የዓለም ባንክ

ከ 4 ሰአት በፊት

ዓለም ባንክ በድጋፍ፣ ለዕዳ ሽግሽግ እና ለረዥም ጊዜ ብድር ክፍያ በአጠቃላይ 16.6 ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ባንኩ ትናንት ምሽት ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ “የኢትዮጵያን የመጀመሪያና ቀጣይነት ያለው አካታች ዕድገት የልማት ማሻሻያ ፖሊሲ እርምጃ” ማጽደቁን አስታውቋል።

የባንኩ ቦርድ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እና ብድር ማጽደቁን አስታውቆ ከዚህ መካከል 1 ቢሊዮን ዶላሩ ድጋፍ ሲሆን 500 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ብድር ነው።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ የለያዩ ማዕቀፎችንም ይፋ አድርጓል። በዚህ መሠረት የ1 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ ድጋፍ ይፋ ተደርጓል።

የዕዳ ክፍያ እንዲራዘም 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተደርጓል።

ለበጀት ድጎማ ደግሞ በየዓመቱ የሁለት ቢሊዮን ድጋፍ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚደረግ የ6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ትብብር 320 ሚሊዮን ዶላር፣ 1.15 ቢሊዮን ዶላር የባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ እና 2.1 ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ለኢንቨስትመንት ታገኛለች።

ይህ የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት አማካይነት እንዲወሰን አድርጓል።

መንግሥት የወሰደው እርምጃ ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ጠቀሜታ አለው ይላል።

የውጪ ምንዛሪ ገብይት ማሻሻያው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተገቢው መንገድ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን እና ለነዋሪዎች እንዲሁም ለአምራቾች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ያግዛል ብሏል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከወጪ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እና የገበያ ድርሻቸው እንዲያድግ ያበረታታል የተባለ ሲሆን የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማሻሻል አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካቶች የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ የገበያ ንረትን የከፋ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ አሉታዊ ነገሮችን ይዞ ይመጣል የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።