JULY 21, 2024

ናታን ዳዊት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ወደፊት ያራምዳል ያላቸውን የተለያዩ ዕርምጃዎች እየወሰደ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ሥር ነቀል ሊባሉ የሚችሉም ናቸው፡፡ ባለፉት ሁለት ወሮች ደግሞ በማከታተል ያመጣቸው ሕጎች፣ መመርያዎችና ፖሊሲዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው።

ከባንክ አሠራር ጋር የተያያዙ የተለያዩ መመርያዎች ማሻሻያዎች የተደረገባቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ ዘርፉን ለማዘመን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ሊበረታቱ የሚችሉ ድንጋጌዎች እንዲተገበሩም እያደረገ ነው፡፡

ከባንክ አሠራርና ቁጥጥር ሥራ ጋር እየተደረጉ ካሉ ማሻሻያዎች ባሻገር የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ ከዓመት በፊት ይፋ የተደረገውና እየተተገበረ የሚገኘው የገንዘብ ፖሊሲም ቢሆን የታለመለትን ውጤት እያስገኘ ስለመሆኑ ባንኩ አሳውቋል፡፡ ከሰሞኑም አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ በማድረግ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ይህ ማዕቀፍ ሊያስገኘው የሚችለው ውጤት ወደፊት የሚታይ ሲሆን፣ ሌሎች አዳዲስ ማሻሻያዎች ይወጣሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ሊያደርግበትና በደንብ ሊፈትሻቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔ በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ከአሳሳቢነቱ አንፃር ምንም እየተባለበት አለመሆኑ ሊጠቀስ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ የሆነ አበርክቶ ያላቸው ባንኮች ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች በተለየ ያልተቋረጠ ዕድገት እያስመዘገቡ ሦስት አሠርት ዓመታትን የማስቆጠራቸውን ያህል በኢኮኖሚው ላይ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተጋነነ የብድር ወለድ ምጣኔያቸው ያለ ገደብ እንዲሠሩበት መደረጉ ነው፡፡ 

በአገራችን ባንኮች አሁን እያሳዩ ያሉት ያልተቋረጠ ዕድገት ጤናማነት ላይ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች አንደኛው መሞገቻ ነጥባቸው ባንኮች በየዓመቱ የተንበሸበሸ ትርፍ የሚያውጁት በተጋነነ የብድር ወለድ ምጣኔ በተበዳሪዎች ላይ በመጣላቸው ነው፡፡ 

እጅግ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት ፍላጎት መኖሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን ከፍ በማድረግ ከፍተኛ ትርፍ እያገኙ መቀጠላቸው ጤናማ አለመሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች ሲጠቅሱ ይሰማል፡፡ የአገራችን ባንኮች ዛሬ እስከ 22 በመቶ በሚደርስ የወለድ ምጣኔ ብድር እየሰጡ መሆኑ የአገሪቱን የዋጋ ንረት በማባባስ ረገድ ያላቸው ሚና እየጎላ መምጣቱ ደግሞ ጉዳዩ የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ብዙ ሥራ ይቀረዋል የሚባልበት አንዱ ምክንያትም ይህንን የብድር ወለድ ምጣኔ የተመለከተ ምንም ዓይነት ዕርምጃ ያለመወሰዱ የብድር ወለድ ምጣኔ ያለገደብ እየተለጠጠ እንዲቀጥል እያደረገ ነው፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ዝቅተኛ የተቀማጭ ገንዘብ የወለድ ምጣኔን ከማስቀመጥ ሌላ ባንኮች ብድር ሲሰጡ የሚያበድሩበትን የወለድ መጠን አለማስቀመጡ ባንኮች ያዋጣናል ባሉት መንገድ እንዲጓዙ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ ከፖሊሲ ባንኮች ውጪ ያሉት ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔያቸው በአብዛኛው ከ18 እስከ 22 በመቶ ሆኗል፡፡ ከዚህ በላይ ወለድ የሚጠየቅባቸው የብድር ዓይነቶች እንዳሉም ይገልጻልና ይህ አካሄድ ማቆሚያ ከሌለው ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ቀላል አይሆንም፡፡ 

እርግጥ ነው በገበያ የሚመራ ኢኮኖሚ ውስጥ የብድር ወለድ ምጣኔ በገበያ መወሰን አለበት፡፡ ነገር ግን ጤናማ ገበያና ጤናማ ውድድር በሌለበት የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ባንኮች ያሻቸውን የወለድ ምጣኔ እያስከፈሉ እንዲቀጥሉ መፍቀድ ተገቢነቱ ሊጤን ይገባል።

