መሳሪያ የታጠቀ

24 ሀምሌ 2024, 07:05 EAT

ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሦስት አውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ ቁጥራቸው በውል ካልታወቀ ሌሎች መንገደኞች ጋር በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ ከታገቱ ሦስት ሳምንት ሆናቸው።

ከ100 በላይ የሚሆኑት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለክረምት እረፍት አውቶብስ ተኮናትረው ከደባርቅ እና ከባሕር ዳር ከተማ ተነስተው በመጓዝ ላይ እንዳሉ መታገታቸውን የዐይን እማኞች እና የታጋች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አጋቾቹ ተማሪዎችን እየደበደቡ ከተሽከርካሪዎች ካስወረዱ በኋላ ወደ ገጠራማ አካባቢ ለሰዓታት በእግራቸው ይዘዋቸው እንደተጓዙ ከእገታው ያመለጡ እና ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ ተማሪዎች ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ መንገደኞችን ይዘው አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ከተጓዙ በኋላ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎቹ መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉንም የዐይን እማኞች መግለጻቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት ባለው እርምጃ 160 የሚሆኑ ታጋቾችን አስለቅቄያለሁ ቢልም፤ ቤተሰቦች ግን ተማሪዎቹ አሁን በእገታ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

አጋቾቹ የማስለቀቂያ ገንዘብ ከ500 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የተጠየቁ ሲሆን፣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች (ሌሎች መንገደኞችን ጨምሮ) በእገታ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር 106 እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እገታው በተፈጸመበት ጊዜ ታጋቾቹ በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ በነበረው ግርግር መካከል የተወሰኑ ተማሪዎች ያመለጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ተማሪዎች በተለያዩ ቡድኖች እና አቅጣጫ በመክፈል ለሁለት ሰዓታት ያህል በእግር ራቅ ወዳለ ስፍራ እንደወሰዷቸው ታጋቾቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በነበራቸው የስልክ ልውውጥ ተናግረዋል።

በመጀመሪያዎቹ የእገታው ቀናት ታጣቂዎቹ 30 የሚሆኑ ተማሪዎችን “ለይተው. . . ያላቸውን ገንዘብ በመውሰድ” መልቀቃቸውን ለደኅንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስምንት የሚሆኑ ተማሪዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው የማስለቀቂያ ገንዘብ በቤተሰቦቻቸው አማካይነት ለአጋቾቹ ከፍለው ተለቀዋል።

“በነጻ” የተለቀቁት ናቸው የተባሉ ተማሪዎች በአካባቢው ነዋሪዎች መንገድ እየተመሩ ወደ ቱሉ ሚልኪ ከተማ እንደተላኩ የጠቆሙት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ምንጭ፤ “መጀመሪያ በተጓዙበት መኪና” ወደ አዲስ አበባ እንደተወሰዱ ጠቁመዋል።

የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ ተማሪዎች ደግሞ ገርበ ጉራቻ ከተማ በአካባቢው ወጣቶች ታጅበው ከደረሱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ሻንጣቸውን አውቶብስ ተራ መሰብሰብ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

ከተለቀቁ ተማሪዎች እና ከታጋች ቤተሰቦች በተገኘ መረጃ የታገቱት ተማሪዎች የሚገኙት ሰው ከማይደርስበት ድብቅ ጫካ ውስጥ ሳይሆን ጎጆ ቤቶች በሚገኙበት መንደር ውስጥ ነው።

ታጋቾቹ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ጎጆ ቤቶቹ ውስጥ ተቀምጠው በታጣቂዎቹ እየተጠበቁ መሆናቸውን ከተማሪዎቹ ጋር ስለማስለቀቂያ ገንዘቡ በስልክ የሚያወሩ ወላጆች መረዳታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ወንዶች እና ሴቶች ተለያይተው እንዲሁም ተቀላቅለውም እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በመጀመሪያዎቹ ቀናት ምግብ ከመንደሮቹ እያመጡ ይሰጧቸው የነበረ ሲሆን፤ እየቆየ ግን የምግብ አቅርቦቱ መቀነሱን ተማሪዎቹ ጠቁመዋል። አንድ ከእገታው የተለቀቀ ተማሪ በቀን አንድ “ኮቾሮ” ይሰጣቸው እንደነበር ተናግሯል።

