August 4, 2024 – Konjit Sitotaw 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የአመጽ እንቅስቃሴዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚል የመንግስት ግምገማ እንዳለ ምንጮች ጠቆሙ

መሰረት ሚድያ– ከሰሞኑ ይፋ የሆነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በአንዳንድ ስፍራዎች፣ በተለይ ደግሞ በመዲናዋ አዲስ አበባ የአመፅ እንቅስቃሴዎች ሊከሰቱ ይችላሉ የሚል የመንግስት ቅድመ ግምገማ እንዳለ ምንጮች ለመሰረት ሚድያ ጠቁመዋል።

እነዚህ ምንጮች እንደጠቆሙት ይህን ግምገማ ተከትሎ “የከተማዬ ሰላም የኔም ሰላም ነው” እንዲሁም “እኔ የአካባቢዬ የሰላም ዘብ ነኝ” በሚሉ መፈክሮች የታጀቡ የማታ ሮንድ (ቁጥጥር) ስራዎች በበርካታ ክፍለ ከተሞች ባለፉት ሶስት ቀናት ተጀምረዋል።

በርካታ የመሰረት ሚድያ ተከታታዮችም ይህን በየአካባቢያቸው እንደታዘቡ ጥቆማ ሰጥተዋል።

“የሰላም ሰራዊት የሚል ስያሜ ያላቸው እነዚህ አደረጃጀቶች ከበፊቱ ላቅ ያለ ቁጥጥሮችን እንዲያረጉ ተደርገዋል” ያሉን ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣን ይህም የሰሞኑን የማክሮ ኢኮኖሚ ውሳኔ ተከትሎ መሆኑን አረጋግጠዋል።

እነዚህ ሰማያዊ እና ነጭ ልብስ የለበሱ የሰላም ሰራዊት አባላት በህብረተሰቡ በቀላሉ የሚለዩ ስለሆነ ሌሎች እነሱን መስለው ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ህገወጥ አካላትን ህብረተሰቡ በቀላሉ መለየት እንደሚችል እኚህ ባለስልጣን ጨምረው ገልፀዋል።

ከሰሞኑ ይፋ የሆነውን ማሻሻያ ተከትሎ በርካታ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የተመዘገበ ሲሆን የአንድ ዶላር የምንዛሬ ተመንም በአንዳንድ ባንኮች ከ100 ብር በላይ አሻቅቧል።

መሰረት ሚድያ ባደረገው የማህበራዊ ሚድያ ዳሰሳ በበርካታ የከተማው ክፍለ ከተሞች የሰላም ሰራዊት ስምሪት ተጀምሯል።