

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)
ዜና መንግሥት ያለ ሰላምና መረጋጋት የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አይሳካም አለ
ቀን: August 4, 2024
- እንደ ኮሶ መድኃኒት መራር ውሳኔ መወሰኑን ገልጿል
ከሰሞኑ እየወሰደው ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳዎች በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጠው መንግሥት፣ ያለ ሰላምና መረጋጋት ሪፎርሙ እንደማይሳካ አስታወቀ፡፡ መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለዓለም ገበያ በመክፈት ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲያድግ የሚያደርግ ሪፎርም ማድረጉን ገልጾ፣ ኢኮኖሚውን ከውድቀት የሚታደግና የሚያክም ነው ያለውን ሪፎርም እንዲሳካ ግን ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ሰፊ ገለጻ የሰጡበት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው የውይይት መድረክ፣ የመንግሥትን ሰሞነኛ የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕርምጃዎች በተመለከተ በርካታ ሐሳቦች የተነሱበት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሪፎርሙ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ መፍጠር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ‹‹የዚህ ሪፎርም አንዱ ወሳኝ መሠረት ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ካልመጣ፣ ኢንቨስትመንት አይመጣም፣ የቱሪስት ፍሰት እንደምንፈልገው አይኖርም፣ እኛም እንደምንፈልገው ተንቀሳቅሰን መማርና መሥራት አንችልም፡፡ ሰላምና መረጋጋት የግድ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሁለትና ሦስት ወራት በመንግሥታቸውና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት የሚያስነሱ ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች ቢኖሩም፣ ከአሥር ያላነሰ ጊዜ ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ከአማራ ክልል ኃይሎች ጋር በሚስጥር ባለፉት ወራት ውይይት ሲደረግ መቆየቱን፣ ከኦነግ ሸኔ ጋርም ሰላም ለመፍጠር ጥረቱ መቀጠሉን ያመለከቱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ሆኖም በተበታተነ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በመሆናቸው ወደ አንድ ሰብሰብ ብለው ለድርድር ካልቀረቡ የሰላም መፍጠር ጥረት ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ኢኮኖሚውን ሪፎርም ለማድረግና ለዓለም ገበያ ክፍት ለማድረግ የወሰደው ውሳኔ መራር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዕርምጃው ያስፈልጋል ሳይሆን የዘገየ ነው፡፡ መጨከን ያስፈልገናል፡፡ እንደ ኮሶ የሚመር ቢሆንም ሕማመችን እንዲሽር ስንል የዋጥነው መራር ውሳኔ ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡
ገበያን መክፈትም ሆነ ኢኮኖሚን ሪፎርም የማድረጉ ውሳኔ ገና ኢሕአዴግ ሳይፈርስ የተወሰነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ በለውጥ ማግሥት እሳቸው ወደ ሥራ በመጡ በወሩ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የንጉሡ መንግሥትም ሆነ የደርግና የኢሕአዴግ መንግሥታት ከእነ አይኤምኤፍ ጋር ሲሠሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
‹‹በስንት ልመናና በስንት ጭቅጭቅ የተገኘ የልማት ድጋፍን በእነ አይኤምኤፍ ተጠመዘዛችሁ ይባላል፡፡ እኛ ከአይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ጋር በመሥራታችን የእነሱ ድል ተደርጎ ለምን ይታያል? የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርማችንን እንዲቀበሉ አድርገን፣ የ4.9 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሽግሽግ አግኝተን፣ እንዲሁም ንግድ ባንክን ከዕዳ መታደጊያ 700 ሚሊዮን ዶላር እንዲለቁ በማድረግ ያሳካነው አጋርነት ነው፤›› በማለት ከውጭ የልማት ተቋማት ጋር የተደረገው ስምምነት መቃለል እንደማይኖርበት ነው የተከራከሩት፡፡
በዚሁ ማብራሪያቸው እግረ መንገዳቸውን መንግሥታቸው ስላሳካቸው የልማት ሥራዎች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ቆሞ የነበረውን ህዳሴ ግድብ 500 ሚሊዮን ዩሮ ካሳ በመክፈል ሥራውን በማስጀመር፣ ዛሬ ላይ የሲቪል ሥራው መቶ በመቶ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖን ተቋቁሞ ባለፉት ዓመታት ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ መክፈሉን፣ በስንዴ ልማት፣ በሩዝ ልማት፣ በጫካ ፕሮጀክት፣ በቴሌኮም፣ በቤት ግንባታ፣ በኮሪደር ልማት በርካታ ስኬቶች ማስመዝገቡን ዘርዝርዋል፡፡