July 30, 2024 – EthiopianReporter.com 

በጌታነህ አማረ

የውጭ ምንዛሪ (Foreign Exchange) ማለት በአጭር አማርኛ እንደ አንድ ዕቃ (Item) ሊታይ የሚችል ሸቀጥ (Commodity) ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዕቃ ከሌላው ለየት የሚያደርገው በተጠቃሚው ዘንድ ምን ያህል ተፈላጊ ነው የሚለው ነው። አገሮች በተፈጥሮ ያላቸው ሀብት ውስን ቢሆንም ሁሉም አገሮች የታደሉት የተፈጥሮ ሀብትም በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት ይለያያል። በዚህም ምክንያት እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ለሰው ልጅ አስፈላጊ በመሆናቸው አንዱ አገር የሌለውን ከሌላው አገር ወስዶ ይጠቀማል፡፡ ሌላኛው አገር የሌለውን እንዲሁ ካለው አገር በመውሰድ ይጠቀማል፡፡ በዚህ መካከል አገሮችን የሚለያያቸውና የሚያበላልጣቸው ነገር ያላቸው የተፈጥሮ ሀብትና ጥቅም ላይ የሚያውሉበት (Exploitation of Natural Resources) መንገድ በጥሬውም ይሁን እሴት ተጨምሮበት (Raw, Sumi-Finished or Finished) የአገር ውስጥ ፍላጎት አሟልቶ ለሌላ አገር ማቅረብ በሚችሉበት ብቃትና ችሎታ ልክ ነው።

ስለዚህ አገሮች ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት ብዛት፣ የመጠቀም ችሎታና ለሌላ አገር በሚልኩት ልክ ገንዘባቸው የጠነከረ ወይም የለሰለሰ (Hard or Soft Currency) ይሆናል። እ.ኤ.አ. በ1944 በብሪተን ውድ ስምምነት ጊዜ (The Brittonwoods Agreement) ወርቅን እንደ ሁለንተናዊ መሥፈርት በመጠቀም ቋሚ የምንዛሪ ተመን መፍጠር የሚቻልበት ሥርዓት ተዘርግቶ ነበር። በአሠራሩም ወርቅ ያላቸው አገሮች ለአሜሪካ በዶላር ይሸጡ ነበር። ሸጠው ባገኙት ዶላር ደግሞ የሚፈልጉትን ዕቃ ከዓለም ይሸምታሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ አገሮች በኢኮኖሚ የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ በታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ ጆን ሜይናርድ ኬንስ (John Maynard Keynes 1883-1946) ሐሳብ አመንጭነት የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ የተቋቋሙት በዚያን ጊዜ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ ዶላር የሚቀርብለትን ወርቅ ለመግዛት አቅም ስላነሰው ሥርዓቱ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 1971 በመፍረሱ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአገሮች ገንዘቦች እርስ በርሳቸው ፍሎት (floating Exchange Rate) መጠቀም  ጀመሩ። ተንሳፋፊ ወይም ተለዋዋጭ የምንዛሪ ተመን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ክስተቶችን በሚመለከት የምንዛሪ ዋጋ እንዲለዋወጥ የሚፈቅድበት የምንዛሪ ተመን ዓይነት ነው።

በሌላ በኩል ቋሚ የምንዛሪ ተመን ማለት ደግሞ በመንግሥት ወይም በማዕከላዊ ባንክ የሚደነገገው የአገሪቷን ምንዛሪ ይፋዊ የምንዛሪ ዋጋ ከሌላ አገር ምንዛሪ ዋጋ ጋር የሚያቆራኝ ነው። ቋሚ የምንዛሪ ተመን ሥርዓት የአንድን ገንዘብ ዋጋ በውስን አቅም ውስጥ የማቆየት ዓላማ አለው። ጥቁር ገበያ ማለት የውጭ ምንዛሪ ልውውጥ መደበኛ ባልሆነ ወይም ሕገወጥ በሆነ የምንዛሪ ተመን ማካሄድ ማለት ነው። አንድ ማዕከላዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ውስጥ በየጊዜው ጣልቃ ካልገባ ጥቁር ገበያ መኖሩ የማይቀር ጉዳይ ነው። በመሆኑም ማዕከላዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማስፈን ካልቻለ ግብይቱ አቅርቦትንና ፍላጎትን መሠረት ወደ አደረገው ጥቁር ገበያ ይሄዳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የትኛውን የውጭ ምንዛሪ ግብይት አካሄድ ትከተል የሚለው ብዙዎችን እያወዛገበ ይገኛል። ነገር ግን እዚህ ጋ መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለችው የነፃና የዕዝ ወይም ቅይጥ ኢኮኖሚ ነው። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት በዕዝ ወይም በትመና የሚመራ ነው። በዚህ ሒደት ውስጥም የውጭ ምንዛሪ ገበያው ጤንነት አይታይበትም። ይህም ማለት ከጥቁር ገበያ ዋጋ ጋር ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ይህም በመሆኑ ምክንያት አገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በእጅጉ ቀንሶታል።