“‘ምግብ በቀን አንድ ጊዜ ይሰጠናል። እስካሁን ልብሳችንን አልቀየርንም። ባለው ነው የምናድረው’” የሚል መልዕክት ከልጃቸው መስማታቸውን አንድ ወላጅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ያለመደረቢያና መቀየሪያ ልብስ” ሲወጡ በለበሱት ልብስ ለሳምንታት እንዲቆዩ የተገደዱት ተማሪዎች አካባቢው ብርዳማ መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ስለ አጋቾቻቸው ሲናገሩም ፀጉራቸውን ያሳደጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ታጣቂዎቹ ፊታቸውን በጭምብል እንደማይሸፍኑ ገልጸዋል።

አጋቾቹ ገንዘብ የመክፈል አቅም አላቸው ብለው ላሰቧቸው ቤተሰቦች ቶሎ ቶሎ እንደሚደውሉ የተናገሩት የቢቢሲ ምንጭ፤ አቅም እንደሌላቸው ለገለጹ ቤተሰቦች ግን ከሳምንት በላይ ለሚሆን ጊዜ እንደማይደውሉ ጠቁመዋል።

ቢቢሲ ካናገራቸው በርካታ ምንጮች አብዛኞቹ ታጋች ተማሪዎች ከሲዳማ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፤ ቤተሰቦች ለክልል መንግሥታት እና ለፌደራል የፀጥታ ተቋማት ስለ እገታው ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን እና ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ቢቢሲ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት የፀጥታ አካላትን ለማነጋገር ለቀናት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የታጋች ቤተሰቦችም አማራጭ ማጣታቸውን ጠቁመው፤ በመንግሥት ላይ ተስፋ ቆርጠው ሁሉን ነገር “ለፈጣሪ” በመተው የሚሆነውን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቤተሰቦች የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመክፈል አቅም እንደሌላቸው ጠቁመው፤ ገበያ፣ በአብያተ ክርስቲያናት እና በአውቶብስ መናኽሪያ አካባቢ ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

“ግራ እንደገባን ነው። ፈጣሪን ወደ ላይ እየጠየቅን ነው፤ አቅም ስሌለለን ዝም ብለናል። ከተያዙ 21 ቀናቸው ነው። አማራጭ ስለሌለን ግራ ገብቶናል” ሲሉ 700 ሺህ ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ የተጠየቁ ወላጅ በምሬት ተናግረዋል።

ልጃቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ያናገሩት ከቀናት በፊት ገንዘቡን ስለማግኘታቸው ሊጠየቁ በተደወለላቸው ጊዜ መሆኑን የጠቀሱት አባት፤ ልጆቹ በምን ዓይነት ሁኔታ ወስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

ከልጃቸው ጋር ሰኞ ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም. በስልክ እንደተነጋገሩ የገለጹ ሌላ ወላጅ ደግሞ፤ ከተጠየቁት 500 ሺህ የማስለቀቂያ ገንዘብ ውስጥ 200 ሺህ ብር ማሰባሰብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም አጋቾች ሁሉንም የተጠየቁትን ገንዘብ ማሟላት እንዳለባቸው ነግረውናል ያሉት የቤተሰብ አባሉ፤ ገንዘቡን ማሰባሰቡን እንድንቀጥልበት አሳስበውናል ብለዋል።

“መንግሥት ባለበት አገር እንዴት ልጆቻችን ላይ፤ ተማሪዎች ላይ እንዲህ አይነት ነገር ይፈጸማል? የተደረገው ነገር ግራ የሚያጋባ ነው” ሲሉ ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ጠቁመው ወላጅ ተስፋቸው “ፈጣሪ” ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ለእግዚአብሔር መስጠት ነው እንጂ በእኛ በኩል መፍትሄ የለንም” ያሉ አንድ የታጋች ቤተሰብ ከመንግሥት በጎ ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የተወሰደው እርምጃን የለም ብለዋል።

ከታገቱ ሦስት ሳምንታት የሞላቸው ተማሪዎች ቤተሰቦች መካከል ተስፋ ቆረጠው በከፍተኛ ሐዘን ወስጥ የሚገኙ ወላጆችን ቢቢሲ ለማናገር ባደረገው ጥረት በሁሉም ነገር ተስፋ በመቁረጣቸው የልጆቻቸውን ነገር “ለፈጣሪ” በመተው ምንም ነገር መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

እገታውን ፈጽሟል የተባለው በአሸባሪነት የተፈረጀው እና መንግሥት “ሸኔ” የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከእገታው ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ በድርጊቱ ወስጥ እጁ እንደሌለበት በመግለጽ መንግሥትን መክሰሱ ይታወቃል።