
ከ 1 ሰአት በፊት
የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዋና ከተማዋ አሥመራ የሚያደርገው በረራዎች ከመስከረም አጋማሽ በኋላ እንዲቋረጡ ወሰነ።
በኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዛሬ በታተመው በመንግሥታዊው “ሓዳስ ኤርትራ” ጋዜጣ ላይ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መታገዱን የገለጸው።
ባለሥልጣኑ በጋዜጣው ላይ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርጋቸው በረራዎችን በሙሉ ማገዱን አስታውቋል።
የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ በጋዜጣ ላይ ባወጣው መግለጫ አየር መንገዱ እንዲታገድ የተወሰነው በኤርትራውያን መንገደኞች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ” የሆነ በደል በማድረሱ ነው ብሏል።
አየር መንገዱ አግባብ ባልሆነ ሂደት ሆነ ብሎ “የተጓዦች ሻንጣዎች ላይ ስርቆት ይፈጸማል”፣ በተደጋጋሚ የበረራዎች እና የሻንጣዎች መዘግየት እንደሚያጋጥም ጠቅሶ፤ አየር መንገዱ ለተጓዦች ካሳ ሳይሰጥ ቆይቷል ብሏል።
ጉዳዩን በተመለከተ ቢቢሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
- ከሦስት ሳምንት በፊት ገርበ ጉራቻ ላይ ስለታገቱት ተማሪዎች ወላጆች ምን የሰሙት ነገር አለ?ከ 5 ሰአት በፊት
- በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 229 ደረሰ23 ሀምሌ 2024
- ህወሓት የቀደመ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ አንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ አስታወቀ23 ሀምሌ 2024
የኤርትራ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አየር መንገዱን ለማገድ ከወሰነበት ምክንያቶች ሌላኛው የበረራ ቲኬቶች ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ ነው ብሏል።
“ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች እንዲቀረፉ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጡ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች ውጤት ማስገኘት ባለመቻላቸው ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚደረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች እንዲታገዱ ተደርገዋል” ብሏል።
የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦች ባወጣው መልዕክት ከመስከረም 20 በኋላ በአየር መንገዱ በረራ ለማድረግ ያቀዱ መንገደኞች ቀድመው ማስተካከያ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የኤርትራ መንግሥት አየር መንገዱን ከመስረም 20 በኋላ አግጃለሁ ቢልም አየር መንገዱ ግን አሁንም በድረ-ገጹ እና በቲኬት መሸጫ ቢሮዎቹ ከመስከረም 21 በኋላ ለሚደረጉ በረራዎች የአየር ቲኬቶችን እየሸጠ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ወደ አሥመራ በሳምንት አምስት በረራዎችን ያደርጋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ የሳዑዲ አረቢያ፣ የቱርክ እና የግብፅ አየር መንገዶች ወደ አሥመራ መደበኛ በረራዎችን አሏቸው።
በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጣልያን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የጣልያን አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በረራ እንዲጀምር ስምምነት መደረሱ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያካሄዱት ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የአውሮፕላን ጉዞ ሐምሌ/ 112010 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ጦርነትም ሆነ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ቆይታው የነበሩት አሥመራ እና አዲስ አበባ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን ተከትሎ ነበር በረራ የጀመረው።
በወቅቱ የሁለቱ አገራት መሪዎች “የአሥመራ ዲክላሬሽን” የተሰኘ ስምምነት ተፈራርመው ከአየር በረራ በተጨማሪ ተቋርጠው የነበሩት የየብስ ትራንስፖርት፣ የንግድ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ዕድል ፈጥሮ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱን አገራት የሚያዋስኑ የድንበር በሮች በሙሉ ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ታድሶ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሰሜን ኢትዮጵያ የእርሰ በርስ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ መልሶ መሻከሩ ይገለጻል።
በሰሜኑ ጦርነት የኤርትራ መንግሥት ከፌደራሉ መንግሥት ጎን ተሰልፎ የትግራይ ኃይሎችን ሲወጋ መቆየቱ ይታወሳል።