ይህ ከሆነ ዘንድ ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ችግር በምን መልኩ አስተካክላ የገጠማትን እጥረት መቅረፍ ትችላለች የሚለው ቁልፍ ነገር ነው። ይህን  ቁልፍ ነገር ለማወቅ ደግሞ የችግሩ ምንጭ ምንድነው የሚለውን ነገር ድምዳሜ ላይ መደረስ አለበት። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ለገጠመው የኢኮኖሚ ችግር ዋና ምክንያቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት እንደሆነ ታምኖበታል። ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ባለበት ሁኔታ በሌላ የኢኮኖሚ ችግር መፍቻ መሣሪያ (የብርን የውጭ ምንዛሪ የመግዛት አቅም ማዳከም) የውጭ ምንዛሪ ገበያ ችግርን እፈታለሁ ብሎ ማሰብ በጣም የዋህነት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተወሰደ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃ ጥሩና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ የዚህን የፖሊሲ ዕርምጃ ውጤት በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋል። ያም ሆኖ ግን እየተወሰደ ያለው የፖሊሲ ዕርምጃ በብዙዎች ዘንድ ለምትታሰበውና የዓለም ኢኮኖሚ መሪ ትሆናለች ተብላ ተስፋ ለተጣለባት ኢትዮጵያ ግን ፈጽሞ የማይመጥን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሪ ዋጋን ከፍ ማድረግ ወይም ለገበያው መተው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ምክረ ሐሳብ እየቀረበ እንደሆነ ይነገራል።

በመሠረቱ ይህን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ሊያስተካክለው ወይም ሊያረጋጋው የሚችለው እየተወሰደ ያለው የማክሮ ኢኮኖሜ ዕርምጃ ነው። ይህ ደግሞ አሁን ገና በሒደት ላይ ይገኛል። ሒደቱ እስኪጠናቀቅና ውጤቱ እስኪታይ ድረስ መነካካት አያስፈልግም። የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለመጨመር ተብሎ በሕጋዊ ምንዛሪዎች ወደ ጥቁር ገበያ ዋጋ እየተጠጉ ግብይት መፈጸም ለጥቁር ገበያው እንደማገዝ ይቆጠራል። ነገር ግን በመደበኛው ግብይት ፀንቶ መቆየት የጥቁር ገበያውን የውጭ ምንዛሪ አቅም በግልጽ ለማየት ይረዳል።