ባንኮች በፈለጉት ወለድ ምጣኔ ብድር መስጠታቸው ከቢዝነስ አንፃር ተገልጋይ እስካለ ምንም ችግር ላይኖረው ይችላል የሚል ግንዛቤ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አንድ የቢዝነስ ተቋም ቀዳሚ ግቡ ትርፍ ማግኘት የባለ አክሲዮኖችን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ምጣኔን ማሳደግ ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል፡፡ ይሁንና የብድር ወለድ ምጣኔ በየጊዜው እየተለጠጠ የትርፍ ምጣኔን በማሳደግ ባለአክሲዮችን ለማስደሰት ብቻ ያለመ ከሆነ እንደ አገር ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ 

ባንኮች የወለድ ምጣኔ በጨመረ ቁጥር ጭማሪው ተበዳሪው ላይ ጫና በማሳረፍ የሚወሰን ብቻ ያለመሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ በአብዛኛው የአገራችንን ገበያ ያጥለቀለቁት የገቢ ምርቶች የሚመጡት በብድር ከመሆኑ አንፃር የብድር ወለድ ምጣኔው ከፍ ባለ ቁጥር እነዚህ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ዋጋን እያናረ ነው፡፡ በተጋነነ የብድር ወለድ የሚካሄድ ኢንቨስትመንትም ሆነ አገልግሎት መጨረሻ ላይ ሸክሙ የሚያርፈው ተገልጋይና ሸማች ላይ ከሆነ ይህ አካሄድ ማቆሚያ እንዲኖረው ያልተደረገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ የብድር ወለዱ በዛብኝ ብሎ ብድሩን ካለመውሰድ የሚታቀብ ወይም በአደባባይ ይህንን ደፍሮ የሚናገሩ ነጋዴዎች እምብዛም የማይታዩት የብድር ምጣኔውን ወደ ሸማቹ እንደሚያስተላልፉት እርግጠኛ በመሆናቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲዎችና ከባንክ አሠራር ጋር በተያያዘ እያደረጋቸው ያሉ ማሻሻያዎች እንዲህ ያለውንም ጉዳይ ሊመለከት ይገባል፡፡

ዛሬ የተለጠጠ ነው የሚባለው የአገራችን የብድር ወለድ ምጣኔ የዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑና ይህ ሸማችና ተገልጋይ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ባይታበልም ይህ ተገኘ የሚባለው የብድር ወለድ ምጣኔ ሄዶ ሄዶ ባንኮቹንም ሊጎዳ እንደሚችል መታመን አለበት፡፡ 

በተለይ የውጭ ባንኮች ሲገቡ አንዱ መወዳደሪያቸው በተመጣጠነ የብድር ወለድ አሸናፊ ሆኖ መውጣት ስለሆነ አሁን ባለው የወለድ ምጣኔያቸው ባንኮቻችን እንዴት ተወዳዳሪ ይሆናሉ የሚለው ነገርም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ 

የአገራችን ባንኮች የተጣጠነ ትርፍ እያገኙ ዕድገታቸው እንዲቀጥል ከተፈለገም ከተጋነነ የብድር ምጣኔ ብቻ ሳይሆን ከተጋነነ የትርፍ ምጣኔ ወጥተው ተወዳዳሪ ወደሚያደርጋቸው አሠራር መግባት ግድ ይላል፡፡ 

በገበያ ውስጥ ለመቆየት ደግሞ ከብድር ወለድ ትርፍ ባሻገር በሌሎች አገልግሎታቸው የሚያገኙትን ጥቅም ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ አሠራር ሊዘረጉ ይገባል፡፡ በተለይ ባለአክሲዮኖች በዚህ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ ትርፋችን አነሰ የሚሉና ለምን ይህንን ያህል አላተረፍክም ብለው የሚሞግቱ ባለአክሲዮኖች የሚፈጥሩት ጫና ባንኮች የብድር ወለድ መጠንን በማሳደግ የባለአክሲዮኖችን ጫና ለመቋቋሙ የሚጠቀሙበት ዘዴ ሆኗል መባሉም እንደዋዛ የሚታለፍ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ የባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔ ዕድገት ብዙ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም፣ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችና ባለአክሲዮኖችም ድርሻ ከፍተኛ ሊሆን ይገባል፡፡ በሰባት በመቶ ተቀማጭ እየሰበሰቡ በ22 በመቶ ብድር ማቅረብ ምን ያህል ጤናማ ነው የሚለውም ነገር መልስ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