ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን
የምስሉ መግለጫ,ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን

ከ 58 ደቂቃዎች በፊት

የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጸመ።

የጦሩ ቃል አቀባይ ነቢል አብደላህ በጄኔራል አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸመው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የሱዳን ጦር በጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔምቲ) ጋር ከሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ጦርነት ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የግድያ ሙከራው የተፈጸመው ጄኔራል አል-ቡርሃን በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በሠራዊት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመው በነበረበት ወቅት ነው ተብሏል።

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ማብቂያ ላይ በተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶች ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

በግድያ ሙከራው አል-ቡርሃን ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመው በድሮን ጥቃት መሆኑን የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው የአገሪቱ ጦር ዋና መቀመጫው ካደረጋት ፖርት ሱዳን 100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ጊቤት በተባለ የጦር ሰፍር ውስጥ ነው።

የግድያ ሙከራ የመፈጸሙ ዜና የተሰማው የሱዳን መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ከተስማማ በኋላ ነው።

የሱዳን መንግሥት የሰላም ንግግር ለማድረግ የተስማማው በአሜሪካ ጥያቄ በስዊትዘርላንድ በሚደረግ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ነው።

ይህ የሰላም ንግግር ለ15 ወራት ለዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋን አጭሮ የነበረ ቢሆንም በአል-ቡርሃን ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ የሰላም ተስፋውን ሊያጨልመው ይችላል የሚልስ ስጋት ፈጥሯል።