አንድ የአሜሪካ ዶላር በመደበኛ ግብይት የመግዣ ዋጋ 57 ብር ነው እንበል፡፡  በሌላ በኩል የጥቁር ገበያ ዋጋ 115 ብር ቢሆንና ገንዘብን የማጥበቅ ፖሊሲ ዕርምጃ (Tightening Monetary Policy Action) የሚወሰድ ከሆነ ሌላ ማስተካከያ መሥራት አያስፈልግም። በጥቁር ገበያ 120 ብር ገደማ የነበረው የአንድ ዶላር ወጋ በመውረድ ወደ 57 ብር ገደማ እየተጠጋ በመሄድ ልዩነቱ ይጠባል፡፡ አሁን ግን በስፋት እየተወራ ያለው የብርን የውጭ ምንዛሪ የመግዛት አቅም ስለማዳከም ነው። ነገር ግን ከጅምሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕርምጃ ሲወሰድ የጥቁር ገበያውን ዋጋ አውርዶ በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛው ግብይት ሥርዓት የሚያመጣ መሆን አለበት። በዚህ ጊዜ ውስጥ በሌላ መንገድ መነካካቱ ዕቅዱን ሊያደናቅፍ ይችላል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕርምጃ መወሰድ ከጀመረ አንድ ዓመት ገደማ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ቀጣይ የዕርምጃዎችን ውጥረት ሊያረግቡ የሚችሉ የገንዘብ ፖሊሲዎች ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ላይ ይፋ ተደርገዋል። ያም ሆነ ይህ ሲደረግ ግን በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ለውጥ ሲመጣ አልታየም። ይህ ለምን ሆነ ብሎ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። አቅም ያላቸው የዘርፉ ተዋንያን የገበያውን አቅም ሳይረዱ በውድ ዋጋ እየገዙ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ተዋንያን በውድ ዋጋ የሚገዙት የጥቁር ገበያው አቅም አለው ብለው ስለሚያስቡ ነው። ነገር ግን እነዚህ ተዋንያን ለተወሰነ ጊዜ የውጭ ምንዛሪን በውድ ከመግዛት ተቆጥበው ወደ መደበኛው ዋጋ ቢመለሱ ትክክለኛውን የጥቁር ገበያ አቅም ለማወቅ ይረዳል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎች ይብዛም ይነስም ፖሊሲ አውጥተው እየተተገበረ ይገኛል። በዚህ ትግበራ ውስጥ ግን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለማስፈን ተብሎ ብዙ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ይታያል። የማክሮ ኢኮኖሚ ዕርምጃ መውሰድ በጣም ብዙ መስዋዕትነት የሚያስከፍልና ልዩ ክትትል የሚሻ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በራሱ የቆመና የሌሎችን ፖሊሲና መመርያዎችን ድጋፍ የማይፈልግ መሆን አለበት። ስለዚህ አንዴ ፖሊሲው  የመወዳደሪያ ሜዳ ላይ ከዋጋ ንረት ጋር ትግል ገጥሟል። ዕገዛ ሊደረግለት አይገባም፣ አሸንፎ ወይ ተሸንፎ መውጣት አለበት። ፖሊሲ አውጭዎች ባወጡት ፖሊሲ የሚተማመኑ ከሆነ ይህን ያድርጉ ካልሆነ ግን ዕርምጃ እየወሰዱበት ያለውን የፖሊሲ መሣሪያ አቅም መፈተሽ አለባቸው።

የማክሮና የማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃዎች በተመሳሳይ ጊዜ መወሰድ የለባቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተወሰደ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕርምጃ በጣም ጠንካራና በድንገት አንድ ቀን ዋጋን በፍጥነት ሊያወርድ የሚችል፣ ወይም ጠንካራ ማረፊያ (Hard Landing) የሚባለው ዓይነት ይመስላል። ይህ ደግሞ በጣም ከባድና ድርጅቶችን ለኪሳራና ኢኮኖሚውን ደግሞ ለድቀት ሊዳርግ ስለሚችል ማዕከላዊ ባንኩ ‹‹ቤልአውት›› ለማድረግ በተጠንቀቅ መቆም አለበት። ለዚህ ዝግጅት ደግሞ በቅርቡ ረቂቅ አዋጅ የወጣለት የመንግሥት የቀጥታ ብድር መጠን ገደብ አዋጅ አሁን ጊዜው እንዳልሆነ ያሳየናል። ነገር ግን ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የተወሰደው የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያ ማሻሻያ የጠበቀውን የገንዘብ ፖሊሲ በመጠኑም ቢሆን በማርገብ፣ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን የመውደቅ ሥጋት ወይም ጫና ይቀንሳል።

ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር መንግሥትም ሆነ እኛ ዜጎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ችግር አክብደን ማየታችንና አስተሳሰባችንም ከዚህ ችግር ጋር የተቃኘ መሆኑ  ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግር በጣም ቀላልና በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቁልፍ የሚባሉ ነገሮች የተረጋጋ የዋጋ ንረት መፍጠር፣ የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስፈንና ሰላምና ፀጥታን ማረጋገጥ ላይ ጠንክሮ መሥረት ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ግን ዓለም እየተከተለው ያለውን የኢኮኖሚ ትርክት በመሠረታዊነት መቀየር ካልቻለ፣ የአገሮች ኢኮኖሚ ከቀውስ ሥጋት ነፃ ሆነው መቀጠል የማይችል መሆኑን ብዙ ሁኔታዎች እያመላከቱ ይገኛሉ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getaneh25@yahoo.com ማግኘት ይቻላል።