ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕ/ት ኢሳያስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ባሻሻለ እርምጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አሥመራ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አቀባበል በተደረገላቸው ጊዜ

ከ 6 ሰአት በፊት

ባለፈው ሳምንት የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ የሚያደርገው በረራ ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲቆም መወሰኑ ይታወቃል።

ለዚህም የተሰጠው ምክንያት “ምክንያታዊ ያልሆነ የቲኬት ዋጋ መጨመር፣ የመንገደኞች ንብረት መበላሸት እና መጥፋት፣ የበረራ መዘግየት እና የመንገደኞች እንግልት” የሚል ነው።

በኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረው የአውሮፕላን በረራ ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም. ነበር መልሶ የጀመረው።

ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርጋቸው በረራዎች ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሮ በሳምንት አስከ ሰባት ደርሷል። ከዚህም በላይ ከፍ እንዲል ከኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን በኩል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ተገልጿል።

ከአፍሪካ ዋነኛ ለሆነው አየር መንገድ የኤርትራ የበረራ መስመር መከፈቱ ተጨማሪ ገበያ እንዲያገኝ ከማድረጉ በተጨማሪ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚነሱ ኤርትራውያን ጉዞ አመቺ አማራጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የየብስ ትራንስፖርት ግንኙነታቸው ገና ላልጀመረው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋኛው የትስስር መስመራቸው ሆኖ ቆይቷል። ይህ ኤርትራ በረራውን የማቋረጥ ውሳኔ በርካቶችን ያስደነገጠ ሆኗል።

ከእነዚህም መካከል ብርኽቲ አንዷ ናት በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የእርቅ መንፈስ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን “የስልክ ወይም የበረራ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ስንጸልይ ነበር!” በማለት ውሳኔው ዱብ ዕዳ እንደሆነባት ትናገራለች።

ዕገዳው ፖለቲካዊ ወይስ. . . ?

የኤርትራ አየር መንገድን እና የፋይናንስ ዲፓርትመንትን ለበርካታ ዓመታት የመሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ክብሮም ዳፍላ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድን በረራ “በደካማ አገልግሎት” ለማገድ መወሰኑ ፖለቲካዊ ነው ይላሉ።

በኤርትራ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ አራት ድርጅቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ክብሮም፣ እሱም የመጀመሪያው ሰዎች እና እቃዎችን በአውሮፕላን የሚያጓጉዘው አየር መንገድ፣ ሁለተኛው የተጓዦችን እና የአውሮፕላኖች ደኅንነት የሚቆጣጠረው የሲቪል አቪዬሽ፣ ሦስተኛው ደግሞ አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን አራተኛው የትኬት ቢሮ ነው።

“እናም የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በረራዎችን ለማገድ የወሰደው እርምጃ መነሻው የተሳፋሪዎች መንገላታት ነው ብሎ ለማመን አዳጋች ነው” ይላሉ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ፍትዊ ወልደይ በበኩላቸው “የሚመለከታቸው የኤርትራ ባለሥልጣናት እንደዚህ ዓይነት ድንገተኛ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያነሷቸው ጉዳዮች እንዲሻሻሉ መጠየቃቸውን በሚዲያ ይፋ ማድረግ ነበረባቸው።

“በድንገት በማስታወቂያ መልክ የተገለጸው የበረራ እገዳ መነሻ ፖለቲካዊ ይሁን ተራ የንግድ ውዝግብ . . . እኛ የምናውቀው ነገር የለም” በማለት የተሰጠው ማብራሪያው አጥጋቢ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።

ጨምረውም ብዙ ኤርትራዊያን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ደካማ መሆኑን ሲያማርሩ እንደነበር መደመጡን፣ ነገር ግን በወቅቱ ግልጽ የሆነ የማስተካከያ እርምጃ አለመወሰዱ፣ እንዲሁም አሁን ይፋ በተደረገበት አግባብ መገለጹ በ1990 ከነበረው ልምድ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለው ይላሉ።

ግራ አጋቢው የዕገዳ ውሳኔ

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉድለቶቹን እንዲያስተካክል እና ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍል እንደተጠየቀ ቢገልጽም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በረራው እንደሚቋረጥ እንጂ የተባሉት ዝርዝር ችግሮችን በተመለከተ የተገለጸለት ነገር እንደሌለ አሳውቋል።

ሮይተርስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቃል አቀባይ ሃና አጥናፉን ጠቅሶ እንደዘገበው አየር መንገዱ በድንገተኛው የበረራ እገዳ መደናገጡን ገልጸው ችግሩ በንግግር መፍትሄ እንደሚያገኝ ገልጸዋል። የዜና ወኪሉ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀልን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።

የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ “ኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን በሐምሌ 1/2016 ዓ.ም. ሳምንታዊ በረራችንን ከ10 ወደ 15 እንድናሳድግ በጽሁፍ ጠይቆን ነበር” በማለት ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን “አስደንጋጭ ነው” ያሉት ውሳኔ መምጣቱን ተናግረዋል።

ዶ/ር ፍትዊ እንደሚሉት በጊዜው መስተናገድ የነበረባቸው ሁኔታዎች ዘግይተው ከሕዝብ ዐይን ተደብቀው ከቆዩ በኋላ አዳዲስ ነገሮች ወይም ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንደ ምክንያት ለሕዝብ እንደሚገለጹ ይናገራሉ።

ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ለማቋረጥ ያሳለፈችው ውሳኔ ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል የሚለው ግምት በማኅበራዊ ሚዲየዎች ላይ ጭምር መነጋገሪያ ሆኗል። በኤርትራ በኩል በአየር መንገዱ ላይ የቀረቡት ቅሬታዎች በመነጋገር መፍትሄ ሊገኝላቸው የሚችሉ ጉዳዮች በመሆናቸው እዚህ ውሳኔ ላይ የሚያደርሱ አይደሉም ይላሉ።

በአፍሪካ እና በመላው ዓለም ወደ 140 የሚጠጉ የበረራ መስመሮች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ ከሚጓዙ ጥቂት ሌሎች አየር መንገዶች በበለጠ በሳምንት በርካታ በረራዎች ያሉት ነው።

ከቀሪው ዓለም ወደ አሥመራ እና ከአሥመራ ወደ ሌሎች መዳረሻዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መንገደኞችን በማጓጓዝ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲሠራ የቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመስከረም ወር አጋማሽ በረራው እንደሚቋረጥ ከተነገረ በኋላ እስካሁን የተቀየረ ነገር ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን እገዳውን በተመለከተ የሕዝብ ማስታወቂያ ካወጣ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማብራሪያ መጠየቁን እና ማንኛውንም ችግር በወዳጅነት በአፋጣኝ ለመፍታት እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር።

ዕገዳው ምን ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ይኖረዋል?

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ባወጣው ማስታወቂያ “ሁሉም የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞች የበረራ መስተጓጎል እንዳይፈጠር በጊዜው አማራጮችን እንዲፈልጉ” ቢያሳስብም እንዲህ ዓይነት ድንገተኛ የበረራ አገልግሎት መቋረጥ በተለይ የረጅም ጊዜ ትኬት የገዙ መንገደኞች ቲኬታቸውን ለማስተካከል ተጨማሪ ክፍያ ሊጠየቁ ይችላሉ።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተቋረጠ በአሁኑ ወቅት በስደት በኢትዮጵያ እና በኡጋንዳ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራውያን እና ከተለያዩ የምዕራብ አገራት ልጆቻቸውን ለማየት በሚጓዙ ወላጆች በሌሎች አየር መንገዶች ለመጠቀም ስለሚገደዱ ለተጨማሪ ክፍያ ይዳረጋሉ። ይህም ተጠቃሚው ላይ ተጨማሪ ጫና እንደሚያስከትል ብርኽቲ ታስረዳለች።

ሆኖም የኤርትራ መንግሥት ከሳምንታት በፊት የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፈተሽ ከመጡ የጣሊያን ባለሥልጣናት ጋር ከጣሊያን ወደ ኤርትራ በረራ ለመጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመወያየቱ ሌላ አማራጭ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት እንዳላት ታክላለች።

አቶ ክብሮም ዳፍላም በኤርትራ ኢኮኖሚውን የሚጎዳ ገቢም ሆነ ወጪ የንግድ በረራ ስለሌለ መንግሥት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የወሰደው እርምጃ በኤርትራ ምጣኔ ሃብት ላይ ብዙ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለው አያስቡም። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተለማምዶ የነበረው የኤርትራ ደንበኛ የአማራጭ እጥረት ሊያጋጥመው ይችላል ይላሉ።