ወደ ማገኝበት የትምህርት ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ መሳተፍ ነው የምፈልገው። ይህ ማለት በተማርኩት ትምህርት የተሻለ ገንዘብ ማግኘት የምችልባቸውን እድሎችን እየፈለግኩ ነው።”

የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ምን ይላል?

የመቀለ ዩኒቨርሲቲ 2,500 መምህራንን ጨምሮ ከ8,000 በላይ ሠራተኞች ያሉት በክልሉ ያለ ትልቁ የፌዴራል መንግሥቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው።

የትግራይን ጦርነት ተከትሎ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ለ17 ወራት ያህል ደሞዝ ሳይከፈላቸው ቆይተዋል። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ዩኒቨርሲቲው ወደ መደበኛ ሥራው ቢመለስም ውዝፍ ደመወዝ ግን መክፈል አልቻለም።

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ለቢቢሲ እንደገለጸው ባለው ሁኔታ ምክንያት “በመምህራን እና በሠራተኞች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተፈጠረ ነው” በማለት የፌደራል መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ መጠየቁን ገልጿል።

“ዩኒቨርሲቲው ሥራ ሲጀምር ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርበናል። እየጠየቅንም ነው። ነገር ግን እስካሁን አይከፈልምም፣ ይከፈላልም አላሉንም” ሲሉ የአካዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልቃድር ከድር ተናግረዋል።

“የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም መጥተው ያለንበትን ሁኔታ ገምግመው በሪፖርታቸው ላይ የሠራተኞች ገንዘብ እንዲከፈል አሳስበዋል” ነገር ግን እስካሁን ምንም ዓይነት ተግባራዊ ምላሽ እንዳላገኙ ይጠቅሳሉ።

በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ሠራተኞቻቸው በተለያዩ ዕዳዎች ምክንያት ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በዚህም ምክንያት 100 ለሚደርሱ መምህራን ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት በሚል ለተማሪዎች ማደሪነትያ በተዘጋጁ ክፍሎች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀው ማግኘት ያልቻሉ መምህራን እንዳሉ ዶክተር አብዱልቃድር ለቢቢሲ ገልጸዋል።